ዋዜማ ራዲዮ- የትግራል ክልል ጊዜያዊ መንግስት በትግራይ ስለደረሰው ውድመት በዚህ ሳምንት ለተወሰኑ የመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ስጥቶ ነበር። ዋዜማ በትግርኛ የተሰጠውን መግለጫ ትርጉምና ጨመቅ እንደሚከተለው አቅርባለች።

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ጦርነቱ ካስከተለው ውድመት በላይ የጎረቤት ሀገር ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት እና ውድመት ማድረሳቸውን አብራርተው መግለጫውን የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አሉላ ሀብተአብ ናቸው፡፡

ጦርነቱ (መንግስት ሕግ ማስከበር ይለዋል) የፈጠረውን ሁኔታ ተከትሎ አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልግ ከጎረቤት ሀገር እና ከጎረቤት ክልል የመጣ ሰራዊት እንዳለ ኢንጅነሩ የገለፁ ሲሆን ይህ ሁኔታ እና ተግባር መንግስት ካካሄደው የህግ ማስከበር አላማ ውጭ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

እናም ሁኔታውን በመጠቀም ጦርነቱ ካስከተለው ውድመት በላይ ሌሎች አካላት ከባድ ውድመት ማድረሳቸውን ሃላፊው ገልፀዋል ፡፡

ለምሳሌ ከጎረቤት ሀገር የመጣ ሰራዊት (የሀገሩን ስም አልጠቀሱም) በትግራይ ክልል ላለፉት 30 አመታት የተገነቡ እስክ ውቅሮ ድረስ የሚገኙ ፋብሪካዎችን እና ሌሎች ተቋማት ማውደሙን የገለፁት ሃላፊው አድዋ የሚገኘው አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፣ የአዲግራት መድሃኒት ፋብሪካ እንዲሁም አዲግራትና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ ደረጃ መውደማቸውን አብራርተዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦችን በርካታ ንብረት መዘረፉን (ሲሚንቶ ፣ ብረት ፣ ማሽነሪዎቻቸው እና መኪኖቻቸው) እና ንብረቶቻቸው ወደ ተለያዩ አከባቢዎች መሄዱን ተናግረዋል፡፡

የኤርትራ ስራዊት በትግራዩ ጦርነት ተሳትፎ ማድረጉ በተደጋጋሚ ቢገለፅም የኤርትራ መንግስት ግን መረጃውን ሲያስተባብል ቆይቷል።

እነዚህ ተግባራት ጦርነቱን ተጠቅመው ሌሎች አካላት ያደረሱት ውድመት እንደሆነ የገለፁት ሃላፊው በሌላ መልኩ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሀገር መከላካያ ሰራዊት በጦርነቱ ያገኘሁት ንብረት በሚል ምክንያት በርካታ የትግራይ ክልል መንግስት ፣ የግለሰቦች እና የኢፈርት ንብረቶችን በቁጥጥር ማዋሉን አስረድተዋል፡፡

በጦርነት የተገኘ ንብረት ይወረሳል ብለው የሚያስቡ የሀገር መከላከል አባላት አሉ ፣ በትግራይ የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንጂ ጦርነት አይደለም እናም ንብረት መወረስ የለበትም ብለው የሚያስቡም አሉ ፤ እኛ እንደ ክልል መስተዳደር ግን ዘመቻው የህግ ማስከበር ተግባር በመሆኑ እና የሀገር መከላከያ እንደ ራሳችን አካል ስለምናየው የተወሰዱ ንብረቶች እንዲመለሱ በኮማንድ ፖስት በኩል ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን በመጠኑም ቢሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተለይ ለእርዳታ የሚያገለግሉ የትራንስ መኪኖች እየመለሰ እንደሚገኝ እና ለሰራዊቱ በጎ ተግባር እንደሚያመሰግኑን አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና አሁንም በርካታ የኢፈርት ፣ የትግራይ ክልል መንግስት እንዲሁም የግለሰቦች ንብረት መቃጠሉን ፣ በሀገር መከላከያ ስር እንዲገቡ መደረጉን ፣ ወደ ኤርትራ ፣ አማራ ክልል እና አዲስ አበባ እንዲሻገሩ መደረጉን ሀላፊው አክለው አብራርተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]