የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በሦሰት ዐበይት ጉዳዮች ጥልቀት ያለው ውይይት አድርጎ የመፍትሄ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ለዋዜማ ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡

EOC Synod -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በ24/12/2011 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን በሚል እነ ቀሲስ በላይ መኮንን የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ሥርዓት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ “ሕገወጥ” ነው ብላ ማወጇ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥትም ሆነ ምእመናን ይሄን እንቅስቃሴ እንዲያወግዙት በመግለጫው ተጠይቆ ነበር። በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም። በምዕመናን በኩል ግን ከፍተኛ ተቃውሞና ስጋት እየተሰማ ነው። ጉዳዩ በብልሀት መያዝ እንዳለበት የሚመክሩም አሉ። በተለይ ጉዳዩን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ ለመጠቀም የሚደረገው ሙከራ የቤተክርስቲያኒቷን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። የሐሙሱ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ (ስብሰባ) ይዘት በተመለከተ የዋዜማ ዘጋቢ ረቡዕ ማምሻውን ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡


አሁን ቤተ ክርስቲያን የገጠሟት ብዙ ወቅታዊ ችግሮች አሉ፡፡ ይኹንና ለሕዝቡ የማይጠቅም፣ ዘላቂነት የሌለው መሆኑን ቤተ ክርስቲያን አምናበት በቋሚ ስኖዶስ በኩል መግለጫ ብትሰጥም ከመንግሥት በኩል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም ብለዋል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፡፡ ነገር ግን መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደነበረበትና አሁንም ቢሆን መንግሥት ከቤተ ክርስያኗ ጎን እንዲቆም ትፈልጋለች ብለዋል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፡፡ ምክንያቱም አሉ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ በሆነው ነገር ብፁዓን አበው ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡንና ምእመናኑን አስቆጥቷል፡፡ ጉዳዩ በአጠቃላይ ሰሞኑን መነጋገሪያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ነገሩ እንዳይሰፋና ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ መንግሥት ጉዳዩን ዐይቶና ተገንዝቦ ማለት ያለበትን እንዲል ቤተ ክርስቲያኗ አሁንም ታሳስባለች ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም (ሐሙስ) የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በሦሰት ዐበይት ጉዳዮች ጥልቀት ያለው ውይይት አድርጎ የመፍትሄ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ለዋዜማ ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡


በመጀመሪያ የሚያየው አጀንዳ ሕዝቡንና ቤተ ክርስቲያናን የመጠበቅ ሓላፊነት ስላለበት ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተዋል ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እንዳሉት መግለጫውን የሰጡት አካላት ጉዳዩ የማይመለከታቸው ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አይወክልም፡፡ ምክንያቱም መግለጫ ሰጭዎች የራሳቸውን አሳብ ይዘው ነው የተነሡት፡፡ አሳቡ በራሱ የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅር የሚጻረር ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን እስከወዲያኛው እንደማትደግፋቸው አበክረው ተናግረዋል፡፡


ሁለተኛው አጀንዳ ቤተ ክርስቲያኗ በቀጣይ ከመንግሥት ጋር እንዴት መቀጠል እንዳለባት ቅዱስ ሲኖዶስ ይወያያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች መንግሥት በቀጣይ በምን አግባብ መመለስ እንዳለበት እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን በኩል ደግሞ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ካሉ ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚወያይባቸው ተገልጿል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ አያይዘውም መንግሥት በልዩ ልዩ ችግሮች የተወጠረ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን ትረዳለች ብለዋል፡፡


በሦስተኛ ደረጃ ቅዱስ ሲኖዶስ ይወያይበታል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ የቅርብ ጊዜውን ጨምሮ በልዩ ልዩ ጊዚያት አብያተ ክርስቲያናት ይቃጠላሉ፣ ምእመናን ይሰደዳሉ፣ ካህናት ይገደላሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ቅዱስ ሲኖዶስ በስፋትና በዝረዝር ከተወያየ በኋላ የመፍትሄ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን፣ ቋንቋና እውቀትን የሰጠች እናት ብትሆንም ዛሬ ዛሬ ግን በየጊዜው በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚኖሩ ምእመናኖቿ በፍርሃት እየኖሩ፣ በየጊዜው የአምልኮ ቦታቸው እየተቃጠለ፣ ምእመናኑ እየተሰደዱ እንዲሁም ሕፃናት ለችግር እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፡፡
ዝርዝር ዘገባ ይዘን እንመለሳለን