Ahmed Shide- FILE
  • እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጓል

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ በተከሰተው የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ምክንያት የተጓተቱ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶችን ቀድሞ በተያዘላቸው የዋጋ ተመን ማጠናቀቅ የማይቻል በመሆኑ በመንግስት ወጪ የሚካሄዱ ግንባታዎች ላይ የዋጋ ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከክልሎች ሰምታለች፡፡

የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ የተደረገው፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣንና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የወቅቱን የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ንረት ካጠኑ በኋላ ነው፡፡ 

ትምህርት ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር በተላለፈለት የዋጋ ማስተካከያ መሰረት ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን፣ ዋዜማ በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ተፈርሞ ለዩኒቨርስቲዎች ከደረሰ ደብዳቤ ተመልክታለች፡፡

የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር ለገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረበው ዋጋ መስተካከያ ጥናት ከ2009 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ያለውን የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ሲሆን፣ ወካይ ግብዓት ተብለው የዋጋ ጥናት የቀረበባቸው ናፍጣ፣ ሲሚንቶ፣ ከውጭ የሚገቡ ሴራሚክሶች እና የብረት ዋጋ ነው፡፡ 

በግንባታ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ዋጋ ማስተካከያ የቀረበው የግንባታ ግብዓቶች ወካይ ዋጋ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ የናፍጣ ወካይ ዋጋ በ2009 ዓ.ም በሊትር 16 ብር የነበረው እስከ 2014 ዓ.ም 28 ብር፣ ሲሚንቶ በኩንታል በ2009 ዓ.ም 174 ብር የነበረው እስከ 2014 ዓ.ም 450 ብር፣ የአርማታ ብረት በኪሎ ግራም  በ2009 ዓ.ም 27 ብር የነበረው እስከ 2014 ዓ.ም 110 ብር እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ሴራሚክሶች 30 በ30 ሴንቲሜትር በ2009 ዓ.ም 250 ብር የነበረው እስከ 2014 ዓ.ም 493 ብር ነው፡፡ 

የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከገንዘብ ሚኒስቴር በደብዳቤ የተፈቀደላቸው ተቋማት ከላይ በተገለጸው ወካይ ዋጋ መሰረት በግንባታ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች ማስተካከያ ማድረግ እንደሚችሉ፣ በገንዘብ ሚኒስትሩ በአሕመድ ሺዴ ተፈርሞ ለትምህርት ሚኒስቴር ከደረሰው ደብዳቤ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ በክልል መንግሥታት እየተደረገ ሲሆን፣ ማስተካከያ ካደረጉ ክልሎች መካከል አማራ ክልል አንዱ ነው፡፡ ክልሉ ያደረገውን ዋጋ ማስተከከያ ዋዜማ የተመለከተች ሲሆን፣ የክልሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዋጋ መስተካከያ እስከ 30 በመቶ የሚደርሰ ነው፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ገንዘብ ቢሮ የዋጋ ንረት ማስተካከያው በ2012 በጀት ዓመት ከተጀመሩ የመንግሥት ግንባታዎች እስከ መጋቢት 2014 ድረስ ያሉትን ያካተተ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶች እንደየተጀመሩበት ጊዜ የዋጋ ማካካሻ እንዲደረግላቸው ይፈቅዳል፡፡

የክልሉ ግንዘብ ቢሮ ለሁሉም ዞኖች ያስተላለፈው ዋጋ ማስተካከያ ለህንፃ ግንባታ፣ ለመስኖ ግንባታ፣ ለድልድይ ግንባታ፣ ለመጠጥ ውሃ ግንባታና ለመሬት ስራ የተለያየ ነው፡፡ 

ከሰኔ 2012 ዓ.ም በፊት ውል የተፈጸመላቸው ፕሮጀክቶች ለህንጻ 30 በመቶ፣ ለመስኖ፣ ለድልድይና ለመጠጥ ውሃ 26 በመቶ፣ ለመሬት ስራ 11 በመቶ ሲሆን፣ ከሀምሌ 1/2012 ዓ.ም እስክ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም ለተፈጸሙ የፕሮጀክት ውሎች ለህንፃ 21 በመቶ፣ ለድልድይ 18 በመቶ፣ ለመሬት 6 በመቶ፣ ለመስኖና ለመጠጥ ውሃ ግንባታዎች 15 በመቶ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

እንዲሁም ከሀምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም ውል ለተፈጸመባቸው ግንባታዎች ለህንጻ 10 በመቶ፣ ለመስኖ 11 በመቶ፣ ለድልድይ 12 በመቶ፣ ለመጠጥ ውሃ 10 በመቶና ለመሬት ስራ የሁለት በመቶ ዋጋ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ክልሉ መወሰኑን ዋዜማ ተመልክታለች፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]