20160221_105401ዋዜማ ራዲዮ- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የነቀዝ መድኃኒት በመውሰድ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ የኦሮሚያ ወጣቶች ቁጥር ማሻቀብ በጳውሎስ ሆስፒታል ሥር የሚገኘው አቤት የድንገተኛ ሕክምና ማዕከል ሐኪሞችን እያነጋገረ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 47 ወጣቶች ተመሳሳይ በሆነ ዘዴ የነቀዝ መድኃኒት ኪኒን በመዋጥ ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸው የተመዘገበ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ የሰላሳ አንድ ወጣቶችን ሕይወት ማዳን እንደተቻለ ዋዜማ ከሆስፒታሉ ታማኝ ምንጮች ያገኘቸው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከጉዳዩ ስሱነት አንጻር ስማቸው መግለጽ ያልፈቀዱና ኾኖም ስለሁኔታው የሚያውቁትን ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊነቱን የሚያምኑ አንድ በጳውሎስ ሆስፒታል የአቤት ድንገተኛ ሕክምና ማዕከል የጤና ባለሞያ ‹‹ክስተቱ ለሁላችንም እንግዳ ሆኖብናል›› ይላሉ፡፡

‹‹ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ሰባት ወጣቶች ተመሳሳይ ራስን የማጥፋት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ሁሉም ሙከራውን ያደረጉት Celphos የሚባል የነቀዝ መድኃኒት በመዋጥ ነው፡፡ ሦስቱ በጣቢያው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሁሉም ወጣቶች ናቸው፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ ሁሉም ሪፈር የተደረጉት ከኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ ይህ ክስተት አጋጣሚ ነው ብሎ ለማለፍ ስለከበደኝ ነው፡፡›› ይላሉ እኚሁ የጤና ባለሞያ ስለ ጉዳዩ ሲያብራሩ፡፡

አቤት የድንገተኛ ሕክምና ማዕከል   በጳውሎስ ሆስፒታል ሥር ኾኖ የተቋቋመ የጤና ማዕከል ሲሆን በእሳት አደጋ፣ በመኪና አደጋና ሌሎች ተያያዥ ድንገተኛ አደጋዎች ጋር በተያያዘ የተጎዱ ሰዎች የሚታከሙበት ልዩ የሕክምና ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በተለምዶ አራትመንታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ተጠሪነቱም ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነው፡፡

ከኦሮሚያ አጎራባች ልዩ ዞኖች ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ ታካሚዎች በተለምዶ ሪፈር የሚደረጉት ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን አቤት የድንገተኛ ሕክምና ማዕከል ራስን የማጥፋት ሙከራን የመሰሉ ጊዜ የማይሰጡ የጤና እክል ያጋጠማቸው በሽተኞችን ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ ማዕከሉ ዉስጥ የሚገኙ ሐኪሞችን እያነጋገረ ያለው ጉዳይም እንዴት በተመሳሳይ ጊዜ፣ ከተመሳሳይ ቦታ በሚመጡ ወጣቶች ይህን ያህል ቁጥር ያለው ራስን የማጥፋት ሙከራ ሊደረግ ይችላል የሚለው ነው፡፡

ኾኖም ከኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ሪፈር የተባሉ ራስን የማጥፋት ሙከራዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጅጉ መበራከት መንስኤው ምን እንደሆነ በውል የሚናገር ሰው የለም፡፡ ክስተቱ በኦሮሚያ ተፈጥሮ ከነበረው አመጽ በኋላ መኾኑ ምናልባት ወጣቶቹ ላይ የተፈጠረ አንዳች ተስፋ መቁረጥ ያመጣው ጣጣ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ ሰዎች ግን አልታጡም፡፡ በተቃራኒው ይህ ነቀዝ መድኃኒት በመዋጥ ራስን ለማጥፋት መሞከር ቀድሞም በገጠር አካባቢ የሚዘወተር ተግባር ነው፤ አሁን ልዩ የሚያደርገው ድግግሞሹ ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡

አቤት የጤና ማዕከል ወትሮም ቢኾን ከድንገተኛ አደጋ ጋር በተያያዘ በርካታ ታካሚዎች በመኖራቸው ማገገሚያ አልጋ እንኳ ማግኘት ፈተና እንደሆነ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራስን የማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ታካሚዎች በጊዜ ቢደርሱ እንኳን ማዳን እየተቻለ በባለሞያና በቦታ እጥረት የተነሳ ሕይወታቸው አላግባብ የሚያልፍበት ጊዜ በርካታ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡

‹‹የነቀዝ መድኃኒት የወሰዱ ወጣቶች በሰዓታት ዉስጥ የደም ናሙና ተወስዶ የደማቸው ዐይነት ከተለየ በኋላ በፍጥነት ደማቸውን ማጽዳት ካልተቻለ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የተናገሩት እኚህ የጤና ባለሞያ፣ ኾኖም በሆስፒታሉ በቂ ቦታና በቂ ባለሞያ ባለመኖሩ ‹‹በሕንጻው ወለል ላይ ታካሚዎችን አስተኝተን ሕክምና ለመስጠት የምንገደድበት ወቅት አለ›› ይላሉ፡፡

የሚያገግሙ ታካሚዎች አልጋ ቢያገኙ እንኳን ሙሉ በሙሉ ሳይድኑ ፎርስ ዲስቻርጅ ይደረጋሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ሲባል ነው፡፡ በማዕከሉ ለእያንዳንዱ ታካሚ ሁለት አስታማሚዎች አብረውት እንዲሆኑ የይለፍ ካርድ የሚፈቀድ ሲሆን አሁን አሁን ግን ከሁለቱ አንዱ አስታማሚ በቦታ ጥበት የተነሳ በኮሪደርና በሎቢዎች ወለል ላይ እንዲያድር ይገደዳል፡፡

የድንገተኛ ማዕከሉ ሐኪሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ እያስተዋሉት ባሉት በዚህ እንግዳ ክስተት መገረማቸውን የሚገልጹት እኚህ የጤና ባለሞያ ‹‹በነገሩ ላይ ቁጭ ብለን በቅጡ ባንወያይም ዉስጥ ዉስጡን እርስበርስ መነጋገራችን አልቀረም›› ይላሉ፡፡ ለምን ይህ ክስተት በኦሮሚያ ወጣቶች ዘንድ ሊዘወተር ቻለ ተብለው የተጠየቁት የጤና ባለሞያው ‹‹ከመላምት ያለፈ መልስ ልሰጥሽ አልችልም›› ሲሉ ሙሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በአቤት የድንገተኛ አደጋ ማዕከል የሚያገለግሉ በርካታ ተለማማጅ ሐኪሞች የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹ ከጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ የሚመጡ ዕጩ ዶክተሮች ናቸው፡፡ ከነዚህ ተለማማጅ ሐኪሞች መካከል በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከተጠየቁት መሐል ስሟን መግለጽ የማትሻ አንዲት ዕጩ ሐኪም በነቀዝ መድኃኒት ራስን የማጥፋቱ ነገር በአቤት ማዕከል ዉስጥ የተለመደ እንደሆነ ማረጋገጫ ከሰጠች በኋላ ኾኖም የታካሚዎቹ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እንደምትቸገር፣ የመጡበትን አካባቢም ሆነ ድርጊቱን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳቸው ጠይቃም ሆነ ልብ ብላው እንደማታውቅ አብራርታለች፡፡ ‹‹ በየጊዜው አንድ ሁለት ኬዝ ያጋጥማል፣ አዲስ ነገር አይመስለኝም›› ትላለች፡፡

የነቀዝ መድኃኒት በገጠር ሱቆች እንደልብ የሚገኝ ሲሆን ገበሬዎችን ለማበረታታት በርካሽ ዋጋ የሚሸጥና አገር ዉስጥ ጭምር የሚመረት መድኃኒት ነው፡፡ በአንድ ኩንታል ዉስጥ በማዳበሪያ አንድ ፍሬ ኪኒን የነቀዝ መድኃኒት ማኖር የተለመደ ነው፡፡ በሞያዊ መጠርያው Celphos Fumigant  Insect side በመባል የሚታወቀው ይህ መድኃኒት አንዱ ፓኬት 30 ፍሬን የሚይዝ ሲሆን አንዱን ፍሬ መዋጥ ብቻውን በሁለትና ሦስት ሰዓታት ዉስጥ ሕይወትን ሊያጠፋ ይችላል፡፡

መድኃኒቱ ጠጣር ቢሆንም በትነት መልክ ወደ ጋስነት የመቀየር ባህሪ ሲኖረው ሽታውም የሚቋቋሙት ዐይነት አይደለም፡፡ ይህ የነቀዝ መድኃኒት በገጠር ሱቆች ዉስጥ በአመዛኙ እንደልብ የሚገኝ ሲሆን በአንዳንድ ከተሞች ግን በአዝርእትና የእንሰሳት መድኃኒት ቤት ዉስጥ ብቻ እንዲሸጥ ይደረጋል፡፡ ዋዜማ በተክፊ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታና በቡራዩ የአዲስ አበባ አጎራባች ልዩ ኦሮሚያ ዞኖች ዉስጥ ባደረገችው መደበኛ ሐሰሳና መጠይቆች የነቀዝ መድኃኒት በአማካይ አንዱን ፍሬ  3 ብር፣ እንዲሁም 30 ፍሬ የሚይዘውን ፓኬት 90 ብር እንደሚሸጥ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

ብዙዎቹ አካባቢዎች ላይ ኪኒኑን ለመግዛት ከባለሱቆች መጠነኛ ማጣራትና ጥያቄዎች የሚሰነዘሩ ሲሆን  ሁለት ሆኖ በመሄድ አንዱ ገዢ አንዱ መስካሪ ሆኖ ኪኒኑን በቀላሉ መግዛት እንደሚቻል ታውቋል፡፡ አንዳንድ የአዝርእት መድኃኒት መሸጫዎች ገዢዎች መድኃኒቱን ለእርሻ ሥራ የገዙት ስለመሆኑ በመዝገብ ላይ በፊርማቸው እንዲያረጋግጡ ይደረጋል፡፡ አልያም ገዢው ለምን እንደፈለገው የሚገልጽ ማስረጃ ማቅረብ ያሻል፡፡ ይህ ለምን እንደሚደረግ ከተጠየቁ ባለሱቆች መሐል ‹‹ወጣቶች እየዋጡት ተቸግረናል›› ሲሉ ምላሽ የሰጡ በጅማ መንገድ የሚገኙ የተፍኪ የመድኃኒት መሸጫ ባለሱቅ  ይገኙበታል፡፡

የነቀዝ መድኃኒት መተንፈሻ አካልን፣ ጉበትንና ደምን እንደሚያጠቃ ይታመናል፡፡ ፍሬዎቹ በከፍተኛ መጠን ከተወሰዱ በከፍተኛ ፍጥነት የመግደል እድል አለው፡፡ በአንድ ጊዜ ሦስት ፍሬ የወሰዱ ወጣቶች ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ወዲያውኑ እንደሚሞቱ ታውቋል፡፡

መረጃውን ለዋዜማ ያቀበሉት የአቤት ድንገተኛ ሆስፒታል የጤና ባለሞያ ከአሮሚያ ልዩ ዞኖች ሪፈር የሚደረጉና በነቀዝ መድኃኒት  ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩ ወጣቶች ከአቤት የጤና ማዕከል በተጨማሪ አሁን አሁን ወደ ጴጥሮስ ሆስፒታል እንደሚወሰዱ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጴጥሮስ የምንልካቸው እኛ ዘንድ በቂ የማገገሚያ ቦታ ማግኘት እየከበደ ስለመጣና እዚያ ደግሞ ቶክሲኮሎጂ ማዕከል ስላለ ነው‹‹ ብለዋል እኚሁ የጤና ባለሞያ፡፡ ጴጥሮስ ሆስፒታል ቀድሞ ሳንባ ነቀርሳ ማገገሚያ በመሆን የሚታወቅና ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኝ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ ሆስፒታል ነው፡፡

ይህ ራስን በነቀዝ መድኃኒት የማጥፋት ሙከራ ከኦሮሚያ ወጣቶች ጋር ብቻ የሚያያዝ ክስተት እንዳልሆነ የሚገልጹ የጴጥሮስ ሆስፒታል የቶክሶኮሎጂ ዲፓርትመንት ባልደረባ ‹‹ገበሬዎችና የገበሬ ልጆች በምርት መበላሸት፣ በእዳ መያዝና በኑሮ ዉድነት የተነሳ ብስጭት ዉስጥ ሲገቡ የሚያዘወትሩት ነገር ነው፤ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ሆለታ ድረስ ሄደው መድኃኒቱን ገዝተው በጋራ ራሳቸውን ያጠፉ ወጣቶች እንዳሉ እናውቃለን›› ሲሉ በማዕከሉ ባልደረባ የኾኑ ሰው ለዋዜማ ዘጋቢ ገልጸውላታል፡፡ ‹‹….ብዙዎቹን የነቀዝ መድኃኒት ቸርቻሪዎች መድኃኒቱን ለወጣቶች መሸጥ እንዲያቆሙ መክረናል፣ ብቻውን ለሚመጣ አንድ ሰው መሸጥ ማቆም ይኖርባቸዋል›› ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተለምዶ ከአገሪቷ አጠቃላይ የገበሬ የእርሻ ምርት 20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው ሰብል በአጨዳ አልያም በስብሰባና ጎተራ ከገባም በኋላ በሚፈጠሩ የአያያዝ ችግሮች አማካኝነት ለብክነት እንደሚዳረግ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ የነቀዝ መድኃኒት ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ የነቀዝ ትል ጥድ ኮሶ ዋንዛ ዝግባና የመሳሰሉ እንጨቶችንና በተለይም እህል ዉስጥ ገብቶ ዉስጣቸውን በልቶ አመድ የማድረግ አቅም አለው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ጥንጣን በመባልም ይታወቃል፡፡ ብዙዉን ጊዜ ምርት ወደ ጎተራ ከገባ በኋላ ተሰብስቦ በማዳበሪያ ዉስጥ ሳለ መድኃኒቱ ይሰጣል፡፡ መንግሥት የምርት ብክነትን ለመቀነስ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መሐል የተሰበሰበ ምርት በተባይ እንዳይበላ አርሶ አደሮች የነቀዝ መከላከያ ጆንያ እንዲጠቀሙ ማበረታታት አንዱ ዘዴ ኾኖ ቆይቷል። 

አቤት የተሰኘው የአዲስ አበባ የቃጠሎ የድንገተኛ ህመምና የአደጋ ጊዜ ሆስፒታል የእንግሊዝኛ ምኅጻረ ቃል ሲሆን AaBET( Addis Ababa Burn Emergency Medicine and Trauma Hospital የሚለውን ስም አቅፎ የያዘ ነው፡፡  ማዕከሉ 250 አልጋዎች ሲኖሩት በአንድ ጊዜ 50 እስከ 60 ታማሚዎችን በድንገተኛ ደረጃ የማከም አቅም አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 12 አልጋዎች ያሉት የጽኑ ሕሙማን ማገገሚያ ልዩ ማዕከል ባለቤት ነው፡፡