ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል

[ዋዜማ ራዲዮ] በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ተሳትፈዋል ከተባሉት ውስጥ 8 ተከሳሾች ከህግ ውጪ የአማራ የስለላ እና ደህንነት ድርጅት(አስድ) በመገንባት የተለያየ ተልዕኮ ወስደው እንደነበር አቃቤ ህግ ገለፀ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሀኑ ፀጋዬ ከዚህ ቀደም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሰከሰኔ 15ቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ 68 ሰዎች ላይ ክስ መዘጋጀቱን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው 5 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ 17 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 20 የሚሆኑ ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱ ተገልፆ ነበር፡፡

ከተከሳሾቹ ውስጥም 13ቱ ዛሬ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓም (ዓርብ) ረፋድ ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍርድቤት ቀርበዋል፡፡

ጉዳያቸውንም ቀድሞ 4ኛ ወንጀል ችሎት የሚባለው እና የሽብር ጉዳዮችን የሚመለከተው በአዲሱ ስያሜው 1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገመንግስታዊ ስርዓት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ችሎት ተመልክቶታል፡፡

በክስ መዝገቡም የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን የግል አጃቢ የነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ አስጠራው ከበደ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አበበ ፈንታ፣ አስቻለው ወርቁ፣ ተሸመ መሰለ፣ አለምኔ ሙሉ፣ ከድር ሰኢድ፣ የለ አስማረ፣ አማረ ካሴ፣ ፋንታሁን ሞላ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ክርስቲያን ታደለ እና ሌላኛው የፓርቲ አባል በለጠ ካሳ የተካተቱ ተከሳሾች ናቸው፡፡

ሁሉም ተከሰሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በ1996 የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ 32/1/ሀ/ለ፣ 35፣38 እና 238/2/ ሰር የተቀመጠውን ተላልፈዋል በማለት ነው ክሱን ያቀረበው፡፡

በመዝገቡ የመጀመርያ ተከሳሽ የሆነው የጄነራል ሰዓረ መኮንን የግል አጃቢ የነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በመከላከያ ሰራዊት ታጅቦ የቀረበ ሲሆን ከችሎቱ ለሚቀርብለት አብዛኛውን ጥያቄ በፅሁፍ ከመመለስ ወይንም አዎ ከማለት በቀር ሌላ ማብባራሪያ ለመስጠት መናገር አቅቶት ነበር፡፡

አቃቤ ህግ ይህ ተከሳሽ ከብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙን የመግደል ተልዕኮ በሚያዝያ ወር ተሰጥቶት እንደነበር በክሱ ገልፅዋል፡፡

በተጨማሪም ምክትል ኢታማዦር ሹሙን ጄነራል ብርሀኑ ጁላን መግደል የሚችል ደፋር ሰው ሰው እንዲፈልግ የታዘዘ ሲሆን ለሁለተኛው ተልዕኮ የታጨው ሰው የአቃቤ ህግ 1ኛ ምስክር መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ሁለቱን የጦር መሪዎች በመግደል ሰራዊቱን ለመበተን ታቅዶ እንደነበርም የክሱ ዝርዝር ያስረዳል፡፡

አቃቤ ህግ ከ2ኛ እስከ 9ኛ ያሉት ተከሳሾች ማለትም አስጠራው ከበደ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አበበ ፈንታ፣ አስቻለው ወርቁ፣ ተሸመ መሰለ፣ አለምኔ ሙሉ፣ ከድር ሰኢድ እና ረዳት ሳጅን አየለ አስማረ ከህግ ውጭ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከአማራ ክልል መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ውጭ የአማራ የስለላ እና የደህንነት ድርጅት (አስድ) የሚል ተቋም መስረተዋል ሲል በክሱ ገልፀዋል፡፡

በዚህም ጠላት ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ህ.ወ.አ.ት እና ኦዴፓን ለማዳከም እና የሀይል እርምጃ ለመውሰድ የስለላ እና የመረጃ ደህንነት ስልጠና እንዲሁም የተግባር ልምምድ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት አክሏል፡፡

አቃቤ ህግ የተከሳሾቹን የወንጀል ተሳትፎም በተናጠል በክሱ ላይ ያብራራ ሲሆን ገሚሶቹ በፌስቡክ ገፅ ቅስቀሳ ሲፈጥሩ እንደነበር አብራርቷል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች በጠበቃ የተወከሉ ሲሆን ጠበቆች ለቀረበው ክስ የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሾ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ለችሎቱ ያስረዱ ሲሆን ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥም ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱ ማረምያ ቤት ለደህንነታቸው ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን መቃወምያቸውን የሚያቀርቡበት ደግሞ 18 ቀን ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]