HMD Saudi(ዋዜማ ራዲዮ)- ሳዑዲ አረብያ በሱዳን የምታደርገው የግብርና ኢንቨስትመንት በግብጽ የአባይ ወንዝ ድርሻ ይገባኛል ክርክር ላይ ተጨማሪ ስጋት እንደኾነባት ከግብጽ የሚሰሙ ዜናዎች እያመለከቱ ነው።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተብሎ በሚጠራው የኢትዮጵያ ግድብ ፕሮጀክት ምክንያት የ3ትዮሽ ስምምነት ላይ ለመድረስ የምትታገለው ግብጽ፤ ከጎረቤቷ ከሱዳን ጋር ተጨማሪ ፍጥጫ ሊጠብቃት እንደሚችል የሚያመለክቱ ዜናዎች ከወደ ግብጽ መደመጥ ጀምረዋል።
መዝገቡ ሀይሉ ጉዳዩን ተመልክቶታል- አድምጡት

የሱዳን መንግስት፣ የሳዑዲ አረብያን የየመን ዘመቻ በመቀላቀል በሁቲ አማጽያን ላይ በሚደረገው ወታደራዊ ጥቃት ውስጥ አስተዋጽዖ እያደረገች ነው። ይህንንም ተከትሎ የሳዑዲ መንግስት የሳዑዲ አረብያ ባለሀብቶች ሙዋዕለ ነዋያቸውን ወደ ሱዳን በማዞር የሱዳንን ኢኮኖሚ እንዲያግዙ ጠይቃለች። ከዚሁም በሱዳን ከሚደረግ ኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሳዑዲ አረብያ መንግስት በሱዳን የግብርና ማስፋፋት ትብብር ለመጀመር ከሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት 13 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሙዋዕለ ነዋይ በሱዳን እንዳዋለች የሚነገርላት ሳዑዲ አረብያ ይህንን የኢንቨስትመንት መጠን ከፍ በማድረግ በሱዳን የግብርና እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ትፈልጋለች። በመኾኑም ሱዳን በ5 ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ 3 ግድቦችን ለመስራት የሚያስችላትን 1.7 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ተስማምታለች። አጅባር፣ ዳል ና አል ሻሪክ የሚባሉት እነዚህ ግድቦች በሱዳን ሰሜናዊ ክፍል የሚገነቡ ሲኾኑ ዋነኛ አገልግሎታቸውም ለግብርናና ለኃይል ማመንጫ የሚኾን እንደኾነ ተጠቁሟል። ከነዚህም ግድቦች በተጨማሪ ለሚሰሩ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ልማት የሚኾን 500 ሚሊዮን ዶላርም መድባለች። ይህም ገንዘብ በምስራቁ የሱዳን ክፍል በሚገኙት በ አትባራና ሰቲት ወንዞች ላይ ለሚደረግ የ 1 ሚሊዮን ሄክታር የግብርና ልማት እንደሚውል ተገልጿል።

ይህ የሳዑዲ አረብያ እንቅስቃሴ ለግብጽ ተጨማሪ ፈተና ጥሎባታል። የቀድሞው የግብጽ የውሃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትር ሞሐመድ ናስረዲን ኦላም ከዚህ በፊት ሲናገሩ “የኢትዮጵያው የግድብ ተሞክሮ በኢትዮጵያ ብቻ የሚቀር ሳይኾን ወደሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገራት የሚዛመት ጦስ ይዞ ይመጣል” ብለው ነበር። ይህም ስጋታቸው በዚህ የሱዳን ፕሮጀክት እውን የኾነ መስሏል። ሞሐመድ ነስረዲን በዚሁ ማስጠንቀቂያችው ላይ ከሱዳን በኩል ሊነሳ ይችላል ብለው እንደ ስጋት ያስቀመጡት የግብርና ማስፋፋት ፍላጎት እውን እንደኾነ እየታየ ነው።

እኚሁ የቀድሞ ሚኒስትር ግብጽ ኢትዮጵያን ለማስገደድ ወታደራዊ ርምጃን እንደ አማራጭ መጠቀምን አጥብቀው የሚደግፉ ሲኾኑ፤ ከህዳሴው ግድብ ጎን ለጎን ብዙም የማይወራላቸውን ተጨማሪ 3 የኢትዮጵያ የግድብ ፕሮጀክቶች እንዳይዘነጉ የሚወተውቱ ፖለቲከኛ ናቸው። እንደርሳቸው አባባልም 3ቱ ተጨማሪ የኢትዮጵያ ግድቦች ስኬታማ ከኾኑ በድምሩ የሚያስከትሉት ጉዳት ለግብጽ አደገኛ ሊኾን እንደሚችልም ሲናገሩ ቆይተዋል።
እኤአ በ1959 በተደረገው ስምምነት መሰረት ሱዳን ከአባይ ውሃ አመታዊ ፍሰት ውስጥ የተመደበላት ድርሻ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው። በአንጻሩ ግብጽ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ታገኛለች ፡ በግብጽ እና በሱዳን መካከል የተደረገው ይህ ስምምነት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወንዙ የሚመነጭባቸዉንና የሚያልፍባቸውን ስምንት የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ያገለለለ ነው ፡፡
ግብጻውያኑ እንደሚሉት ሱዳን ይህን ድርሻዋን ምንም ሳታስቀር ትጠቀማለች። ከዚህ በኋላ የሚደረግ ማንኛውም አባይን መሰረት ያደረገ ፕሮጀክት ከስምምነቱ ጋር በመጣረስ በቀጥታ የግብጽን ድርሻ የሚነካ ይኾናል ብለው ይሰጋሉ። የግድቡ ውኃ ለግብርና መስኖ መዋሉ ከሚያስከትለውም ችግር በተጨማሪ ሱዳን ባላት የአየር ጸባይ ምክንያት በትነትና በብክነት ምክንያት የሚጠፋው የውሃ መጠን ሊያስከትል የሚችለውም የውኃ መቀነስ ያሳስባቸዋል።
ይህን የሱዳንን የግብርና ማስፋፋት መቃወም ለግብጽ ቀላል ነገር እንደማይኾንም ይገመታል። ለወትሮም ቢኾን በ3ትዮሹ ድርድር ላይ ለኢትዮጵያ ታደላለች የሚሏት ጎረቤታቸው ሱዳን ሳዑዲ አረብያን ያህል ትልቅ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል ከጎኗ አሰልፋለች። ቱርክ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስና ኢራንም ከሱዳን ጋር ተጨማሪ ስምምነቶችን ለማድረግ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል።
የዐረቡን ዓለም 45% የሚኾነውን ለእርሻ ምቹ የኾነ መሬት እንደያዘች የሚነገርላት ሱዳን በቅርቡ ኢኮኖሚዋን ለኢንቨስትመንት በሚያመች መልኩ ለማማሻሻል የሚያስችል ርምጃ መውሰዷን ይፋ አድርጋለች። ራሷንም የዐረቡ ዓለም የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ መዘጋጀቷንም በቅርቡ ተደርገው በነበሩት የሳዑዲና የሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረምና በሱዳን እና በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ፎረም ላይ አስተዋውቃለች። ይህም ያደረገችው ማሻሻያ በሁቲ አማጽያን ላይ ለመዝመት ካሳየችው ፍላጎት ጋር ተደማምሮ ሰፊ የኢንቨስትመንት በር ከፍቶላታል።
ይህም የሳዑዲ አረብያና የሱዳን ስምምነት በ1959 የአባይ ወኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ግብጽና ሱዳን በተፈራረሙት ስምምነት ላይ ሌላ ተጨማሪ ፈተና ሊፈጥርበት እንደሚችል አመላካች ነው።