great-runዋዜማ ራዲዮ- መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው 16ኛው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ” በከፍተኛ የጸጥታ ተጠንቀቅ መካሄዱን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሩጫው ወደለየለት ተቃውሞ የመለውጥ አጋጣሚን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በሚል ከስምንት መቶ ያላነሱ የጸጥታ ኃይሎች የመሮጫ ትጥቅ ለብሰው እንዲሮጡ መደረጉን ታማኝ የቅርብ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይህ ቁጥር ከደኅንነት መሥሪያ ቤት የተመደቡትን እንደማይጨምርና ነጭ ለባሽ የፖሊስ አባላትን ብቻ ከግምት ያስገባ እንደሆነ የተናገሩ ምንጮች በኅቡዕ ከዋናው ደኅንነት መሥሪያ ቤት የተሳተፉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አልሸሸጉም፡፡ “የነዚህን ቁጥር ለማወቅ አዳጋች ነው፣ አንዱ ሌላውን ማወቅ ስለሌለበት አሰራሩም አይፈቅድም፣ ኾኖም በዚህን መሰል ዝግጅት ዉስጥ በርካታ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦችን መበተን የተለመደ ነው” ሲሉ ስለ ሁኔታው ያብራራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስና በፌዴራል ፖሊስ ልዩ ቅንጅት የተጠናከረ ጥበቃ የተደረገለት ይህ ዉድድር ለሦስት ሳምንታት ያህል ጥብቅ የጸጥታ ዝግጅት ሲደረግ እንደቆየና ኮማንድ ፖስቱ በሚመራው ዕዝ ሰፊ የደኅንነት ሥምሪት ቀደም ብሎ እንደተደረገ ተመልክቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመሩት የጸጥታ ካቢኔ ከሳምንታት በፊት ጠንካራ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ያመለከቱት እኒህ ምንጮች “ዉድድሩ መካሄድ አለበት ወይስ መሰረዝ ይኖርብናል?” በሚለው ላይ ምክክር እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምክክሩ ላይ ዉድድሩ በሰላም መካሄድ ከቻለ ከፍ ያለ አገራዊ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበታል፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት ዉድድሩ መካሄዱ በዓለማቀፍ ደረጃ የደበዘዘውን የአገሪቱን መልካም ገጽታ ወደነበረበት ለመመለስ በእጅጉ ይረዳል በሚል እምነት መግባባት ላይ መደረሱንና ከጠነከረ ጥበቃ ጋር ዉድድሩ እንዲካሄድ፣ ከዚህ ጎን ለጎን ሰፊና አለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ልዩ ጥረት እንዲደረግ መመሪያ ተላልፎ ሥራ መጀመሩን እነዚህ የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ቁጥራቸው በዉል ያልታወቁ የድርጅት አባላት በተለይም ወጣቶች ዉድድሩ ከሚካሄድበት ዕለት ቀደም ብሎና በዋዜማው ዕለት በዋና ዋና አደባባዮች የክትትል ሥራ እንዲያካሄዱ፣ አደባባዮች ሥር የተበተኑ የቅስቀሳ ወረቀቶች ካሉ እንዲያጸዱ፣ ድልድዮች ላይ የተቃውሞ ጽሑፎች በቀለም እንዲያስለቅቁ፣ የተለየ እንቅስቃሴ ካለ ፈጥነው ጥቆማ እንዲሰጡ በስፋት ተሰማርተው ነበር ተብሏል፡፡

ጎተራ ፔፕሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቀይ የራስ ጭንብል (ሄልሜት) የለበሱ የፌዴራል ፖሊስ ልዩ አባላት የያዟቸው የሬዲዮ መገናኛዎች ትዕይንቱን ተከታትለው መቅረጽ የሚያስችሉ ካሜራዎች የተገጠሙላቸው እንደነበሩና ይህም የሆነው ሁከት ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ካሉ ዉድድሩን ሳይረብሹ እነዚህን ወጣቶች ብቻ አድኖ ለመያዝ ታልሞ ዝግጅት በመደረጉ ምክንያት እንደነበረም ተመልክቷል፡፡

መስቀል አደባባይ ፊንፊኔ ሕንጻ፣ ሳር ቤት አዳምስ ፓቪሊዮን ሕንጻ፣ ሜክሲኮ ፌዴራል ፖሊስ ሕንጻ፣ ሜቴክ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ፣ ቄራ መስጊድ፣ ጎተራ ማሳለጫ ፔፕሲ ግቢ በርካታ የልዩ ኃይል አባላት በሕንጻዎቹ አናት ላይ በመሆን የተጠንቀቅ ጥበቃና ቅኝት እንዲያደርጉ መደረጉንም ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

መቻሬ ሜዳን የሚጎራበተው ጦር ኃይሎች ግቢ፣ ሜክሲኮ የሜቴክ ግቢ ዉስጥ፣ ቦሌ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት እና ሸራተን ፖሊስ ጋራዥ ግቢ ዉስጥ ችግር ቢከሰት ፈጥኖ የሚደርስ ልዩ ተጠባባቂ ኃይል እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ በተጠንቀቅ ላይ እንደነበረም እነዚሁ ምንጮች አብራርተዋል፡፡

ከቀድሞዎቹ የታላቁ ሩጫ ዉድድሮች በተለየ የዘንድሮው ዉድድር ምንም አይነት የተቃውሞ ድምጽ ሳይሰማበት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህም በመንግሥት በኩል ከፍተኛ እርካታን እንዳስገኘ ተመልክቷል፡፡ በርካታ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ በመምከራቸው የተነሳ ከፊል መነቃቃት አሳይቶ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ ተመልሶ ከፍተኛ ድብታ ዉስጥ መግባቱና ይህንንም ለመቀልበስ በመንግሥት በኩል ሰፊ ዘመቻ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር የሚጫወተው ሚና ጉልህ እንደሆነ ታምኖበት ነው የተገባው ተብሏል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቅርቃር ዉስጥ የገባችውን ኢትዮጵያ አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ዉስጥ አዋጁ እንደሚነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ፍንጭ የሰጡት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ነበር፡፡