Sheik Al Amoudi-PHOTO FILE
Sheik Al Amoudi-PHOTO FILE

ዋዜማ ራዲዮ-ከሳምንታት በፊት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከበርካታ የሳዑዲ አረቢያ ልዑላንና ባለስልጣናት ጋር በቅንጦት ሆቴል ውስጥ በቁም እስር ላይ የሚገኙት ሼክ መሀመድ አላሙዲ የሀብታቸውን የተወሰነውን ክፍል ለመንግስት በመስጠት ከእስር ለመለቀቅ እየሞከሩ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይናገራሉ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አላሙዲንና ሌሎች ባለሀብቶች ታስረው ባሉበት ካርል ሪትዝ ሆቴል በአካል በመገኘት ስለታሳሪዎቹ መረጃ ሲያሰባስቡ የነበሩ የዋዜማ ምንጮች አላሙዲ እጅግ በተዋበው የሆቴሉ የመመገቢያ ክፍል ከሁለት እንግዶች ጋር ተቀምጠው ሲያወጉና ሲመገቡ ተመክተዋቸዋል።
ታሳሪዎች እያንዳንዳቸው በሆቴሉ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ተደልድለው የሚኖሩ ሲሆን የተወሰነ የስልክ ግንኙነትና በተወሰኑ የሆቴሉ ክፍሎች መንቀሳቀስ ይፈቀድላቸዋል።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሳዑዲ መንግስት የፀረ ሙስና ኮሚቴና አቃቤ ህግ ተወካዮች ከታሳሪዎቹ ጋር በተጠረጠሩበት ወንጀል ዙሪያ ሰፊ የአንድ-ለአንድ ውይይት ሲያደርጉ ስንብተዋል።
አላሙዲም የሚጠየቁበት የህዝብ ገንዘብ መጠን ተነግሯቸው የሚጠየቁትን ገንዘብ ለመመለስና ከእስር ለመፈታት ድርድር ላይ መሆናቸውን ስምተናል።
ይሁንና ከፀረ ሙስና ኮሚቴው የቀረበው የገንዘብ መጠን እስከ ሰባ በመቶ የባለሀብቱን ገንዘብ መውረስን የሚያካትት በመሆኑ ጉዳዩ ያልተዋጠላቸው አላሙዲ በድርድሩ መቀጠላቸውን ጉዳዩን የሚከታተሉ ምንጮቻችን ነግረውናል።ሌሎች ታሳሪዎችም ተመሳሳይ ድርድር ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።
የሳዑዲ መንግስት ከፈቀደለት እንግዳ በስተቀር ጎብኚዎችን ማናገር ለታሳሪዎቹ አይፈቀድም።
የታሳሪዎቹ አያያዝ ላይ የመገናኛ ብዙሀን ያቀረቡት ዘገባ ስህተት ነው ብሎ ያመነው የሳዑዲ መንግስት የተወሰኑ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ተወካዮችን ዲፕሎማቶችንና ጋዜጠኞችን ጋብዞ ነበር።
ጉብኝቱ ከፍተኛ ቁጥጥር የተደረገበት ሲሆን የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ስለ እስረኞቹ “ደረጃውን የጠበቀ” አያያዝ ገለፃ አድርገዋል።
የባለሀብቶቹና የልዑላኑ መታሰር ከሙስና ይልቅ ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው በመሆኑ ታሳሪዎቹ በድርድሩ ተሳክቶላቸው ከእስር ለመውጣት ያላቸው ዕድል በሳዑዲ መንግስት እጅ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል። ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ያድምጡት

https://youtu.be/MCh8cjsiPaw