ዋዜማ ራዲዮ-

አዲስ የተጨመረ ዘገባ (12:00 ሰዓት ምሽት ድረስ)

በጎንደር የተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ምሽቱ 12 ድረስም እንዳልበረደ የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዋዜማ ገለጹ፡፡ ከነዋሪዎች በተገኘው መረጃ እስካሁን በትንሹ ሁለት ሰዎች ተገድለው በርካቶች ቆስለዋል፡፡ ከቆሰሉት መካከል በጎንደር ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኝ ባንዲራ ለማውረድ የሞከረ አንድ ወጣት እንደሚገኝበት የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

አሁንም በከተማይቱ የተኩስ ድምጽ የሚሰማ ሲሆን በየቦታው ጭስ እንደሚታይም አስረድተዋል፡፡ መንገዶች በሚቃጠል ጎማ እና በተለያዩ ቁሳቁሶች መዘጋታቸውንም ይናገራሉ፡፡ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ በየቦታው እንደተሰማራ እና ለተቃውሞ ወደ ጎዳና የሚወጡ ነዋሪዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እንደሚተኩሱ ይገልጻሉ፡፡

በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚተኩሱ አስለቃሽ ጭሶች በመኖሪያ ቤት ግቢ ጭምር ሲያርፍ መመልከቷን አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ ለዋዜማ ገልጻለች፡፡ ነዋሪዎች በየቤታቸው ሆነው በአስለቃሽ ጭስ የመታጠን እጣ እንደገጠማቸው ጭምር ታስረዳለች፡፡

በአሁኑ ሰዓት በከተማይቱ የሞባይልም ሆነ የኢንተርኔት ግንኙነት ማድረግ አዳጋች መሆኑን ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ ወደ ጎንደር የሚደረጉ የስልክ ግንኙነቶች ከፍተኛ የጥራት ችግር እንደሚስተዋልባቸው የዋዜማ ዘጋቢዎች ታዝበዋል፡፡

የቀደመ ዘገባችን (እስከ 10 ሰዓት ተኩል የነበረው)

ከሶስት ሳምንት በፊት በጸጥታ ኃይሎች እና በከተማይቱ ነዋሪዎች መካከል ግጭት አስተናግዳ የነበረችው ጎንደር ዛሬ አርብ ሐምሌ 29 በተቃውሞ እና በተኩስ እየተናጠች ትገኛለች። ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሱ ጥይቶች ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ሞተዋል።

የዛሬው ግጭት መንስኤ በቀደመው ግጭት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት እና የወልቃይት ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍርድ ቤት የመቅረብ ያለመቅረብ ጉዳይ ያስነሳው ውዝግብ ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት ኮሎኔሉ ሳይመጡ በመቅረታቸው ቦታው ተገኝቶ ይጠባበቃቸው በነበረው ህዝብ ዘንድ ጉርምርምታ አስነስቶ ነበር፡፡ ኮሎኔሉ ባልቀረቡበት ለአርብ መቀጠራቸውን የሰማው የከተማይቱ ነዋሪ በዛሬው ዕለት ከጠዋት ጀምሮ ፋሲል አካባቢ በሚገኘው የጎንደር ፍርድ ቤት በብዛት ተገኝቶ የሰውየውን መምጣት ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡

ችሎቱን ለመታደም የተሰበሰበውን ህዝብ ቁጥር የተመለከቱ የጸጥታ ኃይሎች የኮሎኔሉን መምጣት ማዘግየታቸውን የከተማይቱ ነዋሪ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ ኮሎኔል ደመቀ “እንደቀደሙት ቀጠሮዎች ሁሉ አይቀርቡም” የሚል ግምት የያዘው በፍርድ ቤት የተገኘው ነዋሪ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተፋጥጦ ይቆያል፡፡ በፍርድ ቤቶች የተለመደ አሰራር መሰረት ከሐምሌ 30 በኋላ ችሎት እንደማይኖር የገመቱት ነዋሪዎች ሁኔታው አስቆጥቷቸው ተቃውሞ መጀመራቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ተቃውሞው በቪዲዩ ጭምር ታግዞ በማህበራዊ ድረ ገጾች ጭምር ተለቅቋል፡፡ በቪዲዩው ላይ “ይለያል ዘንድሮ” የሚል የመፈክር ድምጽ ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ ከመርገብ ይልቅ እየከረረ የመጣው የሁለቱ ወገኖች ፍጥጫ ወደ ግጭት ማምራቱን በአካባቢው የነበሩ እማኞች ያስረዳሉ፡፡ እንደ አንድ የዋዜማ ምንጭ ገለጻ ችሎቱን ሊታደሙ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የነበሩ ግለሰቦች በፍርድ ቤቱ ተሰቅሎ የነበረውን ባንዲራ በማውረድ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ልሙጥ ባንዲራ ለመስቀል ሞክረዋል፡፡

በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ተቃውሞ የሚያሰሙትን ወገኖች ለመበተን በመጀመሪያ አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ተቃውሞው ሲያይል በኦራል እና በፒካፕ የተጫኑ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው መድረሳቸውን ያስረዳሉ፡፡ የጸጥታ ኃይሎቹ የመከላከያ ሰራዊት ዩኒፎርም መለያ የለበሱ እንደነበሩም ያብራራሉ፡፡ አንዳንድ ምንጮች እነዚህን ወታደሮች የ“አግአዚ” አልሞ ተኳሾች ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

ተጨማሪ ኃይል መምጣቱን ተከትሎ ሁኔታው ወደለየለት ግጭት ማምራቱን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ በተኩስ ጭምር የታጀበ እንደነበር የሚያስረዱት ነዋሪዎች ከዚያ በኋላ ወደ ሌሎች የከተማይቱ ቦታዎች እንደተስፋፋ ይገልጻሉ፡፡ በግጭቱ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

“የዛሬው በጣም ያስፈራል” ትላለች አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ ሁኔታውን ለዋዜማ ስትገልጽ፡፡ “ሰሚ እንኳን በሌለበት እየሞትን ነው” ስትል የግጭቱን አስፈሪነት ትናገራለች፡፡

በከተማይቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ንብረቶች ላይ ጉዳቶች እንደደረሱ፣ የቃጠሎ ጭስ እንደሚታይ፣ የጥይት ተኩስ እንደሚሰማ እና መንገዶች መዘጋታቸውን የተለያዩ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ ተጧጥፎ በቀጠለበት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጽህፈት ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ በመስጠት ላይ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ “ሰሞኑን በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አንዳንድአካባቢዎች የተካሄዱ እና እየተጠሩ ያሉ ሰልፎች አግባብነት እንደሌላቸው” ማንሳታቸውን መንግስት ዘመም የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል፡፡

“በህገ መንግስቱ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት የተጠበቀ ቢሆንም፥ ሰሞኑን የተካሄዱት እና ለማካሄድ የሚፈለጉት ሰልፎችግን ከህግ አግባብ ውጪ ባለቤት የሌላቸውና በማህበራዊ ድረ ገጾች የተጠሩ ያልተገቡ ቅስቀሳዎች ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ፋና ዘግቧል፡፡ “መንግስት ህግ ለማስከበር ህገወጥ ድርጊቶችን የመግታት ኃላፊነቱን ይወጣል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውንም ጠቅሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከመግለጫቸው በኋላ በደቡብ ሱዳን ብጥብጥ ዙሪያ እየተካሄደ በሚገኘው የኢጋድ ሀገራት መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሸራተን አዲስ አቅንተዋል፡፡ የሸራተኑ ስብሰባ መክፈቻ ባልተለመደ ሁኔታ ለጋዜጠኞች ዝግ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

የአዘጋጁ ማስታወሻ-በየደቂቃው የሚደርሰንን መረጃ እናክልበታለን፣ ይህ በአዲስ አበባ ስዓት አቆጣጠር አርብ ከቀኑ 12:00 ድረስ የተጠናቀረ ነው