ዋዜማ ራዲዮ- በምስራቅ ወለጋ ሆሮጉድሩ ዞን ኢሙር ወረዳ ልዩ ቦታው ኢላሞ የተባለ አካባቢ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን አካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናገሩ፡፡


እሁድ አመሻሽ ላይ “የኦነግ ሸኔ” ናቸው ያሏቸው ታጣቂዎች ወደ አካባቢው መተው ተኩስ እንደከፈቱባቸው የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች በወቅቱ የመንግስት የፀጥታ አካላት በቦታው አልነበሩም ብለዋል። ታጣቂዎቹ አምስት ወንዶችና አራት ሴቶች በድምሩ ዘጠኝ ሰዋችን በጥይት እንደገደሉ ሌሎች ስድስት ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግረዋል።


ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ አራት ህፃናትን ከአካባቢው ይዘው ተሰውረዋል ፡፡ የሟቾቹ አስከሬን ትላንት ተነስቶ ስርዓተ ቀብራቸው መፈፀሙንም ስምተናል።


ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የአካባቢው ሚሊሻና ልዩ ሀይል ባለመኖሩ ለጥቃት ተጋልጠናል ባይ ናቸው።
መልክአ ምድሩ ሸለቆ እና ጫካ እንደሆነ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዋች ታጣቂዎቹ የመንግስት የፀጥታ አካላት በቦታው አለመኖራቸውንና ጨለማን ተገን አርገው በተደጋጋሚ ግድያና ዘረፋ እያደረሱብን ነው ሲሉ ተነገረዋል ፡፡


የኦሮሚያ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጠን ጠይቀን በጉዳዩ ላይ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ገልፆ ከሁለት ቀናት በኋላ መልሰን እንድንጠይቅ ነግሮናል። [ዋዜማ ራዲዮ]