book-venderosዋዜማ ራዲዮ- መጻሕፍትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሕትመት ዉጤቶችን ለማሳተም ማተሚያ ቤቶች ፍቃደኛ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ሙሉ ክረምቱን መነቃቃትና እምርታን እያሳየ የነበረው የሕትመት ዘርፍ መቀጨጭ ይዟል ይላሉ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች፡፡

አንዳንድ ደራሲዎች በተለይ ረቂቅ ሥራዎቻቸውን ወደ ማተሚያ ቤት ይዘው ሲሄዱ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) እየተደረገባቸው እንደሆነ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

“ረቂቁን በባለሞያ እስመርምረን ዉጤቱን በሳምንት ዉስጥ ደውለን እናሳውቅሀለን” ተብሎ እንደነበር የተናገረ ወጣት ደራሲ ከ10 ቀን በኋላ ተደውሎ “የሽፋን ሥዕሉ ከመንግሥት ጋር ሊያጋጨን ስለሚችል ቀይረው” እንደተባለ ይናገራል፡፡ “በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ያጌጠ ሽፋን እንዴት አድርጎ ከመንግሥት ጋር እንደሚያጋጭ ሊገባኝ አልቻለም” ይላል ግርምትና ሳቅን በቀላቀለ ድምፀት፡፡

ፍጹም ከፖለቲካ ጋር ያልተያያዙ የፈጠራ ሥራዎችም ቢሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት እክል አጋጥሟቸዋል፡፡

አዲስ የፈጠራ ሥራውን ከሰሞኑ ወደ ማተሚያ ቤት ይዞ እንደሄደ ለወዳጆቹ የተናገረው ደራሲ ዘነበ ወላ መጀመርያ የሄደበት ማተሚያ ቤት ረቂቂን ከተመለከተ በኋላ ‹‹እኛ እንድናትምልህ ከፈለክ ከኮማንድ ፖስቱ “ቢታተም ችግር የለውም” የሚል ደብዳቤ ይዘህ ና!›› መባሉን ተናግሯል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈጠረው ፍርሃት ቀደም ብለው ገበያ ላይ በተሰራጩ ሥራዎች ጭምር ጥላውን እንዳጠላ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡

መቼቱን በቅድመ ደርግ ላይ ያደረገና በፖለቲካ ልቦለድ ዘርፍ ሊመደብ የሚችል መጽሐፍ ሁለት ጊዜ በተደጋጋሚ ታትሞ  ለ3ኛ ጊዜ ለማሳተም ቢፈለግም ማተሚያ ቤቱ አንድ ጊዜ “ጊዜው ጥሩ አይደለም” ሌላ ጊዜ “ችግር ዉስጥ ትከቱናላችሁ” እንዲሁም፣ “እባካችሁ ትንሽ ታገሱን›› በሚል ሰንካላ ምክንያት መጽሐፉን ለማሳተም እንዳልፈቀደ ደራሲውና አሳታሚው ለዋዜማ ዘጋቢ ነግረውታል፡፡ በዚህም የተነሳ በድጋሚ ሕትመት ቅናሽ ማግኘት የሚችሉበትን ማተሚያ ቤት ትተው የረቂቁን የኮምፒውተር ቅጂ (ሶፍት ኮፒ) ለአዲስ ማተሚያ ቤት ለመስጠት እንደተገደዱ አብራርተዋል፡፡ ይህ ላልተፈለገ የጊዜ መራዘምና ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

“ወደ ደርግ ጊዜ የተመለስን ያህል ነው የተሰማኝ” የሚለው ይህ ደራሲ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለጥጦ የማየት ፍርሃት ተንሰራፍቷል፡፡” ይላል የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ ሰዎች ሰዓት እላፊ እንደታወጀ አድርገው በጊዜ ወደቤት መግባት ጀምረው እንደነበር በማስታወስ፡፡ “መንግሥት ምን እንደተከለከለና ምን እንዳልተከላከለ በግልጽ ሊያስረዳ ኃላፊነት አለበት” በማለት ያሳስባል የዚህ ፖለቲካዊ ልቦለድ መጽሐፍ ደራሲ በግርምት፡፡

ዝዋይ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጋዜጣና መጽሔት ላይ ቀደም ብሎ አትሟቸው የነበሩ ጽሑፎች ተሰብስበው “የፈራ ይመለስ” በሚል ርዕስ ታትመው መሠራጨታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የኾነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ ቀደም ብሎ አመጽ በተቀጣጠለበት ወቅት ነበር፡፡ አዝዋሪዎች እየተዋከቡም ቢሆን በወቅቱ የመጽሐፉ 10ሺ ቅጂዎች በከፍተኛ ፍጥነት ተሸጠው የተጠናቀቁ ሲሆን ከዚያ በኋላ ድጋሚ ሕትመት ለማተም የፈቀደ ማተሚያ ቤት ማግኘት ግን ፈተና እንደነበር አሳታሚው ይናገራል፡፡ “የመጀመርያውን 10ሺ ቅጂ የሠራልን ማተሚያ ቤት ከእንግዲህ ለሕይወቱ እንደሚሰጋ ገለጠልን፡፡ ሌሎች ማተሚያ ቤቶችን ስናናግር መሳርያ የደቀንባቸው ያህል ደንግጠው መለሱን፡፡ ከፍ ያለ ገንዘብ ሁሉ አቅርበንላቸው እምቢ ያሉን ማተሚያ ቤቶች አሉ፡፡” ይላል፡፡

“ማተሚያ ቤቶች በተለምዶ ስማቸውን በመጽሐፍ ሽፋን ጀርባ የመጻፍ ልማድ ነበራቸው፡፡ አሁን ያን እየተዉ መጥተዋል፡፡ ይህም የኾነው ያስጠይቀናል፣ መንግሥት እርምጃ ሊወስድብን ይችላል ከሚል ፍርሃት ነው” ይላል ዋዜማ ያናገረችው የደራሲያን ማኅበር አባል፡፡ “ይህን ሁኔታ ለቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አንስተንላቸው ነበር፤” የሚለው ይኸው የደራሲያን ማኅበር ባልደረባ “ሚኒስትሩ ግን በደፈናው “ክሰሷቸው” ብለውን ሄዱ፡፡” ይላል፡፡ “መፍትሄው እነሱን መክሰስ አይመስለኝም፣ አገርን ከገባችበት የፍርሃት ማጥ ማውጣት እንጂ” ሲል ጨምሮ ይገልጣል፡፡

አይናለም መጽሐፍት መደብር፣ ጃፋር መጽሐፍት መደብር፣ አራት ኪሎ የሚገኘው ዩኒቨርሳል መጻሕፍትና ሌሎችም በዘርፉ የተሰማሩ አሳታሚዎችና አከፋፋዮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከፍተኛ የሥራ መቀዛቀዝ እንደተከተለ መስክረዋል፡፡

“ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በሳምንት ቢያንስ ሦስትና አራት መጽሐፍት መታተም ጀምረው ነበር፡፡ ከፍተኛ የንባብ ፍላጎትና መነቃቃትም ተፈጥሮ ነበር፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ግን ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ተለወጠ፡፡ አታምነኝም፣ በቀን 2 መጽሐፍ ሳልሸጥ የዋልኩበት ዕለት አለ” ይላል የዋዜማ ዘጋቢ ያነጋገረው የመጽሐፍ መደብር ባለቤት፡፡