ENDF

የኢትዮዽያ መከላከያ ሰራዊት እየፈረጠመ የመጣ የኢኮኖሚ ቅርምት በመጪው ጊዜ ሰራዊቱ የሲቪል አሰተዳደሩን በሰሩ የመዋጥ አልያም በመፈንቅለ መንግስት ገሸሽ የማድረግ ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል። ዋዜማ ሬድዮ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ዘገባዎች ታቀርባለች። ቻላቸው ታደሰ ያዘጋጀውን አድምጡ

 

የኢትዮጵያ ጦር ሃይል በአፍሪካ ከግብፅ ቀጥሎ ሁለተኛው ጠንካራ ሃይል ሲሆን በዓለም ደግሞ 29ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉት አምስት ሃያላን ሀገራት አንዷ ነች፡፡ ለዚህ ደረጃ ያበቃት አንዱና ዋኛው አላባ ወታደራዊ ሃይሏ ነው፡፡ ጦር ሰራዊቱ ከአሜሪካ መንግስትም ወታደራዊ እርዳታ ሲቸረው እንደኖረ ይታወቃል፡፡ ለሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ልዕለ ሃያል ሀገር (regional hegemon) መሆን መንግስትና አንዳንድ ታዛቢዎች አስረጂ አድርገው የሚያቀርቡትም ወታደራዊ ሃይሏ ነው፡፡
መንግስትም ሰራዊቱ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን የውጭ ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ዋልታ፣ የኢትዮጵያ ትንሳዔ አብሳሪና የኢኮኖሚ ዕድገቱ ምሰሶ መሆኑን ደጋግሞ ይገልፃል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁንም ቢሆን ወታደራዊ-ነክ ጉዳዮች በህዝቡም ሆነ በተቃዋሚዎች ዘንድ በአደባባይ ውይይት የማይደረግባቸው አይነኬ ጉዳዮች በመሆናቸው ህዝቡ በቂ ግንዛቤ የለውም፡፡ የመከላከያ ኢንዱስትሪው ግዙፍ ሃብትና ምርቶች በከፊልም ቢሆን ለህዝቡ ይፋ የሆኑት በከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ በሚከበሩት የሰራዊቱ ቀኖች ወቅት በተዘጋጁት ኤግዚብሽኖች አማካኝነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ከግዙፉ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ጀርባ የሚያንዣብበው ፖለቲካዊ አደጋ ገና በደንብ የተጤነ አይመስልም፡፡ በመከላከያ ሚንስቴር ሚስጢራዊነት ሳቢያም በወታደራዊ ኢንዱስትሪው ባጀት አጠቃቀምም ሆነ የሰራ ሂደቱ ላይ ፓርላማው ያለው ቁጥጥር በጣም አነስተኛ እንደሆነ የሚካድ አይደለም፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት ለጦር ሰራዊቱ የኢኮኖሚ አቅም መጎልበት የሰጠው ትኩረት በማደጉ በህግ ማዕቀፍ ረገድ የጦር ሰራዊቱ ኢኮኖሚያዊ ይዞታ እንዲፈረጥም የሚያስችሉ ደንቦችንና አዋጆችን በማውጣት በስራ ላይ አውሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በመንግስት ልማት ድርጅትነት የተመዘገቡት የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ፣ የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት እንዲሁም የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሰራዊቱን ሞራልና ኑሮ ለማሻሻል ያስችላል የተባለው የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽንም በህግ ተፈቅዶ ሰራ ላይ ውሏል፡፡
በተለይ ከአምስት ዓመት በፊት በ10 ቢሊዮን ብር (ወይም ግማሽ ሚሊዮን ዶላር) መነሻ ካፒታል የተቋቋመው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የተላለፉለትን የልማት ድርጅቶች ጨምሮ የ15 ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችና የ100 ፋብሪካዎች ባለቤት ሆኗል፡፡ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ብቻ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስገቡ የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች ይጠቅሳሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የመከላከያ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ያልገባበት ትርፋማ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማግኘት አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ በወታደራዊ ፍጆታዎች በኩልም አውቶማቲክ መሳሪያዎች፣ የታንክ መለዋወጫዎች፣ ሞርታርና ላውንቸር የሚያመርት ሲሆን ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችንና አውሮፕላኖችንም የመጠገን አቅም አዳብሯል፡፡
የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች “ተልዕኳቸውን ለማሳካት በሚያስችሉ ዘርፎች” ሁሉ እንዲሰማሩ መንግስት ስለፈቀደላቸው እምብዛም ገደብ የለባቸውም፡፡ ስለሆነም ድርጅቶቹ ለሲቪል አገልግሎት የሚውል ብረታ ብረት፣ ጀነሬትርና ትራንስፎርመር፣ ከባድ ማሽነሪዎች እንዲሁም የከተማ አውቶብስ፣ የባቡር ፉርጎ፣ ትራክተር፣ ቡል ዶዘርና ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠምና ለገበያ ማቅረብም ዋነኛ ስራዎቻቸቸው ሁነዋል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊትም መከላከያ ሚንስቴር “የሰራዊት ባንክ” (Army Bank) በማቋቋም ወደ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለመግባት እያቆበቆበ ስለመሆኑ ለፓርላማው ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
መንግስትም አሁንም በርካታ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጄክቶችንና ምርት አቅርቦቶችን ያለ ጨረታ ለመከላከያ ተቋማት በኮንትራት እየሰጠ ይገኛል፡፡ የተቋሙ ኢንዱስትሪዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብን ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ከመረከባቸውም በላይ በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተያዙትን በርካታ የስኳር ልማትና ማዳበሪያ ፕሮጄከቶችንም እየገነቡ ይገኛሉ፡፡
እዚህ ላይ አሳዛኙ ነገር የሀገሪቱ የግል ዘርፍ ከወታደራዊ ኢንዱስትሪው ጋር ሽርክና የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በአንፃሩ የመከላከያው ኢንዱስትሪ ተቋማት ዋነኛ ሸሪኮች መሰል የአሜሪካ፣ አውሮፓና ቻይና ድርጅቶች ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ከሃያላን ሀገሮች ጦር መሳሪያ አምራች ድርጅቶች ጋር ብቻ ሳይሆን በተባበሩት መንግስታት የጦር መሳሪያ ማዕቅብ ከተጣለባት ሰሜን ኮሪያ ጋር ሳይቀር የስራ ግንኙነት እንዳላቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡
ገና በማቆጠቆጥ ላይ ካለው የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ አንፃር ሲታይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነትና ምናልባትም በብቸኝነት ለመቆጣጠር በመንደርደር ላይ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህ ላይ የህወሃት ኢንዶውመንቶች ሲታከሉበት በነፃ ገበያ ላይ የተመሰረተው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሁለት አቅጣጫ ከባድ አደጋ እንደተደቀነበት ያረጋግጣል፡፡ ስለሆነም የመከላከያ ኢንዱስትሪ ኢምፓዬር በግዙፎቹ የህወሃት ኢንዶውመንቶች ተደቁሰው በመቀጨጭ ላይ ያሉትን የግል ድርጅቶች ጭራሹን ከገበያ እንዳያሳወጣቸው ያሰጋል፡፡ ምናልባት ህወሃት ኢንዶውመንቶቹ ከመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚዋሃዱበት ወይም በጋራ የሚሰሩበትን ዕድል ያመቻች ይሆናል እንጂ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ወደፊት ከኢንዶውመንቶች ጋርም ፉክክር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡
ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት የጦር ሰራዊቱ ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ መፈርጠም በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ቁልፍ ሚና እንዲኖረው መገፋፋታቸው አይቀሬ ይሆናል ይላሉ፡፡ እንዲያውም የአንዳንድ ታዛቢዎች ስጋት በጦር ሰራዊቱ የሚቀነባበር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትንም የሚጨምር ሁኗል፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ ይህ የወታደራዊ ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ መፈርጠም ምን ዓይነት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውጤት ያስከትላል? የሚለው ይሆናል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ሁለት ተፎካካሪ የስልጣን ማዕከሎች (contending power centers) ይፈጠሩ ይሆን? እውነት አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሰጉት ሁኔታው አንፃራዊ ነፃነት በመጎናፀፍ ላይ ያለው የጦር ሰራዊቱ አመራር ለሲቪሉ መንግስት ያለው ተጠያቂነት ላልቶ ጦር ሰራዊቱ ራሱ የፖለቲካ ተዋናይ እንዲሆንና ስልጣን እንዲይዝ ያደርገው ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡
ኢትዮጵያን የእጅ መዳፋቸውን ያህል ያውቋታል የሚባልላቸው ታዋቂው አሜሪካዊ ምሁር ሬኒ ሌፎርት አምና ባስነበቡት አንድ መጣጥፍ “የፀጥታ ሃይሎችና ጦር ሰራዊቱ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት (a state within a state)” ሁነዋል እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ተጠሪነታቸውም ለሲቪሉ መንግስት ሳይሆን ለራሳቸውና ለተወሰኑ የህወሃት አመራሮች ብቻ መሆኑንም በመጠቆም፡፡ “በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖለቲካ በጠመንጃ ላይ የነበረውን የበላይነት አጥቷል” ሲሉ መደምደማቸውም የሀገራችን ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማል፡፡
የምሁሩ ከባድ ድምዳሜዎች ሀገሪቱ ለወታደራዊ አገዛዝ ወይም መፈንቅለ መንግስት የተመቻቸ ሁኔታ ላይ እንደሆነች የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ግን በህገ-መንግስቱ መሰረት ጠቅላይ ሚንስትሩ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆናቸውን ለሚያውቀው ተራው የኢትዮጰያ ህዝብ አስደንጋጭ መርዶ መሆናቸው እሙን ነው፡፡
በእርግጥ እስካሁን ያለው ሁኔታ ምሁሩ ሬኒ ሌፎርት የገለጡትን ያህል ስለመሆኑ ሊያጠራጥር ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ ዜጎች አንድ ቀን ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ሀገራቸውን በይፋዊ ወታደራዊ መዳፍ ስር ላለማግኘታቸው ዋስትና የለም፡፡ እንደሚታወቀው በአፍሪካ የግዙፍ ወታደራዊና ሲቪል ኢንዱስትሪዎች ባለቤት በመሆን ረገድ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆነው የግብፅ ጦር ሰራዊት የዕለት ተለት ምግብ ፍጆታ የሆነውን ዳቦ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሳይቀር ባለቤት መሆኑ ምን ያህል ዋነኛ የፖለቲካ ተዋናይ እንዳደረገው ባለፉት አራት ዓመታት በገሃድ እየታየ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ሃይል በፖለቲካው ላይ ስለሚኖረው ሚና ሶስት ዋና ዋና የ“ቢሆን መላ ምቶች”ን (possible scenarios) ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አንደኛው መላ ምት ሲቪሉ መንግስት ህገ መንግስቱን በመጣስ ጦር ሰራዊቱ የሀገር ውስጥ ፖለቲካው የጀርባ አጥንት እንዲሆን ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል የሚለው ነው፡፡ ሰራዊቱም የቢዘነስ ኢምፓዬር እንዲገነባ የፈቀደለት የፖለቲካ ስርዓት በማናቸውም መልኩ እንዲቀጥል ጥብቅና በመቆም የሁለትዮሽ እከክልኝ ልከክልህ አሰራር እንዲሰፍን ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር ሲቪሉ መንግስት ሲቪላዊ ማንነቱንና አደረጃጀቱን ይዞ እንዲቀጥል ለማስቻል ጦር ሰራዊቱ ሃይል እስከመጠቀም ሊደርስ ይችላል፡፡ ወይም መፈንቅለ መንግስትን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት እንዲቀጥል ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ በግብፅ ከዓመታት በፊት ሆስኒ ሙባረክ በህዝባዊ ተቃውሞና በራሱ በጦር ሰራዊቱ የመጨረሻ ሰዓት ግፊት ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ጦር ሃይሉ ምንጊዜም የሲቪሉ መንግስት ጠበቃ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከጅምሩም የሀገራችን ጦር ሰራዊት ፖለቲካዊ ገለልተኛነት አስተማማኝ ባይሆንም ሲቪሉ መንግስታዊ አመራር የጦር ሰራዊቱ መኮንኖች በፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ ጥርጊያ መንገዱን ያመቻቸላቸው ግን እኤአ ከ2001 የህወሃት ክፍፍል ጀምሮ ነው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስለሆነም የጦር ሰራዊቱ አመራርና የሲቪሉ ፖለቲካዊ አመራር እጅና ጓንት መሆን ይህን የ“ቢሆን መላ ምት” ከመላ ምትነት አልፎ ወደ ተጨባጭነት የተጠጋ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ እስካሁንም ከሞላ ጎደል በተግባር ሲታይ የኖረው ይህንኑ የሚያጠናክር ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው የ“ቢሆን መላ ምት” ደግሞ በሲቪሉ አመራርና ወታደሩ የስልጣን ሽኩቻ ተነስቶ ሰራዊቱ ሲቪሉን መንግስት ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ገልብጦ ስልጣን ሊይዝ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ልክ ከዓመት በፊት ታይላንድ በፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ስትዘፈቅ ጦር ሰራዊቱ እንዳደረገው መፈንቅለ መንግስት ወይም ከዓመት በፊት የግብፅ ጦር ሰራዊት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡት የሙስሊም ወንድማማቾቹ ሙሃመድ ሙርሲ ላይ እንዳደረገው መፈንቅለ መንግስት ዓይነት ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ይኸኛው የ“ቢሆን መላ ምት” በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ውስጥ የመሞከሩም ሆነ የመሳካት ዕድሉ እምብዛም ይመስላል፡፡
በሶሰተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው የ“ቢሆን መላ ምት” ጦር ሰራዊቱ በሲቭሉ መንግስት ጋባዥነት (coup with civilian consent) በብቸኝነት ወይም ከራሱ ከሲቪሉ ጋር ተዳብሎ ስልጣን ሊይዝ ይችላል የሚለው ነው፡፡ በእርግጥም እስካሁን የሚታየው የህወሃት-ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሁኔታ እንደ የመጀመሪያው መላ ምት ሁሉ ይህንንም መላ ምት የሚያጠናክር ይመስላል፡፡ ስለሆነም ከመፈንቅለ መንግስት አንፃር ከታየ ለእውነታ የሚቀርበው ይኸኛው ነው፡፡
በጠቅላላው እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ገፊ ምክንያቶች ሊሆኑ ከሚችሉት ውስጥ ዋነኛው መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ቀውስ መከሰት እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ለምሳሌ እንደ 1997ቱ ምርጫ-አመጣሽ ቀውስ ዓይነት፡፡ ፖለቲካዊ ቀውስ የሚፈጠረው ደግሞ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ መስጠት ካቻለ ወይም ካፈለገ ይሆናል፡፡ መላ ምቱ ለእውነታ ያለውን ቅርበት የሚያሳየው ደግሞ መንግስት ለሀገሪቱ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ያለው ፖለቲካዊ ፍላጎትና ተቋማዊ ብቃት እየተኮላሽ መሄዱ ነው፡፡