ዋዜማ ራዲዮ- በሶማሌ ክልል በ2010 ዓም በደረሰው የ59 ሰው ሞት እና በርካታ ንብረት ውድመት ክስ ከተመሰረተባቸው 47 ሰዎች 28ቱ ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ነው፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥር 20 2011 ዓም በመሰረተው ክስ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 47 ግለሰቦች በክልሉ በተለያዩ ስብሰባዎች እና በፌስቡክ ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት አብያተ ክርስትያናት መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ከ 47ቱ እስካሁን በቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸውን በከፍተኛው ፍርድ ቤት እየተከታተሉ ያሉት አብዲ ሞሀመድን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ብቻ ናቸው፡፡

ዛሬ (ሕዳር 22, 2012) ጠዋት ደግሞ ይህንን ጉዳይ ከጅምሩ ጀምሮ ሲመረምር የነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ስርዓት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀል ችሎት ሲሰየም ፖሊስ ከላይ የተጠቀሰውን ተከሳሽ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በደብዳቤ የገለፀ ስለመሆኑ የግራ ዳኛዋ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም በችሎት ይዞት ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡

በክሱ 37ኛ ተከሳሽ ሆኖ የቀረበው አብዲ የሬ ጉራጬ ድጋሌ ከተባለ ከሌላ በቁጥጥር ስር ካልዋለ ተከሳሽ ጋር በመሆን ሀምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 06 አካባቢ ከሌሎች ከሄጎ አባሎች ጋር በመሆን ከሶማሌ ብሄር ተወላጆች ውጭ ያሉ የንግድ ቤቶች ላይ በያዙት ዱላ ፤ ብረት እና መዶሻ በርካታ የንግድ ቤቶችን ያወደሙ እና ንብረት የወሰዱ መሆኑን አቃቤ ህግ ቀድሞ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

በዛሬው ችሎት በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የጋዜጣ ጥሪ የተደረገላቸው 10 ተከሳሾች አለመቅረባቸው የተረጋገጠ በመሆኑ አቃቤ ህግ በሌሉበት ጉዳያቸው ይታይልኝ ሲል ጠይቋል፡፡

አክሎም ከድር አብዲ እና ኢብራሂም አደን የተባሉ ሁለት ተከሳሾችን ፖሊስ ፈልጎ ያጣና ከሀገር ስለመውጣታቸው ማረጋገጫ በማቅረቡ በእነዚህ ላይ ደግሞ በጋዜጣ እንዲጠሩ ይታዘዝልኝ ብሏል፡፡

በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተከሳሾችን በሚመለከት በተደጋጋሚ ቀጠሮ መሰጠቱን ተከትሎ ሌሎች በእዚህ መዝገብ ያሉ እስረኞች ጉዳይ እየተንጓተተ መሆኑ እና የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብትን የሚጋፋ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ በተከሳሾችም ሆነ በጠበቆቻቸው አቤቱታ ሲቀርብበት የነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ችሎቱ በቀጥታ የአቃቤህግን ምስክር ወደመስማት ለመሸጋገር ከጥር 14-22 ያለውን ጊዜ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ነገር ግን ከዛ በፊት ዛሬ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ የተገለፀው አብዲ የሬ ታህሳስ 9 ችሎት እንዲቀርብ እንዲሁም ከሀገር ወጥተዋል የተባሉት 2 ተከሳሾች ለታህሳስ 2 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]