Photo- Reuters

ዋዜማ- ለተከታታይ አምስት ዓመታት  ዝናብ በመስተጓጎሉ በተከሰተ አስከፊ ድርቅ  ከ 300 ሺሕ በላይ የቦረና ዞን ነዋሪዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚሁ ተፈናቃዮች ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡

በዞኑ ትልቁ ወደ ሆነው እና ከ 10 ሺሕ በላይ አባወራ ወይም ከ60 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ወደሚገኙበት ዱብሉቅ የተፈናቃዮች መጠለያ በማቅናት ዋዜማ ቅኝት አድርጋለች፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ በተደጋጋሚ ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን እና እስከአሁን ድረስ የተመዘገበ 71 የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መድረሱን የዱብሉቅ የተፈናቃዮች ጣቢያ ተጠሪ አወሉ ዋቆ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በባህል ተፅዕኖና ህፍረት ሳቢያ የጉዳቱ ሰለባ ሆነው ችግራቸውን ያልተናገሩ በርካታ ተጎጂዎች በመኖራቸው ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሆነ መገመት እንደሚቻል የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ነግረውናል። ወንጀለኞችን ለይቶ ለሕግ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚፈጸምባቸው አብዛኛዎቹ ሴቶች እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ እና ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

ችግሩን እጅግ ውስብስብ ያደረገው በመጠለያ ጣቢያው በሚገኙ ቤቶች ውስጥ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የማይተዋወቁ ሰዎች በመኝታ ሰዓት ጭምር በአንድ ላይ ስለሚተኙ ሴቶቹ ለጾታዊ ጥቃቱ ተጋላጭ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እና ላልተፈለገ እርግዝና ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን አውስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ጥቃቱ የደረሰባቸው ተለይተው የሚታወቁ ሴቶችን አካላዊ እና ስነልቦናዊ ክትትል  ማግኘት እንዲችሉ በአቅራቢያው ምንም አይነት የጤና ተቋም አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው አክለው እንደገለጹት አስገድዶ መድፈር  ብቻ ሳይሆን በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ተፈናቃዮች አብረው ከመኖራቸው የተነሳ ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉ ተግባራት ሲፈፀሙ መስተዋሉን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የሆነው ቀድሞም በአካባቢው እንደዚህ አይነት ተግባር በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ባሕል ይታይ ስለነበረ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥም ይህንኑ ተግባር ሊፈጽሙ መቻላቸው አውስተዋል፡፡

ይህንንም በማስመልከት ድርጊቱ ጎጂ እንደሆነ ለማስገንዘብ ከተፈናቃዮች ጋር ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ አዘጋጅተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ከጾታዊ ጥቃቱ በተጨማሪ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ(ሞዴስ) እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንደሌሉ የተናገሩ ሲሆን ተፈናቃዮቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ ስለንፅህና መጠበቂያ ማሰብ ቅንጦት ነው የሚሆነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በወር አበባ ጊዜ ለከፍተኛ ሰቀቀን እና ጭንቀት እንደሚዳረጉ ለማወቅ መቻሉን ኃላፊው አውስተዋል፡፡

ድርቁ በተከሰተበት እና ሰዎች ወደ መጠለያ ጣቢያው እየገቡ በነበረበት ወቅት በመንግሥት፣በረድኤት ድርጅቶች፣በግለሰቦች እና በሌሎች በጎ አድራጊ ተቋማት ሲደረግ የነበረው ድጋፍ መልካም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ ለዕለታዊ ፍጆታዎች የሚውሉ የምግብ ግብዓት፣ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ፣ እና ሌሎችም በበቂ ሁኔታ የነበሩ ቢሆንም  አሁን ድጋፉ መቀዛቀዙን ያስረዱት ኃላፊው በዚህም ምክንያት በተለይም በሴት ተፈናቃዮች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ አደጋ ስጋት መምሪያ ኃላፊ ሊበን ሳራ እንደተናገሩት በዞኑ ከ300 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ያስረዱ ሲሆን በርካቶቹ ኤልወያ እና ዱብሉቅ በተሰኙ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ከሁሉም በተለየ በዱብሉቅ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጸም ሪፖርቶች ይደርሱናል በማለት ገልፀዋል፡፡

ችግሩ በዋናነት የቤቶቹ ጥበት እና የማይተዋወቁ ስዎች ጭምር በአንድ ላይ መተኛታቸው እንደሆነ በመግለፅ ለዚህም ቤቶቹን አስፍቶ ለመስራት እና የመኝታ ቦታዎቻቸውን ለመለየት በመምሪያው በኩል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከጾታዊ ጥቃቱ በተጓዳኝ የሰብዓዊ ድጋፍ መቀዛቀዝ ተፈናቃዮችን ለረሀብ እና ረሃቡ ላስከተለው በሽታ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ሊበን  አብራርተዋል፡፡

አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶ አደር በመሆኑ እና ድርቁ ባስከተለው ረሀብ እንሰሳቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በማለቃቸው ወደመጡበት የመመለስ እና መልሶ የማቋቋሙን ስራ እጅግ ፈታኝ አድርጎታል፡፡  በዱቡሉቅ ወረዳ ብቻ ከ43 ሺሕ በላይ የቀንድ ከብቶች በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን ገልፀዋል፡፡

ለተፈናቃዮቹ መጠነኛ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው ጆፕ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንደነበር የገለጹ ሲሆን እሱም ቢሆን አሁን ላይ በአካባቢው ካለው የጸጥታ ስጋት አንጻር ድጋፉን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ካቆመ ሰንብቷል ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ እየተደረገላቸው ስለነበረው ድጋፍ ለዋዜማ ሲያስረዱ ለአንድ አባወራ የሚደርሰው ዱቄት ከአስር ጣሳ የማይበልጥ መሆኑን በመግለፅ ይህ ደግሞ ለሁለት ቀን የምግብ ፍጆታ እንኳን በቂ እንዳለሆነ አውስተዋል፡፡

ከትምህርት ጋር ተያይዞ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ካለው የትምህርት ቤት የመቀበል አቅም ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ በትምህርት ገበታ ላይ ያልሆኑ ልጆች በርካታ መሆናቸውን ወላጆች ገልጸዋል፡፡

 የዞኑ አስተዳደር እና አደጋ ስጋት መምሪያ ችግሩን ለመፍታት እና ተፈናቃዮቹ ከመጠለያ ጣቢያው ወጥተው ወደቤታቸው የሚመለሱበትን ሆኔታ ለመፍጠር አቅደው ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ [ዋዜማ]

ዋዜማ ይህን ዘገባ ያቀረበችው በኢንተርኒውስ  የገንዘብ ድጋፍ ታግዛ ነው