ዋዜማ ራዲዮ – በኢትዮጵያ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓም መሰጠት የተጀመረው የኮቪድ19 ክትባት እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መዳረሱን የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሙሉቀን ዮሀንስ ዛሬ ለዋዜማ ሬድዮ ተናግረዋል፡፡


“እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በደረሰን መረጃ መሰረት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተከትበዋል፡፡ ክትባቱን በተመለከተ የተለያዩ የተዛቡ እና አንዳንዴም የተጋነኑ መረጃዎች በማህበራዊ ድህረገፆች ቢሰራጩም እስካሁን በሰዉ ዘንድ ያለው አቀባበል ጥሩ ነው ” ብለዋል ዶ/ር ሙሉቀን፡፡


አክለውም “ክትባቱ ሊያስከትላቸው ከሚችላቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ጋር ተያይዞ ስለ ደም መርጋት የተለያዩ መረጃዎች ቢወጡም ተጨባጭ የሆነ ጥናት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በማህበራዊ ድህረገፅ የሚወጡት የተጋነኑ መረጃዎች የክትባቱን በጎ ጎኖች የሚሸፍኑ ናቸው” ብለዋል፡፡


ዋዜማ ሬዲዮ እስካሁን ክትባቱን ከወሰዱት ሰዎች መካከል የጎንዮሽ ጉዳት የተፈጠረባቸው ሰዎች አሉ ወይ የሚል ጥያቄ ለአማካሪው ያቀረበች ሲሆን እሳቸውም ጥያቄውን የአወንታ ምላሽ ሰጥተውታል፡፡


ይሁን እንጂ የደረሰባቸውን የጎንዮሽ ጉዳት ሙሉ በሙሉ መርምሮ የሚያሳውቅ የህክምና ቴክኖሎጂ እንደሌለ እና ባለው ቴክኖሎጂ በተደረገላቸው ህክምና መሰረት የከፋ ጉዳት የሚያደርስ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡


አክለውም የኢትዮጵያ መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጥናት እያደረገበት ስለመሆኑ በመግለፅ “የጥናቱን ሪፖርት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይፋ ሲያደርገው ይታወቃል” ብለዋል፡፡


ክትባት መስጠቱ እስከ ግንቦት ወር ድረስ የሚቀጥል መሆኑን ዶ/ር ሙሉቀን ተናግረዋል
በኮቫክስ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የካቲት 28 ቀን 2013 ዓም 2.2 ሚሊዮን አስትራዜኒካ የተባለውን የኮቪድ 19 ክትባት ኢትዮጵያ የተረከበች ሲሆን ተጫማሪ 5.3 ሚሊዮን ገደማ ክትባቶችን እስከ ግንቦት ወር ድረስ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]


የዋና አዘጋጁ ማስታወሻ– የሚባለው ጉዳት እጅግ አልፎ አልፎ ሊገጥም የሚችልና አደጋ ላይ የማይጥል ሲሆን ጎላ ብለው የታዩ ችግሮች በሚታዩበት ወቅት ወደ ሕክምና አገልግሎት መሄድ ያስፈልጋል። ክትባቱ በተወሰደ ዕለት አልያም በማግስቱ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ቁርጥማትና የመደበት ስሜቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህ ክትባቱ በሰውነታችን ውስጥ መስራትና መዋሀድ ሲጀምር የሚያጋጥም ምልክት ነው። የከፋ ትኩሳት ከተከሰተ ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል።