Ahmed Shide, Finance minster- FILE

ዋዜማ – ባልተለመደ ሁኔታ ለዚህኛው በጀት አመት እስካሁን ድረስ የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አላጸደቀም።

ለወትሮ በየአመቱ ጥር ወይም የካቲት ወር ላይ የፌዴሬል መንግስት ለአመቱ ከሚይዘው በጀት ላይ ተጨማሪ በጀትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያጸድቅ ነበር።  በዚህ አመት ግን የበጀት አመቱ ሶስተኛ ሩብ አመት ሊጠናቀቅ ቀናት ቀርተውት የገንዘብ ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀትን አለማቅረቡን ዋዜማ ከታማኝ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።

የፌዴራል መንግስት ለዚህ አመት 786.6 ቢሊየን ብር በጀትን ነው በአመቱ መጀመርያ ላይ ያጸቀው። ገንዘቡ ካለፈው አመት በጀት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት የሚይዘው ተጨማሪ በጀት በከፍተኛነቱ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ጠቅላላው የ2015 አ.ም በጀት ወደ አንድ ትሪሊየን ብር ይጠጋል የሚል ግምት ነበር። ሆኖም ለዚህ አመት ተጨማሪ በጀት መጽደቅ ከነበረበት የተለመደ ወቅት በእጅጉ ዘግይቷል። 

የባለፈው አመት ወይንም 2014 አ.ም መንግስት ይዞት ከነበረው 561.7 ቢሊየን ብር በተጨማሪ በዚያው አመት ጥር ወር ላይ በታሪክ ከፍተኛ የተባለ 122 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ማጸደቁ ይታወሳል። በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መጠገን ላልተለመደው የተጨማሪ በጀት ጭማሬ በወቅቱ በምክንያትነት መቅረቡ የሚታወስ ነው።

ዋዜማ በዚህ አመት ተጨማሪ በጀት እስካሁን ቀርቦ ያልጸደቀበትን ምክንያት ከምንጮቿ ጠይቃ ነበር። አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን “ለዚህ አመት ተጨማሪ በጀት ላያስፈልግ ይችላል ፣ ሆኖም በሂደት የሚታይ ይሆናል”  ብለውናል።  ምንጫችን ተጨማሪ በጀት ላያስፈልግ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ከመዘርዘር ተቆጥበዋል።

ሌላኛው የዋዜማ ምንጭ በበኩላቸው የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀትን ለዚህ አመት ከመያዝ ሊቆጠብ የሚችለው ለተከታታይ የብር ህትመት ላለመጋለጥ ከመፈለግ አኳያ ብቻ ነው እንጂ ተጨማሪ በጀቱ ሳያስፈልግ ቀርቶ አይደለም ብለውናል። 

ሰሞኑን የወጡ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነዶች እንደሚያሳዩት ማእከላዊ መንግስት በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ብቻ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ 100 ቢሊየን ብርን በቀጥታ ተበድሯል።(ከብሄራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር (Direct advance) ማለት የብር ህትመት መሆኑ የሚታወቅ ነው።) 

የፌዴራል መንግስት በዚህ በጀት አመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከብሄራዊ ባንክ በብር ህትመት የተበደረው ባለፈው አመት ሙሉውን ከማእከላዊ ባንኩ ከወሰደው 76 ቢሊየን ብር ብልጫን ያሳየ መሆኑንም ሪፖርቶችን በመጥቀስ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። 

ማእከላዊ መንግስቱ ለብር ህትመት የተጋለጠውም በዚህ አመት ያለበትን ከፍተኛ የበጀት ጉድለትን ለመሙላት እያደረገው ባለው ጥረት መሆኑን የገለጹልን ምንጫችን ለዚህ አመት ተይዞ ከነበረው 786.6 ቢሊየን ብር በጀት 300 ቢሊየን ብሩ የበጀት ጉድለት መሆኑን አስታውሰዋል። 

ኢትዮጵያ ባለፈችበት ግጭት ሳቢያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የብድርና እርዳታ በእጅጉ ተገልላ በመቆየቷ ፣ በአመት ውስጥ በሚሰበሰብ የተለያየ ገቢ ሊሞላ ያልቻለውን የበጀት ጉድለት የመሙያ ብቸኛ አማራጭ የፌዴራል መንግስት ከብሄራዊ  ባንክ የሚወስደውን ብድር ወይንም የብር ህትመትን አድርጎታልም ብለውናል። 

ሆኖም በዚህ መልኩ ከብሄራዊ ባንክ እየተወሰደ ያለ ብድርም የዋጋ ንረቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው በመምጣቱ ነው መንግስት ተጨማሪ በጀትን ከመያዝ ሊቆጠብ የሚችለው እንጂ ገንዘቡን የሚፈልጉ በርካታ መሰረተ ልማቶች እና የወጪ ጥያቄዎች መኖራቸው ግልጽ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽን ሲሰጡ አብዛኛዎቹ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ በየወከሏቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ግንባታ በጀት እና የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በበጀት መታጠፍ ምክንያት መቆማቸውን የተመለከተ ነበር።

ተጨማሪ በጀት በተለምዶ የፌዴራል መንግስት በበጀት አመት አጋማሽ ቀድሞ በተያዘ በጀት አለመብቃት ወይንም ተጨማሪ ወጪዎች በማስፈለጋቸው የሚያዝ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው አመት ክብረ ወሰን በሚባል ደረጃ አጋማሽ አመት ላይ 122 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል። የ2013 አ.ም ተጨማሪ በጀትም 26.4 ቢሊየን ብር እንደነበር ይታወሳል። [ዋዜማ]