ከአንድ ዓመት በፊት በሞያሌ ከተማ ለዘጠኝ ስዎች ሞትና ከስምንት ሺ በላይ ለሆኑት መፈናቀልና ወደ ኬንያ እንዲሰደዱ ሰበብ በሆነው ግጭት በግድያ የተጠረጠሩት የመከላከያ አባላት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

Gov Forces in Moyale – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓም ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ በሞያሌ ከተማ ልዩ ቦታው ሸዋ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጦር መሳሪያ በመታገዝ ከባድ የአካል ጉዳት እና ከባድ የሰው መግደል ወንጀል  መፈፀሙን ተከትሎ ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉ 6 የመከላከያ አባላት መታሰራቸው ይታወሳል፡፡


ወታደር ማትያስ ሞጉሬ፣ አስር አለቃ ሀብታሙ ተገኝ፣ኮ/ል አብርሃ አረጋይ፣ ወታደር አብዱልፈታህ ዱቦ፣አስር አለቃ ስለሺ ሽናሞ እና አስር አለቃ አስደናቂ ወረና የተባሉት 6 ተከሳሾች ታዲያ የካቲት 28 ቀን 2011 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ቢቀርቡም የፍርድ ቤቱ መደበኛ የስራ ሰዓት መገባደዱን እና የክሱን መስፋት ተከትሎ ሳይነበብ ቀርቷል፡፡


በዕለቱ ተከሳሾቹ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው እና ጠበቃ ለማቆም አቅም የሌላቸው በመሆኑ የተከላካይ ጠበቃ መንግስት እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም አቅማቸው እንደማይፈቅድ ለማረጋገጥ ቃላቸውን በመሀላ ወስዶ የተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ በዋስትናው ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለመጋቢት 5 ቀጥሮ ነበር፡፡

በቀጠሮው ቀን ክሱ ባይነበብም ችሎቱ የጠየቁትን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ምክንያት ያደረገው ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ የተጠቀሰው አንቀፅ በተለይ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 539(1)(ሀ) ዋስትናን የሚያስፈቅድ አለመሆኑ ነው፡፡


የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 539(1)(ሀ) “ማንም ሰው ሰውን ለመግደል አስቀድሞ የነበረው ሀሳብ፣ ወይም ምክንያት ፣ለመግደል የተጠቀመበት መሳርያ ወይም ዘዴ ፣ ያገዳደሉ ሁኔታ ወይም ግድያው የተፈፀመበት ቅጣትን የሚያከብድ ጠቅላላ ምክኒያት ሲታይ ገዳዩ በተለይ ጨካኝ ፣ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን በሚገልፅ ሁኔታ .. ሰውን የገደለ እንደሆነ እስከ ሞት ቅጣት በሚደርስ እንደሚቀጣ ይገልፃል፡፡  


ተከሳሾቹ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ እና አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ 15 ክሶችን የያዘ የክስ መዝገብ ነው የቀረበባቸው፡፡
በ1ኛ ተከሳሽ ወታደር ማትያስ ሞጉሬ የሚጠራው የክስ መዝገቡ የወንጅል ሕጉ አንቀጽ27(1)፣32(1)(ለ) እና 539 (1) (ሀ) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ እንደሆነ ይገልፃል፡፡


መጋቢት 01 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ በሞያሌ ከተማ ልዩ ቦታው ሸዋ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በክስ መዝገቡ የተጠቀሰው ተከሳሽ ኮ/ል አብርሃ አረጋይ “ማንኛውንም ጸጉረ ልውጥ ሰዎችን ተኩሱና እና ግድሉ” በማለት፣ ለ2ኛ ተከሳሽ አስር አለቃ ሀብታሙ ተገኝ፣ ለ4ኛ ተከሳሽ ወታደር አብዱልፈታህ ዱቦ ለ5ኛ ተከሳሽ አስር አለቃ ስለሺ ሽናሞ እና ለ6ኛ ተከሳሽ አስር አለቃ አስደናቂ ወረና ትዕዛዝ በመስጠት ተከሳሾች በተለያዩ ሰዎች ላይ በክላሽ ጠመንጃ ጥይት በመተኮስ የአካል ጉዳት እና የግድያ ወንጅል መፈፀማቸውንም ክሳቸው ያስረዳል፡፡


አቃቤ ህግም በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በሁለት የግድያ ሙከራና በአንድ ከባድ ግድያ፣ በሁለተኛ ተከሳሽ ላይ በ3 ከባድ ግድያ እና በ1 ከባድ የግድያ ሙከራ፣በሶስተኛ ተከሳሽ ላይ በ4 ከባድ የግድያ ሙከራ በ6 ከባድ ግድያዎች በ4 ተከሳሽ በአንድ ከባድ ግድያ በአንድ ከባድ ግድያ ሙከራ በ5 ተከሳሽ በ2 ከባድ የግድያ ሙከራና በ3 ከባድ ግድያ በ6ኛ ተከሳሽ ላይ በአንድ ከባድ የግድያ ሙከራና በአንድ ከባድ ግድያ ወንጀሉን ፈፅመዋል ሲል ነው አቃቤ ህግ ክሱን ያቀረበው፡፡


ከአንድ አመት በፊት በተፈፀመው በዚህ ወንጀል የቀረቡት እኚህ ተከሳሾች የመጀመርያዎቹን 9 ወራት ምርመራ እየተደረገባቸው በመከላከያ እስር ቤት ነው የቆዩት፡፡ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ግን ክስ ባይመሰረትባቸውም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል ፡፡


ወንጀሉ በተፈፀመበት ወቅት በሞያሌ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥ የነበረ ሲሆን ያንን ለማረጋጋት በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማዋ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሆኖም ግን በስህተት የመከላከያ አባላቱ የተኮሷው ጥይቶች ለ9 ሰዎች ህልፈተ ህይወት እና 13 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት መንስዔ እንደሆነ በወቅቱ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ገልፆ ነበር፡፡

ጥቃቱን አደረሱ የተባሉት የመከላከያ አባላት ትጥቅ እንዲፈቱ በአስቸኳይ ትዕዛዝ የተሰጠ እና በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም በወቅቱ ጥቃቱ ያስደነገጣቸው እና ግጭቱን የፈሩ ከ8, 000 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተሰደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የተከሳሾቹ ጉዳይ ለምን በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዳልታየ የተገለፀ ነገር የለም።[ዋዜማ ራዲዮ]