Bekele Gerba
Bekele Gerba

ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሞን ተቃውሞ በመሪነት እያስተባበሩ አገርን አሽብረዋል ተብለው ወደ እሰር ቤት ዳግመኛ የተመለሱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች አመራሮች ከታሰሩ  ታህሳስ 14 ቀን 2009ዓ.ም (ዓርብ ዕለት) አንድ አመት አስቆጠሩ።

ለእስር ቤት መከራና ስቃይ አዲስ ያልሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በ2008ዓ.ም የቀደመው የእስር ቤት ህይወታቸው እንዴት እንደነበር ሲመልሱ “እስር ቤት ማንም ሊገባበት የማይመርጠው ቦታ ነው። እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ግን ሌላኛው ቤታችን ነው፤ ተማሪዎች ፣ወጣቶች፣ወንድሞች፣እህቶች፣ ልጆች፣አባቶች፣ ባሎች እንዲሁም ሚስቶች በእስር ቤት አሉ”ብለው ነበር።
አቶ በቀለ ገርባ በታህሳስ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ወደ ፌደራል ፖሊስ ምርመራ ማዕከል በልዮ ስሙ ማዕከላዊ በድጋሚ ለምርመራ ገብተው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕከላዊ በእስር የተገኙት ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ መምህር፣የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ የላዕላይ ኮሚቴ አባል እና የህዝብ ግንኙነት ዋና ሰው ሆነው በድንገት ሲታሰሩ ነበር።
በህዳር 2008ዓ.ም  ከዳር እስከዳር በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ አስተባብራቹሃል፣በተቃውሞ ተሳትፋቹሃል ተብለው ከመላው አገሪቱ ከተሰበሰቡ የኦሮሞ ወጣቶች ጋር በእሰር ዳግም የተገናኙት አቶ በቀለ በኢትዮጲያ የሚገኙ እስር ቤቶች “ኦሮምኛ ቋንቋ እንደሚናገሩ” ቀደም ብለው ከተናገሩት በይበልጥ ዳግመኛ እስራቸው ማረጋገጫ ሆኖላቸዋል።
ኢትዮጲያ ውስጥ ነገ በሚሆነው ነገር ላይ ማንም እርግጠኛ አይደለም። በማንኛውም ጊዜ መታሰር፣መደብደብ፣መገደል አሊያም ደብዛ መጥፋት አለ ሲሉ ከዳግም እስራቸው አስቀድመው የተናገሩት አቶ በቀለ ገርባ በአራት አመት የእስር ጊዜቸው ዋና ዋናዎቹን የኢትዮጵያ እስር ቤቶች አይተዋቸዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ግዙፍ ማስፋፊያ እቅዶችን ነድፎ የማስፋፋት ስራዎችን በመገባደድ ላይ በሚገኘው ዝዋይ እስር ቤት ውስጥ አመታትን አሳልፈዋል።
የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት አመት ከስድስት ወር በፊት በግንቦት 2006 ዓ.ም ለእስር የተዳረጉትን ኦሮሞ ተማሪዎች በአካል እስር ቤት የተገናኙት አቶ በቀለ እርሳቸው ወደ ቅሊንጦ በሚያመሩበት ወቅት ምንም እንኳን መንግስት ማስተር ፕላኑን ከእንግዲህ በተግባር ላይ አላውለውም ብሎ ቃል ቢገባም እነ አበበ ኡርጌሳ በዚሁ በተቀናጀ ማስተር ፕላን ሰበብ 15 አመታን በእስር እንዲያሳልፉ የከፍተኛው ፍርድ ቤት አዟል።
አመፅ አልባ የተቃውሞ አቀንቃኝ እንደሆኑ በተደጋጋሚ የሚናገሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ዋና ሰው አቶ በቀለ በቅሊንጦ እስር ቤት የሚደርስባቸውን አላግባብ የሆነ በደል እና መድሎ በመቃወም በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም ከአባሪዎቻቸው ጋር በአንድነት በመተባበር የርሃብ አድማ አድርገው ነበር።
ከሳምንት ለሚበልጡ ቀናት የርሃብ አድማ የመቱት በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ከርሃብ አድማቸው ተከትሎ በግንቦት ወር 2008 ፍርድቤት በአደራ እንዲቀመጡ ያዘዘው ቅሊንጦ የእስረኞች ማረፊያ ቤት ልብሶቻቸውን በሙሉ ነጥቆ ለቀናት ጨለማ ቤት እንዲቀመጡም አስገድዷቸውም ነበር።
በዚሁ ግንቦት ወር በቀለ ገርባ እና አባሪ ዎቻቸው በካናቴራ እና በቁምጣ እንዲሁም በባዶ እግር የከፍተኛው ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ችሎት ክሳቸውን ለመከታተል ተገደው ነበር።
በተደጋጋሚ ጨለማ ቤት ስለመታሰራቸው፣አላግባብ የሆነ መድሎ እና መገለል ከሌሎች እስረኞች በተለየ እንደሚደርስባቸው፣ቤተሰቦቻቸው እንዳይጠይቋቸው ስለመከልከላቸው፣በተለያዮ ህመሞች እየተሰቃዩ መሆኑን እና ህክምና እንደማያገኙ፣ጠበቆቻቸውን ለማግኝት እንደተቸገሩ፣ቤተሰብ ይዞላቸውን የሚመጣውን ምግብ እና መጠጥ እስር ቤቱ እንደከለከላቸው፣ ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለው እንደ ሳሙና እና የጥርስ ቡርሽ መግዛት እንዳልቻሉ እንዲሁም ከሌሎች እስረኞች በተለየ ተገለው ሰለመቀመጣቸው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ አቤት ቢሉም ምንም አይነት ምላሽ ሳያገኙ አንድ አመት አስቆጥረዋል።
በነሐሴም እነ በቀለ በእሳት ቃጠሎ ከመሞት ተርፈዋል። በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳድር ሰር የሚገኛው ቅሊንጦ የእስረኞች ማቆያ በእሳት ጋይቶ 23 ሰዎች ወዲያውኑ መሞታቸውን መንግስት ከቀናት በኋላ ቢናገርም በአደጋው መንግስት ከተናገረው በላይ የሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
ከእሳት አደጋው ተርፈው ለወራት በአደጋው ምክኒያት የፍርድ ቤት ክሳቸውን ሳይከታተሉ የቆዮት እነ በቀለ ገርባ በህዳር 12 ቀን 2009 ዓ.ም በታሰሩ በ አስራ አንድ ወራቸው የአቃቤ ህግ ምስክር መሰማት ተጀምሯል።
አቃቤ ሕግ ለ15 ቀን ምስክሮቹን በነበቀለ ገርባ ላይ እንዲያሰማ በተደጋጋሚ በፍርድ ቤቱ ዕድል ቢሰጠውም ሳይጠቀምበት ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቁ በድጋሚ ከታህሳስ 18 እስከ 20 ቀን 2009 ዓም ድረስ ምስክሮቹን ይዞ እንዲቀርብ ተፈቅዶለታል።
የነበቀለ ገርባ እስር ፓርቲያቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን ጭምር በእጅጉ የጎዳ ሆኗል። ይብሱንም ከፓርቲው አመራሮች ሳይታሰሩ የቆቱት ብቸኛ ሰው ዶ/ር መረራ ጉዲና “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል” በሚል ሰበብ መታሰራቸው ፓርቲውን አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።
የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባላትን ለማነጋገር ወደ ቤልጂየም ያቀኑት ዶ/ር መረራ ከብራሰልስ ቆይታቸው ታህሳስ 5 ቀን 2009 ወደ አገር ቤት ሲመለሱ የጠበቃቸው እስር ነበር። መንግሥት እርሳቸውን ለማሰሩ አስቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደምክንያት ቢጠቅስም አስከትሎ “ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋራ ተገናኝተዋል” የሚል ሰበብ አቅርቧል።
በብዙዎች ዘንድ የኦሮሞ ተቃውሞ የአደባባይ ምስል ተደርገው የሚቆጠሩት አቶ በቀለ ገርባ እና አብረዋቸው የተከሰሱት የፓርቲ አጋሮቻቸው ለእስር ከተዳረጉ ዛሬ ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓም አንድ ዓመት ሞላቸው። ከኦሮሞ ተቃውሞ ጋራ በተያያዘ የታሰሩት በሺህ የሚቆጠሩ የተቃውሞ ተሳታፊዎችና ተባባሪዎችም አብረዋቸው ዓመቱን ይቆጥራሉ።