Capital outflow(ዋዜማ ራዲዮ)- በህገወጥ መንገድ ከሀገር ገንዘብ የመሸሽ ወንጀል በእጅጉ እየተባባሰ መምጣቱን የኢትዮዽያ መንግስት ሳይቀር በይፋ እየገለፀ ይገኛል። ለመሆኑ የገንዘብ ማሸሽ ውንብድናው የሚፈፀመው እንዴት ነው?  ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች።

 

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚከታለው “ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ” (GFI)፤ እንደ አውሮፓአቆጣጠር ከ2004-2013 በተለያየ መንገድ 26 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ ወጥቷል ይለናል፡፡ ይህ የGIF መረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ከIMF እና ዓለም ባንክ የተገኘ ነው፡፡ በ2ዐ14 “ትራንስፐረንሲ ኢንተርናሽናል” የሙስና ደረጃ ጥናት ካደረገባቸው 175 ሀገራትኢትዮጵያ 11ዐኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በ2014 ዓ.ም ይፋ ያደረገውን መረጃከመረመርን ደግሞ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በየዓመቱ ከኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ይወጣል፡፡

በየዓመቱ ከሀገሪቱ የሚወጣው ህገ ወጥ ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር ይስተዋላል፡፡ ይህ   የሚወጣው ገንዘብ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ መቀመጥ እና የሀገሪቱን አጠቀላይ  አመታዊ የምርት መጠን እና የነፍስ ወከፍ ገቢ ማሳደግ የነበረበት የሀብት መጠን ነው በሀግወጥ መንገድ ከኢኮኖሚ ውስጥ የሚወጣው ፡፡

በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው የአፍሪካ ህብረት የሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውርን  የሚከታተል ከፍተኛፓነል   አምና በፈረንጆ አቆጣጠር የካቲት 7፣ 2015 በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ውስጥ  በሰጠው መግለጫ፤ በአህጉሪቱ በከፍተኛየገንዘብ መጠን በሕገ ወጥ መንገድ ከሚወጣባቸው 10 ሀገራት አንዷ  ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሷል፡፡ ከ1970-2008 ባለው ጊዜ ውስጥከኢትዮጵያ የወጣው 16.5 ቢሊየን ዶላር  እንደነበር ይገመታል፡፡ ከ2010 በኋላ ደግሞ 10 ቢሊየን ያህል የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ መውጣቱን የህብረቱ ከፍተኛ ፓነል አጋልጧል፡፡

በአምስት ዓመታት ብቻ በህገወጥ መንገድ በድብቅ የወጣው የገንዘብ  መጠን በአራት አስርተ ዓመታት የወጣዉን ሊያክል ምነም ያህል አልቀረዉም፡፡

እንደ ፓነሉ ሪፖርት አፍሪካ በ 50 አመታት ውስጥ በሀገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ወደ 1 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር አጥታለች ፡፡ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ገንዘቡም  በዋናነነት ለመከታተል በሚያስቸግረው ሙስና እና የጦር መሳርያ ግዢ ላይ ይውላል ፡፡

ከሀገሪቱ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ መጠን እንዳሳሰበው የሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግስት በአየር ማረፊያዎች የክትትልካሜራ መረብን በመዘርጋት እና ልዩ የመረጃ ቡድን በማዋቀር ቁጥጥሩን እንዳጠናከረ ይገልፃል፡፡ የጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣንምክትል ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ንጉሴ በኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ እንደሚወጣ አምነው “በመስሪያ ቤታችን ሠራተኞችዘንድ ያለው የመረጃ ውሱንነት፣ የልምድና ክህሎት እጥረት፤ በትክክል ምን ያህል ገንዘብ ከሀገር እንደወጣ ለማጣራትም ሆነ የችግሩንደረጃ ለመረዳት ችግር ፈጥሮብናል” ብለው ለቱርኩ የዜና ወኪል አኖዶሉ ተናግረዋል፡፡ በ2ዐዐ9 ዓ.ም ማንኛውም ግለሰብ ከ3ዐዐዐ ዶላርበላይ ይዞ ከሀገር  እንዳይወጣ የሚያግድ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ሥራ ላይ ቢውልም መንግስት ቀውሱን ለመፍታት ጥረት እያደረገለመሆኑ ማሳያ ሆነ እንጂ መፍትሔ አልሆነም፡፡

በቦርሳና ሻንጣ ተይዞ የሚወጣው ገንዘብ ከችግሩ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የሚያስረዱ ወገኖች በገንዘብ ማሸሹ ረገድየመንግሥት ባለሥልጣናት ዋና ተዋናዮች ናቸው ይላሉ፡፡ ሴራውም እጅግ የተጠላለፈ እና ውስብስብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በሀገሪቱ የጥቁርገበያ (Black Market) ምንዛሪ መስፋፋት፤ ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ  አብይ ሰበብ መሆኑን ይገለጻል፡፡ በባንኮች ካዝናበቂ የውጭ ምነዛሪ ገንዘብ ባለመኖሩ በርካታ ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው በህገ ወጡ ገበያ ነው፡፡  ይህም በርካታ ገንዘብ ወደ ወጪ በሕገወጥ መንገድ እንዲወጣ ምቹ ሁናቴን ፈጥሯል፡፡

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ከገቢና ወጪ (Import/Export) ንግድ ጋር ተያይዞ ደረሰኝ ላይ የሚፈጸም “ውንብድና” ነው፡፡ አስመጪና ላኪዎችበውጪ ሀገራት ከሚገኙ የንግድ ሸሪኮቻቸው ጋር በሚያካሂዱት ምስጢራዊ ስምምነት በሚያስመጡት እና በሚልኩት ዕቃ ላይ እነደሚመቻቸው በማድረግ ዋጋን ከፍ እንዲሁም ዝቅ በማድረግ የሚከውኑት “አስቀያሚ ጨዋታ” ዋናው የገንዘብ ማስወጫ ስልትእንደሆነ ተጋልጧል፡፡

በ10 ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ  ከወጣው 26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 19.7 ቢሊዮኑ በዚህ መንገድ የወጣመሆኑን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ዘዴው ከውጪ የሚገባ ዕቃን ባልተገዛበት ዋጋ ደረሰኝ ላይ እያፃፉ ከፍተኛ ገንዘብን ከሀገር የሚያስወጡበትሲሆን፤ ከሀገር የሚልኩትንም ምርት በዝቅተኛ ዋጋ ክፍያን በደረሰኝ ተቀብለው ከጊዜያት በኋላ ዶላሩን ውጪ የሚረከቡበት ለመሆኑመረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዘመድ አዝማዶቻቸው ስም በሚከፍቷቸው በእነዚህ አስመጪና ላኪ ኩባንያዎቻቸው ሕገ ወጡን ድርጊት በስፋትይከውናሉ፡፡ ሕገ ወጥ ገንዘብ ከሀገር እንዳይወጣ የሚያግድ አዋጅና ደንብም አልጸደቀም፡፡ አዋጅ ባይወጣም፣ ደንብ ባይጸድቅም፤የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት በገቢ/ወጪ ንግድ ዋጋ ማጭበርበር ላይ ባደረገው ክትትል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከሀገር ሊወጣ የነበረ አራት ሚሊዮን ዶላር መያዙ የችግሩን መጠን ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ከሰሐራ በታች ሀገራት ምድብ ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ በማስወጣት ከተቀረው የዓለም ክፍል የሚወዳዳረውቢታሰስ አይገኝም፡፡ ከክልሉ የጥቅል ምርት (GDP) አንፃር 5.5% በሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውሩ ተበልቷል፡፡ በ10 ዓመታት 9.6 ትሪሊዮንከሚደርሰው ከክልሉ ከገቢ/ወጪ ንግድ፤ ዋጋ ከማምታት ጋር በተያያዘ 529 ቢሊየን ዶላር ከአፍሪካ ወጪ ይወጣል፡፡  ጥናቶች ይህ ቁጥርበ2030 በግማሽ ይቀንሳል ቢሉም ለጊዜው ግን ዝርፊያው ፍጥነት ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ ስለዚህም አጠቃላይ አህጉሪቱም ሆነች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የሚያጡት ገንዘብ መሸሸጊያው ይፋ ባልሆነ የውጪ ሀገራት ባንክ ቋት መግባቱን ይቀጥላል ማለት ነው፡፡