Photo- from Openio Juris

በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች የሚከተሉት ይገኙበታል:-

ዋዜማ- በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በቀጠለው ግጭት እንዲሁም በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች “የይገባኛል ውጥረት በሰፈነበት ድባብ ውስጥ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ የይስሙላ ካልሆነ ምንም የረባ ውጤት አያመጣም፣ ለሀገሪቱ ችግርም መፍትሄ መሆን አይቻለውም” የሚል የሰላ ትችት ይቀርባል። ፖሊሲው ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ሁሉም ግጭቶች መቆምና ለሽግግር ፍትሕ አስቻይ መረጋጋት መስፈን አለበት።

ተጨማሪ ለማንበብ- የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ምን ይዟል?

ሌላው ትችት በትግራይ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር በፌደራል መንግስቱ የተሰየመና የስልጣን ጊዜውም የተገደበ በመሆኑ በትግራይ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪመሰረት የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ ሂደቱን ቅቡልና ፍትሐዊ አያደርገውም። 

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው በዋናነት እንዲያሳካ ታስቦ የነበረው ከትግራይ ጦርነት ጋር የተያያዙና አሁንም ድረስ በአማራና በኦሮምያ የተፈፀሙ ወንጀሎችን ቢሆንም፣ ፓሊሲው እመለከታቸዋለሁ ያላቸው ጉዳዮች ከህገመንግስቱ ከፀደቀበት 1987 ዓም ጀምሮ የተለጠጠ መሆኑብርቱ ትችት አስከትሏል።  የፖሊሲው ትግበራ ረጅም ዓመታት ወደኋላ መለጠጡ አንገብጋቢ የሆነውን የቅርብ ጊዜውን የፍትሕ ጥያቄ በመደፍጠጥና በማዘግየት ከሂደቱ የሚፈለገው ውጤት እንዳይገኝ ብሎም ፖሊሲው ወደተግባር እንዳይገባ እንቅፋት ይሆናል የሚል መከራከሪያም እየቀረበበት ነው። 

ሌላው የፖሊሲው ጉድለት ተብሎ የሚነሳው አጠቃላይ ቅኝቱ “ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት መፍጠር” ላይ ያተኮረ በመሆኑ “ተጠያቂነትን” ማስፈን እጅጉን ከባድ ብሎም የማይቻል እንዲሆን ያደርጋል የሚል ነው። መንግስት ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና የግጭት አዙሪትን ለማስቆም ይረዳል ቢልም ተቺዎች ግን በቅርብ ለተፈፀሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ወንጀሉን የፈፀሙ አካላት ተለይተው ሕግ ፊት የሚቀርቡበትና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ዕድል ወደ ጎን ተገፍቷል ይላሉ።

 በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየቶችን እናክልበታለን