Oromo Student Protest at Haromaya University
Oromo Student Protest at Haromaya University

ዋዜማ ራዲዮ- የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት 16 ዓመት ዕድሜን አስቆጥሯል፡፡ ሐምሌ 16 ማለዳ በጣሊያን ኮሚኒት ትምህርት ቤት ባሕል አዳራሽ ምሑራንን በወቅቱ ጉዳይ ላይ ሊያወያይ ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ ርዕሰ ጉዳይ ያደረገው ‹‹በግጭቶች ወቅት የምሑራን ሚና›› ምን መምሰል ይገባዋል የሚል ቢኾንም ጥቂት ሐሳቦችን ብቻ አንስቶ ብዙ ምክር ለግሶ ብዙ የተባለለትን ዉይይት በአጭሩ አጠናቋል፡፡

ይህ ዉይይት ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ዋናው ምክንያት ሆኖ ሳለ በዕለቱ ጽሑፎቻቸው ያቀርባሉ የተባሉትም ሰዎች ስም ዝርዝርም ጉባዔውን በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር፡፡ኾኖም ብዙዎቹ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ለምሳሌ ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ኢታማዦር ሹም የአሁኑ የራያ ቢራ ሊቀመንበር አንዱ ነበሩ፡፡ አልተገኙም፡፡ በርሳቸው ምትክ የአሁኑ ኤታማዦር ሳሞራ ዩኑስ እህት ወይዘሮ ዘሚ ዩኑስ ተጋብዘዋል፡፡ እርሳቸውም የሰላምን አስፈላጊነት በመስበክ 15 ደቂቃዎችን ካጠፉ በኋላ በንግግራቸው ማሳረጊያ በሚጥል በሽታ የሚሰቃይ ልጃቸውን አንስተው የወቅቱን ሁኔታ በጥሩ ተምሳሌት ለመግለጽ ተጠቅመውበታል፡፡

‹‹ልጄ የሚጥል በሽታ አለበት፡፡ የሚወስደው መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቱ ብዙ መሆኑ አሳስቦኝ ሐኪሙን ጠየቅኩት፡፡ ምን ይሻላል አልኩት፡፡ ሐኪሙ ምርጫው ያንቺ ነው አለኝ፣ ከሕመሙ እንዲድን መድኃኒቱን መውሰድ አለበት›› አለኝ፡፡ አገራችንን ለማዳንም ሒደቱ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳትን ያስከትል ይሆናል፡፡ አገራችንን ለማዳን ምርጫው በእጃችን ነው፡፡ መድኃኒቱም እኛው ነን›› ሲሉ ሩብ ሰዓት የወሰደውን ዲስኩራቸውን አሳርገዋል፡፡

ዶክተር ፕሮፌሰር ፍሰሐፂየን መንግሥቱ የዓለም የእርቅና የሰላም ተቋም የቦርድ አባል ከመሆናቸውም ባሻገር የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የግብርና የገቢ ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የመድረኩ አጋፋሪም አርሳቸው ነበሩ፡፡ ድምጻቸውን ጎላ አድርገውና ደፈር ብለው በግልጽ ስለሚናገሩ እርሳቸው መነጋገሪያውን በጨበጡ ቁጥር የአዳራሹ ፀጥታ ይጎላ ነበር፡፡ መድረኩን የከፈቱት ተጋብዘው ያልተገኙትን ምሑራን በመውቀስ ነው፡፡

‹‹ ስለ አገር ጉዳይ፣ ስለ ሰላም መነጋገር ያስፈልጋል፣ ብዙ ምሁር ወዳጆች አሉኝ፤ ያደፈጡ ይመስለኛል፣ የልባቸውን ለመናገር ብዙ ድፍረት የላቸውም፡፡ እኔ 45 ዓመታት በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳትፌያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ብሶት ካለም በመንግሥት በኩልም መወያየት ያሻል ብዬ ነው ጠዋት አንድ ሰዓት የተገኘሁት፡፡ ብዙዎቹ ምሁራን በየጓዳው ማውራት ስለሚመርጡ እዚህ አይመጡም›› ሲሉ ተጋብዘው የቀሩ ምሁራንን ወረፍ አድርገዋቸዋል፡፡

አክለውም  “ብዙ ምሁራንን ጋብዤ ነበር፡፡ በሆነና ባልሆነው ምክንያት አልተገኙም፡፡ እንግዲህ ብዙ አይነት ምሁር አለ፣ አድርባይ ምሁር አለ፣ ታጋይ ምሁር አለ፣ እኔ አሁን በኃይለሥላሴ ዘመን የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ነበርኩ፣ አሁን ባልመስልም›› ብለው ታዳሚው ላይ ፈገግታን ከጫሩ በኋላ አቶ አያልነህ ሙላቱን ወደ መድረክ በመጋበዝ ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል፡፡

አቶ አያልነህ ረዘም ያለ ደቂቃዎችን የወሰዱት ‹‹አገር በቀል ዕውቀት በሌለበት፣ በምንም ዘርፍ ተምሳሌት የምናደርገው ዜጋ ባልተፈጠረበት ሁኔታ የኛ የምንለው ምሁር፣ ችግር ፈቺ ምሁር እንዴት ሊፈጠር ይችላል?›› በሚል ዙርያ ነበር፡፡ ‹‹ምዕራባዊ ምሑር ነው ያለን፣ ቱባውንና ነባሩን እውቀት ማዘመን አልቻልንም፣ አገራዊ ዉይይትን እንኳ በአገር ቋንቋ ለማድረግ ዝግጁ የሆነ ምሁር አጥተናል›› ሲሉም ተችተዋል፡፡

ከሰሞኑ እያንዣበበ ያለውን የርስበርስ ግጭት አስመልክቶ በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖርም በተምሳሌት አንድነትን ለመስበክ ሞክረዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ለኔ የአበባ መደብ ናት፡፡ ነጭ፣ ቢጫ፣ ቀይ፣ አረንጓዴ…ብዙ አበቦች ያሉበት መደብ፡፡ አበቦቹ ለብቻቸውም ዉብ ናቸው፣ አብረው ሲሆኑም ዉብ ናቸው›› ሲሉ በብሔር ቤሔረሰቦች ዉስጥ አንድነትና ልዩነት አብረው ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

በጽሑፋቸው ማጠቃለያም አገሪቷ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እየሰመጠች ባለች መርከብ መስለው አቅርበዋታል፡፡ ‹‹ ወይ ካፒቴኑን፣ ወይ ኮምፓሱን ማስተካከል፣ ወይ የባህር ሞገዱን ማስተካከል፣ ወይ የመርከቧን ችግር ፈልገን ማግኘት አለብን፡፡ ይህን ካላደረግን ሁላችንም እንሰምጣለን›› ሲሉ ጽሑፋቸውን ቋጭተዋል፡፡
ከአቶ አያልነህ በማስከትል የሕብረት ኢንሹራንስ መስራችና የቀድሞው የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚደንት መድረኩን ተረክበዋል፡፡

‹‹ለመወያየት መገናኘት ያስፈልጋል፣ አሁን በምሁራኑ የሚታየው ፍልስፍና ግን ዝም አይነቅዝም›› የሚለው ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን ‹‹አፍ ካልተናገሩበት እዳሪ ነው›› ብዬ ነው የማስበው፡፡ እዳሪ ማት ያልተዘራበት መሬት፣ ዋጋ የሌለው መሬት ማለት ነው›› ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት በምሁራን ላይ ከሰነዘሩ በኋላ ጠቅለል ያለ ምክር ወደመለገስ ገብተዋል፡፡

‹‹ ለችግሮች መፍትሄ፣ ለቅሬታዎች መልሱ ማፈን አይደለም፡፡ አቅም ያለው አቅመ ቢሱን ማጥቃት መልስ አይደለም፡፡ መልሱ ውይይት ነው›› ሲሉ ካስገነዘቡ በኋላ በብሔሮች መካከል ያለውን አንድነት ለማስገንዘብ ‹‹ ምላጭ ይዘን ክንዳችንን በጣ ብናደርገው የሚወጣው ደም ቀይ አይደለምን? ነጭ ደም የሚወጣው አለን?›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከርሳቸው በኋላ ተናጋሪ ሆነው የቀረቡት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ሲሆኑ 90ኛ ዓመታቸውን የደፈኑ በማይመስል ሁኔታ በታላቅ ቅልጥፍናና በሚገዛ ድምጽ ዘለግ ያለ ንግግራቸውን አቅርበዋል፡፡ በንጉሡ ጊዜ የትግራይ ግዛት አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ንግግራቸውን የጀመሩት ለጃንሆይ መልካም ልደትን በመመገኘት ነው፡፡ ‹‹እንዳጋጣሚ ሆኖ ዛሬ ሐምሌ 16 ነው፡፡ ንጉሡ 125ኛ ልደታቸው ነው፡፡›› በማለት ካበሰሩ በኋላ ንጉሡ ከዘር ይልቅ ለዕዉቀት፣ ለችሎታ ይሰጡት የነበረውን ቦታ ለማጉላት ሞክረዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ የአገር አንድነትን እንዲጠብቅ አበክረው ተናግረዋል፡፡

የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት ያዘጋጀው የፓናል ዉይይት የሰሞኑን ግጭቶች አስታኮ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን በሰላም ዙርያ የነበራቸውና ያላቸው ሚና›› በሚል ርዕስ ስለነበረ ጠንካራ ምሁራዊ ሙግቶች ይቀርባሉ ተብሎ በሰፊው ተገምቶ የነበረ ቢሆንም መድረኩ በብዙ አባታዊ ምክር ተሞልቶ ተጠናቋል፡፡

የዚህን የፓናል ዉይይት ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው ሌላው ጉዳይ የማኅበራዊ ሚዲያውን የተቃዋሚ ጎራ ከሚመሩት ፊታውራሪዎች አንዱ የሆነው ጃዋር መሐመድ የዚህን ዉይይት የጥሪ ካርድ በፌስቡክ ገጹ ላይ መለጠፉ ነበር፡፡ ይህ ተግባር በዝግጅቱ ላይ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም፡፡ ጃዋር ይህን ዉይይት በመላ አገሪቱ እየተቀጣጠለ ነው የሚለውን ሕዝባዊ አመጽ ለማብረድ ‹‹ወያኔ›› ስፖንሰር ያደረገውና የነደፈው እንደሆነ አድርጎ ነበር ያቀረበው፡፡ የሆነው ሆኖ የጃዋር ምልከታ በአዘጋጆቹና በተጋባዦች ላይ አንዳች አሉታዊ ስሜትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ለዚህም ይመስላል የመድረኩ መሪና የግብረሰናይ ድርጅቱ የቦርድ አባል ፕሮፌሰር ዶክተር ተስፋጺዮን ስማቸው በፌስቡክ እየተብጠለጠለ መሆኑን እንደተነገራቸውና እርሳቸው ግን አገር ወዳድ ዜጋ መሆናቸውን ለመናገር የተገደዱት፡፡ ‹‹ የወያኔ መሪዎች አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ስለተረበሹ የትግሬዎች ስብሰባ ፓናል ዲስከሽን እያዘጋጁ ነው ተብሎ ተወርቷል አሉኝ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እኔንም እንደ ወያኔ አድርገው ነው ያስቀመጡት፡፡ እኔ በሕይወቴ ዉስጥ ወያኔም አልነበርኩም፤ አደለሁምም፣›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡