Eritrea and Sudan leaders
ሱዳን የኤርትራ ወዳጅ ሀገር ናት፣ ከኢትዮዽያ ጋር ያላት ግንኙነትም ጥሩ የሚባል ነው። ከኤርትራ ወታደሮች ተዋግቶና አምልጦ ወደ ድንበሯ የገባውን የሞላ አስገዶምን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ቡድን ያለምንም ማንገራገር ወደ ኢትዮዽያ እንዲሻገር ፈቅዳለች። ይህ ክስተት በሱዳንና በኤርትራ ግንኙነት ላይ ጥያቄ ያሚያጭር ሆኗል።

ሱዳን የኤርትራንም ሆነ የኢትዮጵያን ተቀዋሚ ሃይሎች በግዛቷ ማስጠለል ካቆመች በርካታ ዓመታት ያለፉ ሲሆን በተመሳሳይም ኤርትራና ኢትዮጵያም የሱዳንን ተቀዋሚ ሃይሎች መደገፍም ሆነ መጠለያ መስጠት ካቆሙ ቆይተዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት የሱዳንን እጅ ሲቆለምሙ የነበሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ የካርቱም ቤተኛ ሆነዋል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች ጠብ ለሱዳን ከሰማይ የወረደ መና ሊባል የሚችል ነው፡፡

የቻላቸው ታደሰ ዘገባ ዝርዝር አለው፣ አድምጡት

 

 

 

ባለፈው ቅዳሜ አንድ የሱዳን መንግስት የደህንነት ባለስልጣን ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የኮበለሉ ሽምቅ ተዋጊዎች ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በኤርትራዋ ኦምሃጀር ከተማ ላይ ከተዋጉ በኋላ ዓርብ ምሽት ሱዳንን ከኤርትራና ኢትዮጵያ ጋር በምታዋስነው የጠረፍ ከተማ ወደሆነችው “ሃምዳይት” መግባታቸውን መናገራቸውን “ሱዳን ትሪቡን” ጋዜጣ ዘግቦ ነበር፡፡ እኝሁ ባለስልጣን 683 ሽምቅ ተዋጊ ወታደሮች መሳሪያቸውን ለሱዳን ፀጥታ ሃይሎች እያስረከቡ እጅ መስጠታቸውን መናገራቸውንም ገልጿል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ የሱዳን ጦር በሁለቱ ሃይሎች መካከል ፍልሚያው እንዳይቀጥል በማድረግ ታጣቂዎቹ ወደ ከሰላ ግዛት እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ 

ይህ ክስተት የሶስቱን ሀገሮች ወቅታዊና መፃዒ ግንኙነቶችንና በክፍለ-አህጉሩ ያላቸውን አሰላለፍ እንደገና እንድናነሳው ያደርገናል፡፡

በእርግጥም ሱዳን ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ የኤርትራ መደበኛ ጦር ሰራዊት ወደ ግዛቷ ሊገባ ሞክሮ ከሆነ መመለሷ የሚጠበቅና ትክክለኛ እርምጃ ስለሆነ ጥያቄ ሊያስነሳ አይችልም፡፡ ሆኖም ግን ሱዳን ከኤርትራ ሰራዊት ጋር እየተዋጋ የሄደውንና የኢትዮጵያዊን መንግስት ነፍጥ አንስቶ ሲታገል የኖረውን ሽምቅ ተዋጊ ሃይል ከነሙሉ ትጥቁ ወደ ግዛቷ እንዲገባ እንደምን ልትፈቅድ ቻለች? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡

መቼም አንድን የውጭ ታጣቂ ሃይል ከነሙሉ ትጥቁ ተቀብሎ ወደሌላ ሀገር ማሳለፍ ጀሌዎችን ተቀብሎ ከማሳለፍ በእጅጉ እንደሚለይ አያጠራጥርም፡፡ የሱዳን እርምጃ ፍጥነት የሚያሳው ግን ኮብላዩ ሰራዊት ኤርትራ ላይ እንኳን ወንጀል ስላለፈጠሙ ለማረጋገጥ ጊዜ እንዳልሞከረች ነው፡፡

በእርግጥ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከሱዳን ጋር ካለው የፀጥታ ትብብር አንፃር ኮብላዮቹን አሳልፋ መስጠቷ እምብዛም አያስገርምም፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ ወንጀለኞችና የሽብር ተጠርጣሪዎች የሚሏቸውን ሁሉ አሳልፎ ለመስጠት ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ስምምነት በጣም ተጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሱዳንም ኮብላዩን የትህዴን ሊቀመንበርና ያስከተሏቸውን ታጣቂዎች ተቀብላ ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት ያሻገረችውም በዚሁ ስምምነት ሽፋን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጉዳዩንም ቀደም ብላ የተዘጋጀችበት ይመስላል፡፡

ከኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ግጭት ጀምሮ የሱዳንና ኢትዮጵያ ግንኙነት ተሻሽሏል፡፡ ኢትዮጵያም የዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንት ሃሰን አልበሽር ላይ ያወጠባቸው የእስር ማዘዣ በአፍሪካ ህብረት ውድቅ እንዲሆን በርትታ በመታገሏ ለሱዳን ከባድ ውለታ ውላላታለች፡፡ የሱዳን መሪዎችም ምንም እንኳን ለትንበያ የሚያመቹ ባይሆኑም ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ውዝግብ ስትገባ ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን አስመስክረዋል፡፡ ምናልባት ግድቡ የሱዳንን ጥቅም ጭምር የሚያስጠበቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ሚዛኗን ጠብቃ የኖረችው ሱዳን አሁን አሁን ከኤርትራ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር በበለጠ መወዳጀቱን እንደመረጠች ግልፅ ሆኗል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ከኤርትራ ምድር የተነሳውን መሳሪያ የታጠቀ ሃይል አስገብታ ሽፋን መስጠቷ የኤርትራን መንግስት ክፉኛ ማሳቆጣቱ አይቀርም፡፡ ሙሉ በሙሉ ማረጋገጥ ባይቻልም ትህዴን ከአስመራው መንግስት ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው የሚነገርለት ሲሆን እንደ ኢሳያስ መንግስት ልዩ ጠባቂ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታም አለ፡፡ ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ኩብለላው የሚሰጣቸው መግለጫዎች በዋናነት የኤርትራ መንግስት ላይ ያነጣጠሩት፡፡ ስለሆነም ኤርትራ እርምጃውን በኢትዮጵያ ላይ የምታካሂደውን የውክልና ጦርነት እንደማክሸፍ አድርጋ መውሰዷ አይቀርም፡፡ መቼም የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ከኤርትራ ቀጥተኛ ወረራ ይሰነዘርብኛል የሚል ስጋት አይኖርበትም፡፡ ይልቁንስ ዋነኛ ስጋቱ የሚነጨው መነሻቸውን ኤርትራ ካደረጉ ኢትዮጵያዊያን ሽምቅ ተዋጊዎች ይመስላል፡፡

የሱዳን ድርጊት ከኤርትራ ጋር በቀጥታ ሊያላትማት የሚችል ቢሆንም የኤርትራ መንግስት ከገባበት አጣብቂኝ አንፃር ግን ከሱዳን ጋር አተካራ ውስጥ መግባቷ ያጠራጥራል፡፡ ምናልባት በድርጊቱ ስለማኩረፏ ከሱዳን ጋር በሚስጥር ትነጋገር ይሆናል፡፡ ይፋዊ መግለጫ መስጠት ግን የኢትዮጵያን ታጣቂዎች ስለማስጠለሏና ስለመደገፏ በይፋ ማመን ስለሚሆንባት አታደርገውም፡፡ እስካሁንም የኤርትራ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ትንፍሽ ያላሉት ለዚያ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በእርግጥ “እንዳየኸው ተኩስህ ግደል” (shoot and kill) በሚል ፖሊሲዋ ከምትታወቀው ኤርትራ በየቀኑ በርካታ ወታደሮች ከነመሳሪያቸው እየከዱ ወደ ሱዳን ይገባሉ፡፡ ሱዳንም በስደተኝነት ስትቀበላቸው ኑራለች፡፡ ኢሳያስ ግን ሱዳን ድርጊቷን እንድታቆም ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ እንኳን የሌላ ሀገር ኮብላይ ሽምቅ ተዋጊዎችን እንዳታስገባ ሊያደርጉ ቀርቶ፡፡ በ1990ዎቹ የሱዳንን እጅ እንደፈለጉ ይቆለምሙ የነበሩት ሰውዬ አቅም እየከዳቸው መሆኑን ሱዳንም ተረድተዋለች፡፡

የሱዳንና ኤርትራ ግንኙነት ብዙ ሳንካዎች አሉበት፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ፣ ሱዳንና ኢራን ለበርካታ ዓመታት የሦስትዮሽ ግንኙነት መስርተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ሙጅሃዲኖች መሳሪያ የምታቀርበው በሱዳን በኩል እንደነበር የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ ከሱዳን ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች ለሚነሱት የጦር መሳሪያዎችም ኤርትራም መተላለፊያ ሆና እንዳገለገለች በሰፊው ይታመናል፡፡ ለዚህም ነበር እስራዔል በተደጋጋሚ የሱዳንን ጦር መሳሪያ ፋብሪካዎችና መሳሪያ የጫኑ የጦር ካሚዮኖች በአውሮፕላን የደበደበችው፡፡ 

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በየመን ቀውስ ላይ ሱዳን በሳዑዲ ዓረቢያ ከሚመራው ፀረ-ሁቲ ጥምር ሃይል ጎን ስትሰለፍ ኤርትራና ኢራን ግን የሁቲ አማፂያንን በመደገፍ መቀጠላቸው የኤርትራና ሱዳን ፖሊሲ ተቃራኒ ሁኗል፡፡ ያለተጠበቀው የሱዳን አቋምም ኤርትራን በአካባቢው እንድትነጠልና አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ ስለሆነም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር የሄዱት በየመን ላይ በያዙት አቋም ሳቢያ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከደቡብ ሱዳን መገንጠል ጀምሮ ኢኮኖሚዋ የደቀቀው ሱዳን ከጥምር ሃይሉ ጋር ተባባሪ በመሆኗ ቱጃሮቹ ሳዑዲና ኳታር መጠነ-ሰፊ የገንዘብ ዕርዳታ እያደረጉላት ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም ተባባሪነቷ ከአይዶሎጂ ይልቅ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምክንያት ሳይኖረው አይቀርም፡፡ የኢሳያስ መንግስት ግን ፕራግማቲስት ስላልሆነ እስካሁንም ከገባበት ከአጣብቂኙ አልወጣም፡፡

ሱዳን የኤርትራ አዋሳኝ ከሆኑትና ተቀማጭነታቸው አስመራ ከነበሩት የቤጃና ራሻይዲያ ህዝቦች ተቃዋሚዎች ከሱዳን መንግስት ጋር በማደራደር የስልጣን ተጋሪ ያደረጓቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ነበሩ፡፡ ተቀዋሚ ፖለቲከኞቹም የከሰላና ቀይ ባህር ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ሆነው በመሾማቸውም የኢሳያስ ቀኝ እጅና አንዳንዴም ነዳጅ ዘይትና የሌሎች የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ማስተላለፊያ ሆነዋቸው ቆይተዋል፡፡ ይህንን ስለታዘቡ ይመስላል ፕሬዝዳንት አል በሽር አምና ሁለቱን አስተዳዳሪዎች ከቦታቸው ሲያነሷቸው የድንበሩ ቁጥጥር በመጥበቁ ኤርትራን ክፉኛ ተጎጂ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ኢሳያስ ቁጥጥሩ እንዲላላ ቢጠይቁም አል በሽር ግን በውሳኒያቸው ፀኑ፡፡ በተጨማሪም ሱዳን ከብሉ ናይል፣ ደቡብ ኮርዶፋንና ዳርፉር ተቃዋሚዎች ጋር አጠቃላይ የፖለቲካ ስምምነት ለመድረስ እየጣረች ነው፡፡

በተጨማሪም ለሁለት አስርት ዓመታት የሱዳን ባላንጣ የነበሩት የዑጋንዳው ዮዌሪ ሙሴቪኒ ሰሞኑን በካርቱም ከአል በሽር ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሱዳንን ራስ ምታት ያስታግሳል፡፡ ሱዳንም የዑጋንዳ የጌታ ተከላካይ ሰራዊት እንደምትረዳ ክስ ሲቀርብባት ኖሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የአፍሪካ ህብረት አጣሪ ልዑክ ሱዳን ይህንን አረመኔ ድርጅት ስለመርዳቷ ለማጣራት ካርቱም ውስጥ ይገኛል፡፡

ኡጋንዳም ተቀማጭነቱን ካምፓላ የሱዳን አብዮታዊ ግንባር የተባለው የአማጢያን ጥምረትና ሌሎችንም የሱዳን ተቃዋሚዎችን እንደምትረዳና ከምዕራባዊያንና አፍሪካ ህብረት ጋር እንምታገናኝ በሱዳን ውንጀላ ይቀርብባታል፡፡ ሙሴቪኒ ከደቡብ ሱዳን ጋር ካላቸው ጥብቅ ትስስር አንጣር የጁባና ካርቱምን ቁርሶም ለመፍታት ዋነኛ ሰው ናቸው፡፡ የግንኙነቱ መሳሳል የደቡብ ሱዳን ነዳጅ መተላለፊያ እንደመሆነዋ መጠን ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡

የሱዳን ሁኔታ የመሻሻል ምልክት ሲያሳይ በአንፃሩ ደግሞ የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኤርትራ በሰው ልጆች ስብዕና ላይ የሚፈፀሙ አረመኔያዊ ወንጀሎችን ጨምሮ በርካታ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ባለፈው ሰኔ ወር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ጠቅላላ ሪፖርቱንም በመጭው ጥቅምት ወር ለተመድ ጠቅላላው ምክር ቤት ያቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ የአውሮፓ ህብረት ሊሰጣት ያሰበው ግዙፍ ሰብዓዊ ዕርዳታም የፖለቲካና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ሰለባ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ይህ ሁሉ በሯን ዘግታ ለኖረችው ኤርትራ መጥፎ ዜና ነው፡፡

ከኩብለላው በፊትም ሆነ በኋላ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በኤርትራ ላይ ውግዘት ማዥጎድጎዱን የዕለት ተለት ስራው ሆኗል፡፡ ሆኖም በፖሊሲ ደረጃ አስቀምጦ ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀምበታል እንጂ የአስመራውን መንግስት በሃይል የመገልበጥ ፍላጎትም አቅምም እንደሌለው መናገር አያዳግትም፡፡ ቢያስብም እንኳን የአስመራው መንግስት በማን መተካት እንዳለበት ግልፅ ፖሊሲም ሆነ አማራጭ ሃይል የለውም፡፡ ተቃዋሚዎችን በጊዮን ሆቴል እየሰበሰበ እንቶ ፈንቶ መግለጫዎች ከማስወጣት በስተቀር የውክልና ጦርነት ሲያካሂድ ወይም ተተኪ አማራጭ ተቃዋሚ ተግቶ ሲያደራጅ አይታይም፡፡ ይህን የማያደርገው ግን ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ጋር ስለሚጋጭበት አይደለም፡፡

ይልቁንስ እየተከተለ ያለው ፖሊሲ ሦስት ግቦችን መሰረት ያደረገ ይመስላል፡፡ አንደኛ በኢትዮጵያ ስደተኛ መጠለያዎችና በኤርትራ ውስጥ ያሉ ኤርትራዊያንን ከመንግስታቸው ነጥሎ እንደሚያያቸው መልዕክት በማስተላለፍ ለኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በጎ አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ሁለተኛ ኤርትራዊያኑ መንግስታቸውን በገንዘብም በዲፕሎማሲም መደገፍ እንዲያቆሙ መገፋፋት፤ ሦስተኛ በተለያዩ እርምጃዎች ቀስ በቀስ የኢሳያስን መንግስት በማዳከም ለኢህአዴግ-መራሹ መንግስት እንዲንበረከክ ማድረግ፡፡ መቼም ሁኔታዎች ሁሉ የሚያሳዩት አንዳኛው ሌላኛውን ለማዳከም እንጂ ሙሉ በሙሉ ከስልጣን ለማስወገድ አይመስልም፡፡

መቼም ኤርትራ ውስጣዊ ችግሮችም እንዳሉባት እሙን ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተዘጋጀ አንድ መድረክ በኤርትራ ዕጣ ፋንታ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት ኤርትራን በደንብ የሚያውቁት ታዋቂው ኖርዌያዊ ፕሮፌሰር ኬጅትል ቶሮኖቮል የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ከምንጊዜውም በላይ በደገኞችና ቆለኞች መካከል የሚቀሰቀስ የእርስ በርስ ጦርነት እንደሚያሰጋው ሲናገሩ የዚህ ሪፖርት አዘጋጅ በቦታው ተገኝቶ ሰምቷል፡፡ 

ቶርኖቮል እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸውን በመጠራጠራቸው ሰራዊቱ የራሳቸው ታማኝ በሆኑ የበታች መኮንኖች እንዲመራ አድረገዋል፡፡ በእርግጥ ከሁለት ዓመት በፊት የተወሰኑ ወታደሮች በአስመራ ከተማ ውስጥ የተወሰኑ የመንግስት ተቀዋማትን ለአጭር ጊዜ ቢከቡም ሙከራቸው ግን መፈንቅለ-መንግስት ይሁን አይሁን ሳይታወቅ ወዲያው እንደከሸፈ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል ኢሳያስ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ወታደራዊ አመፅ አጋጥሟቸው የማያውቀው፡፡

በጠቅላላው ሱዳን ዓለም ዓቀፋዊ ገፅታዋን ለማሻሻል ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር አዲስ አበባ ላይ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በተገኙበት የደቡብ ሱዳን ግጭት ስለሚፈታበት ሁኔታ ምክክር ሲደረግ ሱዳን መወከሏ የአሜሪካ አቋም መለሳለሱን ያሳያል፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮቿንም ለመፍታት ከበርካታ ተቃዋሚዎች ጋር አጠቃላይ ስምምነት ለመድረስ ደፋ ቀና በማለት ላይ ነች፡፡ እነዚህ እርምጃዎቿ የኤርትራ መንግስት መጠባበቂያ መጫወቻ  ካርድ እንዳይኖረው ያደርገው ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ክፍለ-አህጉራዊና ዓለማዓቀፋዊ አሰላለፉ በዚሁ ከቀጠለና ኤርትራም ውስጣዊ ችግሮቿን ካልፈታች መጭው ጊዜ ጥሩ አይሆንላትም፡፡ ክፍለ-አህጉራዊ መዳከሟ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት በመሳሪያ ለመጣል ከሚታገሉ ሃይሎች ጋር ያላትን ግንኙነት ይወስነዋል፡፡ ሱዳን ግን በአንፃራዊነት ወርቃማ ጊዜዋን እየጀመረች ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉት ክስተቶች የሚያጠናክሩትም ይህንኑ ነው፡፡