HMD Saudiዋዜማ ራዲዮ- ሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር በገባችው ውዝግብ የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ወገንተኝነታቸው ወዴት እንደሆነ እንዲያሳውቋት እየጠየቀች ነው።
ሳዑዲ በመላው አለም ያሉ “ወዳጅ” ሀገራት ያለማመንታት ከጎኔ መቆም አለባቸው በሚል እሳቤ በርካታ የአፍሪቃና የእስያ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን ስታግባባ የቆየች ሲሆን አሁን ፊቷን ወደ አፍሪቃ ቀንድ መልሳለች።
በየሀገራቱ መዲና የሚገኙ የሳዑዲ ዲፕሎማቶች ያለፉትን ሶስት ቀናት አጀንዳውን ይዘው መንግስታቱን ለማግባባት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
ሳዑዲና አጋሮቿ ያቀረቡት ባለ አስራ ሶስት ነጥብ ቅድመ ሁኔታ ኳታር ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ፣ ሳዑዲ ኳታር የበለጠ መገለል እንዲደርስባት በርካታ ሀገሮችን የማግባባት ዘመቻ ጀምራለች።

ሱዳንና ኢትዮጵያ በቀውሱ ገለልተኛ አቋም በመያዝ ችግሩ በድርድር እንዲፈታ አስተያየት ስጥተዋል።
ኤርትራ በተድበሰበሰ መልኩ ሳዑዲን ብትደግፍም አቋሟን በዝርዝር እንድታሳውቅ ይጠበቅባታል።
ሶማሊያም ገለልተኛ አቋም መያዟን ብትናገርም ሳዑዲ የቁም ከብት ገበያዋ በመሆኗ ለውሳኔ ፈተና ሆኖባት ቆይቷል።
ሱዳን ከኳታር በቢሊያን ዶላድ የሚቆጠር የኢንቨስትመንት ተቀባይ ስትሆን ይህን ወዳጅነት ማጣት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ሚዛናዊ ዲፕሎማሲን መርጣ ቆይታለች።