ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮ-ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አምሳሉ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

በዚህ የክስ መዝገብ የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኛው ወንድም የሆኑት አቶ ኢሳያስ ዳኘው 2 ኛ ክስ የቀረባባቸው ሲሆን ሌሎች ስምነት የቴሌኮሙ የቀድሞ ሀላፊዎችም ተካተዋል፡፡

በዚህም 1ኛ የቴሌኮም የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አምሳሉ፣ 2ኛ የኤን.ጂ.ፒ.ኦ የስራ አስፈፃሚ አማካሪ አቶ ወልደጊዮርጊስ ወልዱ፣ 3ኛ በኤንጂፒኦ የአፕሊኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣4ኛ የኔትዎርክ ኢንፍራስትራክቸር ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አብዱል ሀፊዝ አህመድ፣5ኛ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክትር አቶ ማስረሻ ጥላሁን፣6ኛ የኢንተርፕራይዝ ማኔጅመንት ፕሮጀክቶች ዳይሬክትር አቶ ሰይፈ ሀ/ስላሴ፣ 7ኛ የኦፕሬሽን ሰፖርት ኦፊሰር አቶ ፀጋዬ መኮንን፣ 8ኛ የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አይተንፍሱ ወርቁ ፣9ኛ የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ሲቪል ማስተባበርያ ቢሮ ሰራተኛ የነበሩት ጌታሁን ያሲን እና 10ኛ ላይ የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ሞባይል ፕሮግራም ሀላፊ የነበሩት አቶ ሳሙኤል ፈጠነ የተካተቱ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ስድስቱ እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ናቸው ፡፡

ከስድስቱ ውስጥ ሁለቱ ማለትም ወልደጊዮርጊስ እና ፀጋዬ በሌላ መዝገብ በተመሰረተባቸው ክስ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ የጋዜጣ ጥሪ የተደረገባቸው መሆናቸውን ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጉዳዩን ዛሬ ከሰዓት ለተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡

ከዚህ ቀደም የካቲት 12/2011 ዓም በተመሳይ ችሎት ከዩኒቨርሲቲ ኔትዎር ዝርጋታ ጋር በተገናኘ ከቻይናው ዜድ.ቲ.ኢ ከተባለ ኩባንያ ጋር በጥቅም በመመሳጠር 44.5 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት በቴሌኮሙ ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል የተከሰሱት አቶ ኢሳያስ ዳኛውና በዛው መዝገብ ተካተው የነበሩት አቶ አብዱልሀፊዝ በዛሬው እለት ጉዳያቸውን ለመከታተል ከሚቆዩበት የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

በስነ ስርዓት ህጉ መሰረትም ክስ የሚደርሰውም ሆነ የሚነበበው በችሎት ለተገኘ ተከሳሽ በመሆ9ኑ ከ18 ቀን በፊት በቁትጥር ስር ውለው የክስ መመስረቻ ጊዜ ተጠይቆባቸው የነበሩ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ የቆዩት 5ኛ እና 8ኛ ተከሰሽ ብቻ ክሳቸውን ተረክበው ተነቦላቸዋል፡፡

አቃቤ ህግም ባቀረበው የመጀመርያው ክስ ላይ ፡-

ተከሳሾች በ1996 ዓም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ)እና 407(1) (ሀ)(ለ) እንዲሁም (3)በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ብሏል፡፡

እንደ አቃቤ ህግ ገለፃ በ2002 ዓም ኢትዮ ቴሌኮም በሶማሌ ክልል በሚያደርገው የሞባል ማስፋፍያ ግንባታ ላይ ተከሳሾች ለራሳቸው ወይም ለብረታ ብረት እና ኢንጀነሪንግ ኮርፖሬሽን ጥቅም ለማስገነት በማሰብ ወንጀሉን እንደፈፀሙ አስረድቷል፡፡

የግዥ መመርያ ስለመጣሱ

የኢትዮ ቴሌኮም የግዥ መመርያ እና ፖሊሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት የግዠ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አንድ ግዥ በቀጥታ ከአንድ አቅራቢ ብቻ ሊገዛ የሚችለው ግልጋሎቱ አልያም እቃው ከዛ አቅራቢ ብቻ እንደሚገኝ በሰነድ ከተረጋገተ ብቻ ነው እንደሚል በክሱ ተገልፃል፡፡እንዲሁም ከ50ሺህ ብር በላይ የሆነ ግዥ በፍፁም በቀትታ ግዥ እንደማይፈፅም መደንገጉን አክሏል፡፡

በዚህ የኢትዮቴሌኮም ፕሮጀክት ላይም በወቅቱ የስራና ከተማ ልማት ሚኒስትር የነበረው ዋጋ እንዲያቀርብተጠይቆ ሚኒስትር መስርያ ቤቱ ኮንትራክተር ቀትሮ የሚያሰራበትን ዋጋ ማለትም 99 ሚሊዮን 909 ሺህ ብር ገደማ አስገብቶ ነበር፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ ግን 321,710, 421 ብር ላስገባው የብረታ ብረት እና ኢንጅነረንግ ኮርፖሬሽን ተከሳሾቹ እንዲሰጥ ስለመወሰናቸው ክሱ ያስረዳል፡፡

በዚህም በልዩነት 221.8 ሚሊዮን ብር ገደማ ጉዳት ቴሌኮሙ እንዲደርስበት አድርገዋል ሲል አብራርቷል፡፡

ስራው ያለ ኢትዮቴሌኮም ፍቃድ በዝቅተኛ ዋጋ ለንዑስ ተቋራጭ ስለመተላለፉ

አቃቤ ህግ በዝርዝር ባቀረበው ክስ ፕሮጀክቱን የተረከበው ብረታ ብረት እና ኢንጅነሪን የኢትዮ ቴሌኮምን የፅሁፍ ፍቃድ ካላገኘ በቀር ስራውን ለንዑስ ተቋጭ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል በገባው የውል ግዴታ ላይ በግልፅ ተቀምጦ እያለ ለሌላ ንኡስ ተቋራጭ በ44.3 ሚሊዮን ብር አሳልፎ መስጠቱ ተገፅዋል፡፡

በዚህም ኮርፖሬሽኑ 277.3 ሚሊዮን ብር ያልተገባ ጥቅም እንዲያገኝ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ያሉት ተከሰሾች አድርገዋል ብሏል አቃቤ ህግ፡፡

አቃቤ ህግ አክሎም የመጀመርያውን ውል 1ኛ ተከሳሽ 289.8 ሚሊዮን ብር ስለመፈራረማቸው፣ 2ኛ ጊዜ የተሸሻለውን ውል በ289.8 ሚሊየን ብር እና 3ኛውን የተሸሻለ ውል በ321.7 ሚሊዮን ብር አቶ ኢሳያስ መዋዋላቸውን እና ውሉ ለ4ኛ ጊዜ ሲሻሻል አቶ አይተንፍሱ በ322.6 ሚሊዮን ብር መዋዋላቸውን ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም አቃቤ ህግ የግንባታ እቃዎችን ለማጓጓዝ ከውል ውች ኢትዮ ቴሌኮም 397ሺ ብር እንዲከፍል አቶ አይተንፍሱ እንዳደረጉ አክሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የራሱን ስራ ራሱ እንዲቆጣጠር ስለመደረጉ

አቃቤ ህግ ሌላው በክሱ ያካተተው የፌደራል የግዥ መመርያ ከሚያዘው ውጭ ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰራውን የማስፋፍያ ስራ የሚቆጣጠር ማህንዲስ መቅጠር ሲገባው አልያም የራሱን ባለሞያ ቀጥሮ መቆጣጠር ሲገባው ተከሳሾቹ ይህንን የተቆጣጣሪ ምህንድስና ስራ ለራሱ ለብረታብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ደርበው በመስተት የጥቅም ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል የሚል ነው፡፡

በስተመጨረሻም ይርክክብ ሰነድ ሳቀርብና ስራዎቹ በአግባቡ ስለመሰራታቸው ቁጥጥር ሳይደረግ ለ51 ሳይቶች ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙን እንዲሁም ግንባታውን ለማስረከብ በውሉ ከተቀመጠው 5 አመታትን ዘግይቶ ሲቀርብ በማዘግየቱ ኮርፖሬሽኑ መቀጣት የነበረበትን ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ አካቷል ፡፡

እናም ተከሳሾቹ በጥቅሉ በቴሌኮሙ ላይ 295, 586, 120 ብር ጉዳት በማደርስ ከባድ የሙስና ወንጀል ሰርተዋል በማለት ክሱን አቅርቧለክ፡፡

በአማራጭም የይዘት ለውት ሳይኖረው የክሱን አንቀፅ ብቻ የመንግስትን ስራ በማያመች ሁኔታ መምራት በሚል አቃቤ ህግ 2ኛ ክስ አካቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]