Tele Awardበሚሰጠው አገልግሎት መቆራረጥ ፤ በኔትወርክ ችግር እና በብልሹ  አሰራር ደንበኞቹን በማስመረር የሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ወይም  ቴሌ ዓለም አቀፍ የጥራት ሽልማት አሸነፍኩ እያለ ነው። ይህንንም የድል ዜናውን በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ በተብረቅራቂዋ የሽልማት ምስል አስጊጦ እንኳን ደስ አላችሁ የሚለውን የደስታ መግለጫ ሲያበስር አገር ወክሎ ሻምፒዮን የመኾን ኩራት እየታየበት ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ከጥራት ውጪ በማንኛውም በሌላ ነገር አሸነፍኩ ቢል ይቀበለው የነበረው የድርጅቱ ደምበኛ ሁሉ ጥራት የሚለውን የሽልማቱን ምክንያት  ሲመለከትና ግራ ሲጋባ ተስተውሏል። የኢትዮጵያ ቴሌኮም በጥራት ምክንያት ሲሸለም ያውም የአውሮፓን ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘሁ ሲል ለብዙዎች ግርምትን ፈጥሮ ሰንብቷል።

(መዝገቡ ሀይሉ ያዘጋጀውን የድምፅ ዘገባ መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች)

ከቴሌ አካባቢ እንደተገኘ በተገለጸ መረጃ  እንደሰማነው ቴሌ ይህን ሽልማት ለማግኘት 2 መቶ ሺህ ብር ከፍሏል። ሽልማቱን ለቴሌ ያበረከተለት ድርጅት ዓለም አቀፍ የንግድ ሥራ መሪዎች ክለብ በመባል የሚታወቅ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከዚህ በፊት የተደራጀ ወንጀል እና ሙስና ዘገባ በእንግሊዝኛው Organized Crime and Corruption Reporting እየተባለ በሚጠራ አንድ የመርማሪ ጋዜጠኞች ቡድን በተደረገበት ምርመራ፤ ሐሰተኛ ሽልማት የሚሸጥ ድርጅት እንደኾነ ተጋልጦ ነበር። በምርመራውም ውጤት መሰረት ድርጅቱ ሽልማቱን ሲሰጥ በሽልማቱ ላይ እንደሚገለጸው ጥራትን መሠረት ያደረገ ውድድር እንደማያደርግ እና እንዲያውም ውድድር መሠል ተግባር እንደማያከናውን ተገልጿል።ማንኛውም ገንዘብ መክፈል የቻለ ድርጅት ሁሉ ሽልማቱን ማሸነፍ ይችላልየሚልም መደምደሚያ ተሰጥቶበታል።

የድርጅቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ማቲው ሊደን ከዋዜማ ሬዲዮ ጋር በኢሜይል ባደረጉት ምልልስ ጥራት የሚለውን የሽልማቱን መግለጫ እንደገና ሲያጤኑት ተስተውለዋል።እንደምትረዱት ዓለም አቀፍ የአውሮፓ የጥራት ሽልማት እንደ አይ ኤስ 9 ሺህ የጥራት ሰርተፊኬት አይደለም። ተሸላሚዎቹ እየሰሩ ላሉት ነገር እውቅና መስጠትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትብብር ሊያደርጉ የሚችሉበትን ማስተዋወቂያ መስራት ነው።ብለዋል። ሽልማቱ ከማስታወቂያ አገልግሎቱ በላይ መታስብም እንደሌለበት አምነዋል።

ቴሌ ምን ያህል ከፍሏችሁ ነው ሽልማቱን የሰጣችሁት ለሚለው ጥያቄያችንም በሰጡት ምላሽ፤ኢትዮ ቴሌኮም የመጓጓዣ፣ የምግብና የሆቴል ወጪያቸውን እንዲሁም የስብሰባው ተሳትፎ የሚጠይቀውን ገንዘብ ሸፍነዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ውጪ የከፈለውን የገንዘብ መጠን የነርሱ የግል ምስጢር ስለኾነ ልናገር አልችልም።የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ድርጅቱ ከዚህ በፊት የሸለማቸውን ድርጅቶች ማንነት ባይገልጽም፤ በየዓመቱ ብዙ ሽልማቶችን በዓለም ዙሪያ በተለይም በታዳጊ አገርዕች ላሉ ድርጅቶች እንደሚሰጥ ታውቋል። Organized Crime and Corruption Reporting Project ትኩረት አድርጎ የመረመራቸው በባልካን አገሮች አካባቢ የነበሩትን ተሸላሚዎች ማንነት ቢኾንም፤ በአፍሪካም ለብዙ ድርጅቶች ሽልማቱ ተሰጥቷል። በየአገሩም ያሉ ተሸላሚዎች ማንነት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ኹሉ አነጋጋሪ ሲኾን ተስተውሏል።

እንደምሳሌ ያህልም የናሚቢያው ቴሌኮም ካምፓኒ ኤም በብዙ ማጭበርበርና ደምብ ማፍረስ የሚታማ እና የሚያቀርበውም አገልግሎት እንደ ኢትዮጵያው ቴሌ ሁሉ አነጋጋሪ ቢኾንም፤ የሽልማት ድርጅቱ ለዚህም ካምፓኒ እኤአ 2014 ሽልማቱን ሰጥቶት ነበር። የካምፓኒው የናሚቢያ ደምበኞችም የሽልማቱን አግባብ አለመኾን እያነሱ ሲወያዩበትም ነበር። ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በኾነ ኹኔታ የጋናው 5 ፕላስ የተባለ የብረት አስመጪና ላኪ ድርጅትም ይጠቀሳል። 4 መቶ ሺህ ዶላር በላይ ቀረጥ በማጭበርበር ስሙ ተነስቶ ሲከሰስ የጎደፈ ስሙን ለማስተካከል ከዚሁ ድርጅት የተሰጠውን ክብር እንደ መታያ ሲያቀርበው ነበር።

ከነዚህ ሁሉ በላይ አስገራሚ የነበረው የላይቤሪያው ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የዶክተር ሚልስ ጆንስ ሽልማት ነበር። ዶክተር ሚልስ ከሚታሙበት የሙስና ተግባር በተጨማሪ የአገሪቱን ገንዘብ ራሳቸውን ለፕሬዚዳንትነት ለማስመረጥ መንገድ እየጠረጉበት ነው የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ነበር። የላይቤሪያን ማዕከላዊ ባንክ ገንዘብ እያባከኑ ነው በሚል በአገሪቱ ፓርላማም እንዲሁም ከዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ ሳይቀር የሚወቀሱበትም ድርጊት ገደብ በሌለው ኹኔታ ባንኩ ለብዙዎች ገንዘብ እንዲያበድር በማድረጋቸው ነው። እርሳቸው ላይቤሪያውያን የአገራቸው ኢኮኖሚ ባልቤት እንዲኾኑ አድርግያለሁ በሚሉት እቅዳቸው ለብዙ ላይቤሪያውያን ገንዘብ ማበደራቸው ለተቺዎቻቸው በአገሪቱ ገንዘብ ድምጽ ለመግዛት የሚደረግ ሙከራ እንደኾነ ተቆጥሮ ነበር።

ይህ ክርክር በከረረበት ሰሞን እኚህን የባንክ ገዢ የሚታደጉ ሁለት ሽልማቶች ተበርክተውላቸው ነበር። አንደኛው ድርጅት በአሜሪካ መቀመጫውን ካደረገ አህጉራዊ የአፍሪካውያን ማኅበር ሲኾን ሁለተኛውን ሽልማት ያገኙት ከዚሁ በማድሪድ ከሚገኝ አወዛጋቢ ድርጅት ነበር። ሽልማቶቹም እኚህን ሰው ላይቤሪያውያንን የኢኮኖሚያቸው ባለቤት በማድረጋቸው አሞካሽተዋቸዋል። ዶክተር ሚልስ ምንም ያህል ተቃዋሚ ቢበዛባቸውም እነኚህ ሽልማቶች ያደርጉት የነበረውን ተግባር አበጀህ የሚሉላቸው ዓለም አቀፍ ምስክሮች ኾነው ተቆጥረውላቸዋል። ብዙዎችን ባላስደነቀም ርምጃ ዶክተር ሚልስ 2017 የላይቤሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩም አሳውቀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን የሸለመው ድርጅት ይህን የመሰለ የኋላ ታሪክ ያለው ድርጅት ነው። ብዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ሽልማት ይዘው ለመገኘት እና ተወዳዳሪዎቻቸውን በዓለማቀፋዊ ጥራት እንደሚበልጡ ለማሳየት እንደሚጥሩ ይታወቃል። ይህን ግን ብዙዎች ከቴሌ አልጠበቁትም ነበር። ምክንያቱም በመታለቧ ምክንያት በማትሸጥ ላም የተመሰለውን ቴሌ ማንም ተፎካካሪ ሳይኖርበት ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኾኖ እንደሚቀጥል በመገመቱ ነው። ምን አሳስቦት ይህን አይነት ሙስና ውስጥ ራሱን እንዳስገባ ለመገመትም ይከብዳል። ባለፈው ዓመት ኢንተርናሽናል ቴሌኮምዩኒኬሽን ዩኒየን የተባለ ድርጅት ባወጣው ደረጃ ኢትዮ ቴሌኮም 166 አገሮች መካከል 162 ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አሳውቆ ነበር። ይህን ዓለም አቀፍ ደረጃ በሌላ ዓለም አቀፍ ሽልማት ለማካካስ የተደረገም ርምጃ ከኾነም ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ የዘገየና በቀላሉ ሌጋለጥ የሚችል ማጭበርበር ፈጽሟል።