ዋዜማ ራዲዮ- በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 እና ህዳር 1 ቀን 2013 ዓም በተፈፀመው የግድያ ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ተጨማሪ 11 ቀን ለምርመራ ተፈቀደ፡፡
የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ (ሐሙስ) ረፋድ ላይ ከዚህ የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡


የፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በሁለት መዝገብ ከፍሎ ነው በችሎት ያቀረበው፡፡
ከዚህ ቀደም ለምርመራ በተሰጡት ቀናት የምስክርነት ቃል ስለመቀበሉ እና በ አካባቢው የወደመው ንብረት ላይ ማጣራት ስለማድረጉ የገለፀው ፖሊስ የአስክሬን ምርመራ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለማምጣት እና ሌሎች የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ 14 ቀናትለምርመራ እንዲፈቀዱለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡


ይሁን እንጂ ምርመራው ከተጀመረ ሶስት ወር ከ18 ቀናት እንደሆኑት ያስታወሱት የተከሳሾችቸ ጠበቆች ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ የተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊት በተናጠል ሳይለይ በጅምላ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ አግባብ ያለው የህግ ስራ አይደለም በማለት ተቃውመዋል፡፡


ሁሉም ተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፏቸው በግልፅ ተቀምጦ በማን ላይ ምን ያህል ምርመራ እንደቀረ በዝርዝር እየቀረበ ነው ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ ያለበት በማለት አክለዋል፡፡


ደምበኞቻቸውን ፖሊስ የተጠርጣሪነት ቃል ሳይሆን የምስክርነት ቃል ብቻ እንደተቀበላቸው የገለፁት ጠበቆች “ይህ የሚያሳየው በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ሳይሆን ወደፊት ምስክር የሚሆኑ ሰዎችን አስሮ ጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ መሆኑን ነው” ብለዋል፡፡


ከዚህ በተጨማሪም “ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ላይ በተደጋጋሚ ተጠርጣሪዎቹ ከህወሀት እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር ነው ወንጀሉን የፈፀሙት እያለ ቢገልፅም የታሰሩት ውስጥ ግን ህፃናት ልጆች የያዙ እናቶች እና ቄሶችም ጭምር ናቸው ያሉበት እና የተባለውን ድርጊት የሚፈፅሙ አይደሉም፤ በእርግጠኘኝነት የምርመራ መዝገቡ ቢታይም ያንን አያሳይም፡፡ ስለዚህ ችሎቱ መዝገቡን አስቀርቦ ይመርምርልን” ብለዋል፡፡
“ቄስ እና እናቶች ግብራቸው አይፈቅድም ቢባልም አብዛኞቹን ተጠርጣሪዎች ራሳቸው ተጎጂዎች የለይዋቸው ናቸው” ያለው ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪዎቹን የወንጀል ድርጊት የሚያሳዩ ማስረጃዎች እያጠናከረ መሆኑን አብራርቷል፡፡


አክሎም “ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ኮማ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች ነቅተው ማን በምን ጉዳት እንዳደረሰባቸው መናገር አለባቸው፡፡ የሞተው ሰው ምን ያህል እንደሆነም ደግሞ የሚታወቀው በሆስፒታል ምርመራ ስለሆነ ያ ውጤት እሰኪመጣ ተጨማሪ ቀን ያስፈልገኛል” ብሏል፡፡


የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ ፖሊስ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ በግልፅ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ተጨማሪ 11 ቀናትን ለምርመራ ፈቅዷል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]