ዋዜማ ራዲዮ- በምስራቅ ወለጋ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሻንቡ ዞን ጃርቴ ወረዳ ዴቢስ በተባለ ቀበሌ 29 ሰዎች ” በኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዋዜማ ሬዲዮ ዛሬ ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ የጃርቴ ወረዳ የዴቢስ ቀበሌ ነዋሪዎች የአቢይ ጾም መያዣን ምክንያት በማድረግ ቤተክርስቲያን ተሰባስበው በነበረበት ወቅት “የኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ወደ ቤተክርስቲያኑ በመዝለቅ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳዳሪ ቄስ ወዲያውኑ እንደገደሏቸው እና 28 የሚሆኑትን ደግሞ ገርጂ ወደተባለ ጫካ ይዘዋቸው በመሄድ በጥይት ደብድበው ገድለዋቸዋል ብለዋል።

አስከሬናቸው በትናንትናው እለት ጫካ ውስጥ ተጥሎ መገኘቱን እና ዛሬ በዚያው በቀበሌያቸው የቀብር ሥነ ስርዓቱ መፈጸሙን የሟች ቤተሰቦች ለዋዜማ ተናግረዋል።

በእለቱ እለት የቀበሌው ሚሊሻዎች የወረዳው አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል የልዩ ሃይል ፖሊስ ጋር በመሆን በሌላ አካባቢ “የኦነግ ሸኔን ታጣቂዎችን” ለመምታት ዘመቻ በመሄዳቸው ምክኒያት በተፈጠረ ክፍተት መሆኑን የቀበሌው ነዋሪዎች ተናገረዋል።

የቀበሌውን ሚሊሻ እና የልዩ ሃይል አሰሳ በሚል መውጣታቸውን መረጃ የደረሰው “ኦነግ ሸኔ” ወደ ቀበሌው በመግባት ጥቃት ማድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀበሌው ህዝብ “የኦነግ ሼኔን ታጣቂዎች” በመፍራት ቄያቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች እና ወደ አጎራባች ወረዳዎች እየሸሹ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።

የኦሮምያ ክልል ፖሊስ ሰለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠን ጠይቀን እስካሁን ምላሽ አላገኘንም። [ዋዜማ ራዲዮ]