በቀጣዩ ምርጫ ብዙ ዕጩ በማስመዝገብ ብልፅግና ቀዳሚው ነው። እሱን የሚከተሉት ዋና ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

Birtukan Midikssa, Photo -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወክሉናል ያሏቸውን 8209 እጩዎች ማስመዝገባቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ቦርዱ ለመገናኛ ብዙሃን እንዳስታወቀው በክልል እና በፌዴራል ምክር ቤቶች መቀመጫ ለመወዳደር በጠቅላላ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን እንዳስመዘገቡ ገልጿል ።

ብዙ እጩዎችን ያስመዘገበው የብልጽግና ፓርቲ ሲሆን 2432 ፤ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ ) 1385 ፤ እናት ፓርቲ 573 ሶስተኛ በመሆን እጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል።

አራተኛ ላይ የሚገኘው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 491 እጩዎች ሲያስመዘግብ 472 እጩዎች ይዞ በአምስተኛ ደረጃ የሚገኘው ደግሞ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ነው።

ይህ የእጩዎች ቁጥር በቀጣይ ቦርዱ በሚያደርገው ማጣራት ሊቀንስ ወይም በቦርዱ አሰራር መዘግየት ምክንያት ሳይመዘገቡ የቀሩ እጩዎች ካሉ ተጣርቶ ሲመዘገቡ ደግም የተጠቀሰው ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ዛሬ ሐሙስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት አስረድተዋል።

ብርቱካን ሚዴቅሳ እንደገለጹት የፖለቲካ ፓርቲዎች ካስመዘገቧቸው እጩዎች በተጨማሪ 125 በግላቸው ለመወዳደር እጩ ሆነው መቅረባቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን የእጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን አስመልክተው እንዳሉት ከሞላ ጎደል ምዝገባው ውጤታማ እንደነበር አንስተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ፓርቲዎች ያቀረቧቸው እጩዎች መታሰራቸውን እና ቦርዱ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመተባበር እንዳስፈታቸው ገልጸዋል። በሐረሪ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) ያስመዘገበው አንድ እጩው ከአመት በፊት ወንጀል ፈጽሟል በሚል መታሰሩንም ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል።

አንድ እጩ በምርጫ ለመወዳደር በምርጫ ቦርድ ከተመዘገበ በኋላ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ መከሰስ መብት እንዳለው ሰብሳቢዋ አስታውሰዋል ።

ሌላ በወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እጩ አድርገን ማቅረብ ተከለከልን የሚል ቅሬታ መኖሩን ያነሱት ወ/ሪት ብርቱካን በሕግ የተያዘ ጉዳይ ወደ ፊት የሚሆነውን መተንበይ ስለማይቻል የዜጎችን ድምጽ ከማባከን ያለፈ ፋይዳ የለውም ብለዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮዬ በገዢው ፓርቲ ተዘግቶብኛል ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ተዘጉብኝ ያላቸው ቢሮዎች አድራሻቸው የት እንደሆነ ቢጠየቅም ሊያቀርብ አልቻለም ሲሉ ወይዘሪት ብርቱካን ተናግረዋል።

ሌላው አፋር እና ሶማሌ የሚገናኙበት ገዳማይቱ ፤ አዳይቱ እና እንድፎ የተባሉ ቀበሌዎች በመልካምድር አቀማመጣቸው ምክንያት ሁለቱ ክልሎች የሚጋጩበት እና በየጊዜው የሰላም መደፍረስ የሚታይበት አካባቢ መሆኑ ይታወቃል ። ይሁን እንጂ በ2007 ዓ/ም በተካሄደው ምርጫ ከላይ የተጠቀሱት ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል ስር ስለነበሩ በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫም በነበሩበት እንደሚቀጥሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]