FILE

ዋዜማ- መንግስት በስጋ ላኪዎች የስራ ዘርፍ እየተባባሰ የመጣውን የውጪ  ምንዛሪ ስወራ ማስቆም ስላልቻለ ስጋ ወደ ውጪ ሀገር እንደማይልኩ አስታወቁ። 

በውስጡ አስር ዋና ስጋ አምራችና ላኪ ኩባንያዎችን የያዘው ፣የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ለግብርና ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ መንግስት የዘርፉን ችግር እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦለት ስላልፈታ ፣ የስጋ አምራችና ላኪ ኩባንያዎች ከዛሬ መጋቢት 28 ቀን 2015 አ.ም ጀምሮ ምርቱን ወደ ውጭ መላክ እንደሚያቆሙ ገልጿል።

ዋዜማ የተመለከተችውና ለግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ፣ የስጋ አምራቾች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ላለመላክ ከውሳኔ የደረሱት የኤክስፖርት ቄራዎችን ተከራይተው ምርቱን የሚልኩ ኩባንያዎች ዘርፉን ለውጪ  ምንዛሪ ስወራ እየተጠቀሙበት በመሆኑና ህግ አክብረው የሚሰሩት እየከሰሩና ከገበያ እየተገፉ በመሆኑ ነው። 

መንግስት የኤክስፖርት ቄራን ተከራይተው ስጋን የሚልኩ ኩባንያዎች እሴትን እየፈጠሩ ካለመሆኑ በላይ ለወጪ ንግድ የጨመሩት ነገር የለም በሚል ከዚህ በፊት እገዳ አድርጎባቸው እንደነበረ የገለጸው ደብዳቤው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኤክስፖርት ቄራን ተከራይተው ስጋን የሚልኩ ኩባንያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እንደገና መፈቀዱ ዘርፉን ለውስብስብ ችግር ዳርጎታል።

ለግብርና ሚኒስትሩ ሰኞ መጋቢት  25 ቀን 2015 አ.ም ከማህበሩ ተጽፎ የገባው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ፣ የኤክስፖርት ቄራን ተከራይተው ስጋን ለመላክ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ዋና አላማ ሀገሪቱ ከስጋ ምርት የምታገኘው ገቢ ሳይሆን ለራሳቸው የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እና ባንኮች ለምርት ላኪዎች የሚሰጡትን ብድር ለመውሰድ ብቻ መሆኑን ይጠቅሳል።

ባለው የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም መመሪያ መሰረት ምርት ላኪዎች ካመጡት የውጭ ምንዛሬ የተወሰነውን የፈለጉትን ምርት ለማምጣት እንዲጠቀሙበት ይፈቅዳል። የኤክስፖርት ቄራን ተከራይተው የሚሰሩ ኩባንያዎችም ፍላጎታቸው የውጪ ምንዛሪ እጃቸው ማስገባትና ለሌላ የንግድ ወይም የግል ጉዳይ ማዋል በመሆኑ፣ ለእርድ የሚሆኑ እንሰሳትን በውድ ዋጋ በመግዛት ስጋውን እየከሰሩ ለውጭ ገበያ እንደሚሸጡ ተገልጿል።

የኤክስፖርት ቄራ ተከራይተው የሚሰሩት ኩባንያዎች ሁሌም ተመሳሳይ አለመሆናቸው እና የውጭ ምንዛሬ ሲፈልጉ ብቻ የላኪነት ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ መሆናቸውን ማህበሩ ያስረዳል። የሚልጉትን የውጭ ምንዛሬ ሲያገኙም ከዘርፉ ይወጣሉ። በዚህ መልኩ የሚሰሩ ኩባንያዎች ቁጥራቸው ከ30 እስከ 40 እንደሚሆኑም ሰምተናል። 

የኢትዮጵያ ስጋ አምራች ላኪዎች ማህበር ለግብርና ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ፣ ላለፉት አራት ወራት ለሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግስት ተቋማት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ባለማግኘቱ ፣ምላሽ እስኪገኝም ድረስ በማህበሩ የታቀፉ ላኪዎች ከዛሬ ሀሙስ መጋቢት 28 ቀን 2015 አ.ም ጀምሮ ምርት መላክ እንደሚያቆሙ ገልጿል። 

ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ወደ ውጭ ከተላከ ስጋ ክብረ ወሰን በሆነ ሁኔታ 120 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች።

updated

የስጋ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ አቁመናል ያሉ ስጋ ላኪ ኩባንያዎች ዛሬ መጋቢት 28 ወደ ሥራ መመለሳቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ስጋ ላኪዎች እንደገና ስጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩት፣ ግብርና ሚንስቴር ዘርፉ የገጠመውን ችግር እንደሚፈታ ቃል መግባቱን ተከትሎ ነው። የኢትዮጵያ ስጋ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር መጋቢት 25 ቀን ለሚንስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ የኤክስፖርት ቄራ ተከራይተው ስጋ ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች በሚፈጽሙት ያልተገባ የገበያ ውድድር ሳቢያ በማኅበሩ የታቀፉ ስጋ ላኪ ኩባንያዎች ከገበያ እየወጡ ስለመኾኑ ቅሬታቸውን አቅርበው ነበር። ይህንኑ ተከትሎ፣ ሚንስቴሩ በችግሩ ዙሪያ ከስጋ ላኪዎች ጋር ለመወያየት ለመጭው ሰኞ ቀጠሮ እንደያዘ ዋዜማ ተረድታለች።

[ዋዜማ]