ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ስድስት ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ ያስከተለው ረሃብ በበርካታ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር እያስከተለ ስለመሆኑ ዋዜማ ከእነዚሁ ወረዳዎች ያሰባሰበቻቸው መረጃዎች አመልክተዋል። 

የምሥራቅ ሐረርጌው ድርቅ ከተከሰተባቸው የዞኑ ወረዳዎች መካከል ጭናቅሰን፣ መልካ በሎ፣ ሚደጋ፣ ፈዲስ፣ መዩ ሙሉኬ እና ቁምቢ ይገኙበታል ። 

ግለሰቦች እና ማኅበራት ከሚያደርጉት ድጋፍ በዘለለ በመንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። 

 “እንኳን የዝናብ ዕጥረት ገጥሞት ቀድሞውንም አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የውኃ ዕጥረት ያለበት ነው” የሚሉት ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ነዋሪ ረጅም ርቀት በእግሩ በመሄድ ቢሲ ዲሞ ከሚባል ስፍራ የመጠጥ ውኃ እንደሚቀዳ ተናግረዋል። 

ጉዳቱ በሰዎች ላይ ብቻም ሳይሆን በእንሰሳትም ላይ  ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነና፣ አካባቢው ምንም ውኃ ባለመኖሩ ከብቶቻቸውን ወደ ባቢሌ በመንዳት ውኃ ለማጠጣት እንደተገደዱ ነዋሪዎች  ለዋዜማ ነግረዋታል።

 እነዚሁ ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ቀደም ብለው የነበሩት መንግሥታት አካባቢው ላይ በተደጋጋሚ ድርቅ ስለሚከሰት አስቀድመው የመከላከል እና ረሃብ ከተከሰተም በሰዎች እና እንሰሳት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዳይደርስ ሥራ ይሰሩ ነበር።  በዞኑ ጃርሶ እና አነኖ በተባሉ ስፍራዎች እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማም በተመሳሳይ ትልልቅ መጋዘኖችን በማዘጋጀት እና በእነዚህ መጋዘኖችም ስንዴ እና ዘይትን የመሳሳሉ የምግብ ግብዓቶችን ቀድሞ በማከማቸት የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ይደረግ እንደነበር የዐይን እማኝ ነን ሲሉ ነፅፅራቸውን በማስረጃ ያጣቅሳሉ። አሁን ግን ይህን መሰሉ የቅድመ-መከላከል ሥራዎች በመንግሥት በኩል እየተሰሩ ባለመሆናቸው ኅብረተሰቡ በከፍተኛ መጠን ለረሃብ መጋለጡን ይናገራሉ።

በዚህ ወቅት ያጋጠመው ድርቅ ያስከተለውን ረሃብ በመሸሽ፣ ነዋሪዎቹ በተለይም ወደ ሐረር ከተማና ወደ መሃል አገር በመፍለስ ላይ ይገኛሉ ያሉት ምንጮች፣ በተለይም አርብ ቀን በሐረር ከተማ ከእነዚህ አካባቢዎች መጥተው ጎዳናዎች ላይ የሚለምኑ የድርቁን ተጠቂዎች መመልከት የተለመደ ሆኗል ሲሉም የረሃቡን አስከፊነት ያስረዳሉ።

አስተያየት እንዲሰጥ የጋበዝነው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር የፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት ጥያቄያችንን ከሰማ በኋላ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

የተመድስጋትናትንበያ

 አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ግምት ወደ 126.5 ሚሊየን የሚያደርሰው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ)፣ በአገሪቷ ውስጥ አጠቃላይ የምግብ ዋስትና ዕጦት የሚያጋጥመው የሕዝብ ቁጥር በቀጣዮቹ ከሃምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ወደ ዐስር ሚሊየን እንደሚደርስ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል። 

ኦቻ፣ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት እንደጠቀሰው፣ እ.ኤ.አ. በያዝነው 2024፣ 4 ሚሊየን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና 7.2 ሚሊየን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ዕጦት ገጥሟቸው አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉትን ጨምሮ፣ 15.8 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ለረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ እና የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያትታል። 

   የምግብ ዕርዳታው አስፈላጊ በሆነባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች ላይ ላሉ 3.8 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በሚያዚያ ወር ላይ መድረሱን የኦቻ ሪፖርት ያስረዳል። ያም ሆኖ ግን የምግብ ዕርዳታው ከወር ወር ተመሳሳይ እንዳልነበረ የሚጠቅሰው ተቋሙ፣ የክልሎችን የምግብ ዕርዳታ ተቀባዮችን ቁጥር በተከታታይ ወራት ያሏቸውን ልዩነቶች ይጠቅሳል። 

በዚህም በኦሮሚያ የምግብ ዕርዳታው ተቀባዮች ቁጥር ሚያዚያ ላይ በመጋቢት ወር ከነበረው በሃምሳ በመቶ ሲቀንስ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሶማሌ ክልል ግን በተቃራኒው ዕድገት የታየበት መሆኑን ጠቅሷል። 

በትግራይ 2 ሚሊየን የሚሆኑት በቀደመው ወር ዕርዳታ ሲያገኙ፣ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ደግሞ የነበረው የምግብ ዕርዳታ ስርጭት በተከታታይ በ250 እና በ25 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዳስቀመጠው ግምት፣ በቀጣዩ መስከረም ወር አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልገው የሕዝብ ቁጥር ከዕርዳታ አቅርቦቱ በላይ በመሆኑ ሰፊ ሰብዓዊ ችግር አልያም እጅጉን የባሱ መዘዞች ሊከተሉ እንደሚችሉ ከወር በፊት ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ በኢትዮጵያ በሚያዝያ እና ግንቦት ወራት መጀመሪያ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ጉዳት እንደደረሰበት ባወጣው የቅርቡ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው፣ በሶማሌ ክልል የምግብ፣ ጤና፣ መጠለያ እና የመጠጥ ውኀ የሚፈልጉ 51,000 ዜጎች በዚሁ ጎርፍ ሲፈናቀሉ፤ በሲዳማ ክልል ደግሞ፣ እስከ ቀጣዩ ነሐሴ ሰብል ስብሰባ ወር ድረስ  ወደ 9,000 የሚሆኑ ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስጠንቅቋል።  

 ስለቀጣዮቹ ወራት ግምቶቹን የሚያስቀመጠው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በድርቅ፣ በግጭት እና በደካማ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አባባሽነት፣ ከያዝነው ሰኔ ወር አንስቶ እስከ ቀጣዩ መስከረም ወር ድረስ፣ ለሦስተኛ ጊዜ እና ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የምግብ ዕርዳታ ፍላጎቶች እንደሚኖሩ ተንብዩኣል። 

በዚኽኛው የአውሮፓውያን ዓመት አጋማሽ ላይ ጭምር በሰሜን፣ በማዕከላዊ እና በምዕራብ የአገሪቷ ክፍሎች የምግብ ዋስትና እያሽቆለቆለ እንደሚሄድም ተቋሙ በሪፖርቱ ጠቅሷል።  [ዋዜማ]