METEC former boss Geb. Kinfe Dagnew

ዋዜማ ራዲዮ- የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)  ካሳየው የብቃት ማነስና ከሚጠረጠርበት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ብክነትና ሙስና በተጨማሪ የሀገሪቱ ቁልፍ ፕሮጀክቶች ለዓመታት እንዲጓተቱ ሰበብ ሆኗል። የህዳሴው ግድብ አንዱ ነው። በህዳሴው ግድብ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ላይ ከደረሰው መስተጓጎል በተጨመሪ ለግድቡ ውሀ መተኛ የደን ምንጣሮ ለማድረግ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር ወስዶ አብዛኛው ገንዘብ የደረሰበት አይታወቅም። የምንጣሮ ስራውን እንዲያከናውኑ ስምምነት የፈረሙ 160 ማህበራት 340 ሚሊየን ብር ሊከፈላቸው ሲገባ ሜቴክ ገንዘቡን ከልክሎናል ብለዋል። ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት ክርክር ሲደረግበት ስንብቷል። የዋዜማ ሪፖርተር ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ተመልክቷል። ባለጉዳዮችንም አነጋግሯል። 

በ2006 አ.ም ነበር ሜቴክ የህዳሴው ግድብ ውሀ የሚተኛበትን ቦታ ደን ለመመንጠር በሄክታር 48 ሺህ ብር ተስማምቶ 2.6 ቢሊየን ብር የወሰደው።ስራውን ሲወስድ እንደተለመደው በአድልዎ ነው። ሜቴክ ይህንን ስራ እንዲሰሩለት ለ160 ማህበራት በ700 ሚሊየን ብር 56 ሺህ ሄክተር መሬቱን እንዲመነጥሩ ውል ይሰጣቸዋል።በጣም አስቸጋሪና ወጣ ገባ የሆነውን መሬት በሄክታር 13 ሺህ ብር የመሬቱ አስቸጋሪነት እየቀነሰ ሲመጣ በሄክታር 11 ሺህ ብርና 6 ሺህ ብር ድረስ እየወረደ በሶስት ተከፍሎ ውሉ ይታሰራል። ሜቴክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ደኑን ለመመንጠር በሄክታር 48 ሺህ ብር ነው የተከፈለው።የሆነው ሆኖ ማህበራቱ በተገባው ውል እየሰሩ የመነጠሩት መሬት በሜትር እየተለካ የክፍያ ምስክር ወረቀት እየተሰጣቸው ለሶስት ጊዜ ገንዘብ ተቀብለዋል።በዚህ መልኩ 56 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያለ ደንን እንደመነጠሩ የሚያሳይ የሜቴክ ሰዎች በተገኙበት በሜትር ተለክቶ የተሰጣቸውን ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የሚያሳየውን የምስክር ወረቀት ተመልክተነዋል።

ነገር ግን ማህበራቱ በውሉ መሰረት 56 ሺህ ሄክታር መሬቱ ላይ ያለውን ደን ይመንጥሩ እንጂ ለዚህ ስራ ከገቡት የ700 ሚሊየን ብር ውል ውስጥ ቀሪ 340 ሚሊየን ብር ክፍያ ነበራቸው።ችግር መፈጠር የጀመረውም እዚህ ጋር ነው።ሜቴክ ለማህበራቱ ገንዘቡን በ2007 አ.ም መፈጸም ነበረበት።ኮርፖሬሽኑ ግን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ክፍያውን ያዘገይባቸዋል።የማህበራቱ አባላት ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ደግሞ ለደን ምንጣሮው የሚያስፈልጉ ማሽኖችን በብድር ጭምር የገዙ በመሆኑ እንዲሁም በስራቸው እስከ 300 ሰው የቀጠሩ በመኖራቸው በክፍያው መዘግየት ምክንያት መቃወስ ተፈጥሯል።

METEC -EPEI

ማህበራቱ ሜቴክ ገንዘባቸውን እንዲከፍላቸው በወቅቱ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ የነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ጭምር ምልጃ ሞክረው ነበር።ሆኖም ዶክተር ደብረጽዮን ማህበራቱን በወቅቱ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጋር ይልኳቸዋል።ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ግን ለማህበራቱ የመለሱት ዛቻ እንደነበር የማህበራቱ ተወካዮች ይናገራሉ። ጀነራሉ ጭራሽ ማህበራቱን እንኳን ቀሪውን 340 ሚሊየን ብር እንዲከፈል ሊያዙ ማህበራቱን አጭበርብራችሁናል ፣ ክፍያ የምንፈጽምላችሁ በጂፒኤስ ለክተን ነው ይሏቸዋል።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ይህን ሁሉ የሚሉት የራሳቸው መስሪያ ቤት ሰራተኞች በስፍራው ተገኝተው ማህበራቱ የመነጠሩት መሬት በሜትር እየተለካ ተረጋግጦ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያዝ የምስክር ወረቀት ማህበራቱ በእጃቸው እያለ ነው።ከዚያም ሜቴክ የተመነጠረውን ደን በጂፒኤስ ለክቻለሁ ብሎ ማህበራቱ እንዳሉት ደን የተመነጠረበት የመሬት ስፋት 56 ሺህ ሄክታር ሳይሆን 29 ሺህ ሄክታር ነው በማለት አይደለም ቀሪ 340 ሚሊየን ልከፍላችሁ ያልሰራችሁበትን ገንዘብም ወስዳችሁዋል በማለት እዳ ክፈሉ ብሎ ሰነድ አምጥቶላቸዋል።

ነገሮች ድንገተኛ የሆነባቸው ማህበራቱ የተፈጠረውን ግጭት በፍርድ ቤት እንፍታው ወይስ በመንግስት ባለስልጣናት ምልጃ እንፍታው በሚል ለሁለት ይከፈላሉ።የተወሰኑ ሜቴክን ከሰን ፍትህ ማግኘት ዘበት ነው በሚል በባለስልጣናት በኩል ማግባባቱን እንቀጥል ሲሉ የተወሰኑት ደግሞ ሜቴክን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ፍትሀብሄር ችሎት ክስ ይመሰርታሉ።

የፍርድ ቤት ሂደቱ ምን ይመስላል?

Debretsion G Michael, former METEC cluster head

ከሳሽ ማህበራት ሜቴክ የራሱ ባለሙያዎች ባሉበት የመነጠርነው የደን ስፍራ በሜትር ተለክቶ ገንዘብ ይከፈላቸው የሚል ምስክር ወረቀት ተሰጥቶን ክፍያ አልፈጽምም አለ ሲሉ ሜቴክ ደግሞ ማህበራቱ ከኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው  አጭበርብረውኛል በጂፒ ኤስ አስለክቼም ማህበራቱ ሰራነው ካሉት መሬት በታች መመንጠራቸውን አረጋግጫለሁ ብሎ ካርታ ያቀርባል።  ሜቴክ እንደገና መሬቱን ለካሁ ያለው ማህበራቱ በሌሉበት ነው። እንደገና ቀድሞ ማህበራቱ ያቀረቡት ሰነድ ስለመጭበርበሩ ያመጣው መረጃ የለም። ይህን እንዲዳኙ የተመደቡት የመጀመሪያው ዳኛ ባልታወቀ ምክንያት ከዚህ መዝገብ መገለላቸው ተሰማ ።  ህትመት አሰፋ የተባሉ ዳኛም ተተኩ። እኚህ ዳኛ ሜቴክ እንደገና ለክቻለሁ ያለውን ከሳሽ ማህበራት በሌሉበት ያደረገው በመሆኑ ማስረጃውን ውድቅ አደረጉት።ነገር ግን አወዛጋቢ ትእዛዝን ሰጡ። ዳኛዋ መሬቱ እንደገና ይለካ የሚልና ለመለካት ደግሞ ከሜትርና ጂፒኤስ የቱ ይሻላል? የሚል ማብራሪያ ከኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ ።

ማህበራቱ ደን ሲመነጥሩ ከቦታው አስቸጋሪነት አንጻር ምልክት ብቻ እየተሰጣቸው ነበር የሰሩት ።በዛ ላይ ምልክቶቹ ዛፍ ብቻ በመሆናቸው ስራ ከተሰራ በሁዋላ ዛፎቹም ስለሚቆረጡ መለካቱ ተገቢ አይደለም ብለው ከሳሾች ቢሞግቱ የሚሰማቸው አልነበረም።በሌላ በኩል በሜቴክና ከሳሾች ስምምነት ውስጥም ጂፒኤስ ሳይኖር ማብራሪያ መጠየቁም ተገቢ አልነበረም።ሜቴክ ቀሪ ክፍያውን ላለመክፈል ጂፒኤስን የሙጥኝ ብሏል። ምክንያቱም በጂፒኤስ ስፍራው ላይ ልኬት ሲሰራ የስፋት መጠን በግማሽ ቀንሶም ታይቶ ነበር ።ይሄ ደግሞ ወጪ ይቀንስለታል። ሆኖም ከጂፒኤስና ከሜትር የቱ የተሻለ ይለካል በሚል የተጠየቀው የካርታ ስራዎች ኤጀንሲም ሶስት የተለያየ መልስ ያለው ደብዳቤ  ጽፏል።አንዱ ሜትር ይሻላል የሚል ሁለተኛው ደግሞ በሜትርና በጂፒኤስ እየተለካ ልዩነቱ ናሙና ተወስዶ ሊለካ ይችላል የሚል ነበር።የሚገረመው ሁለቱ ደብዳቤዎች በአንድ ዳይሬክተር ተፈርመው የወጡ ሆነውም በአንድ ችሎት ላይ በማህበራቱና በሜቴክ መቅረቡ ነው።በዚህ የተናደዱት ዳኛዋ እንዴት ለአንድ ጥያቄ ሁለት የተለያየ መልስ በአንድ ዳይሬክተር ተፈርሞ  ይመጣል ብለው የመጨረሻ ጥያቄ ለካርታ ስራዎች ኤጀንሲ ያቀርባሉ ።በዚህ ጊዜ ኤጀንሲው ሁለቱም መለኪያዎች ያው ናቸው የሚል ምላሽን ይሰጣል።

ዳኛዋ ታድያ እዚህ ጋር ተመነጠረ የተባለው የደን ቦታ ከሳሽም ተከሳሽም ባሉበት በሜትር ይለካ የሚል ትእዛዝን ለካርታ ስራዎች ኤጀንሲ ሰጡ። ምልክቶች በጠፉበት ሁኔታ መሬቱን እንደገና መለካት ከሳሾችን ቢጎዳም የካርታ ስራዎች ኤጀንሲ ባለሙያዎች ለመለካት ወደስፍራው ይሄዳሉ። ስፍራውን በሜትር ሲለኩ ታድያ ሜቴክ በማህበራቱ የተመነጠረውን ቦታም ጭምር አንዱን እርሻ ነበር ሌላውን ደግሞ መንደር ነበር እያለ ስላስቸገረ ባለሙያዎቹ ቦታው ድንበር ስለሌለው ሊለካ አይችልም ብለው ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ ያስገባሉ።  ዳኛዋ ህትመት አሰፋ ባለሙያዎቹ መሬቱ አይለካም ካሉ በከሳሾች የክፍያ ምስክር ወረቀት ላይ ተመርኩዘው መወሰን ሲችሉ ፍርድ ከመስጠቴ በፊት ተከሳሾችን በክፍያ ላይ ብቻ ከሜቴክ ጋር ተደራድራችሁ ተስማሙ ይሏቸዋል። ከሳሽ ማህበራቱም አደራዳሪ ተመድቦ ሜቴክን ከወከሉት ኮሎኔል ያሬድ ሀይሉ ከተባሉ ሰው ጋር ሲደራደሩ ኮሎኔሉ በክፍያ ተደራደሩ የተባለውን ትእዛዝ ትተው መሬቱ ሳይለካማ በገንዘብ አንደራደርም ብለዋቸዋል።ነገር ግን የሜቴኩ ተደራዳሪ ቀድመን 29 ሺህ ሄክታር ነው የሰራችሁት ያልናችሁ ቱዲ ጂፒኤስ በተባለ መሳርያ ነው ። እሱ ደግሞ ስህተት ነበረበት ስለዚህ በስሪ ዲ ጂፒኤስ የመነጠራችሁትን ቦታ እንለካ እና በክፍያ እንደራደር ይላቸዋል ለከሳሾች። ይቺ ለከሳሾቹ ማህበራት እጅግ ጠቃሚ መረጃ ነበረች። ምክንያቱ በመጀመርያ ዳኝነት መሬቱ መለካት አይችልም ተብሎ ነበር።አሁን ደግሞ ሜቴክ በጂፒኤስ የለካሁት ተሳስቼ ነው ሲል በራሱ ጊዜ በአደራዳሪዎቹ ፊት አመነ። አደራዳሪዎቹም ቀድሞ በፍርድ ቤት ባልታዘዘ ጉዳይ ድርድሩ ስለተመራ ሂደቱን አቋርጠው መረጃውን ለፍርድ ቤት አቀረቡ።

Abdulaziz Mohamed METEC head

ዳኛ ህትመት አሰፋ ሜቴክ ቀድሞ በጂፒኤስ የለካሁት ስህተት ነበር ማለቱን ብቻ አይተው ለከሳሽ ማህበራቱ መፍረድ ሲችሉ ፍርድ ቤቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል አሉ።ይባስ ብሎም ኤል ኤም ሀት የተባለ የሜቴክ ጥቅም ተጋሪ እንደሆነ የተነገረለት ኩባንያ እንደገና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ መሬቱን ለክቶ እንዲያመጣ ተሰጠው።ህትመት የሚባሉት ዳኛም ተቀይረው ሌላ ዳኛ መጣ።
አዲሱ ኩባንያ በሜትር እየለካ እንኳ ውጤቱ ለአጋሩ ሜቴክ ሳይሆን ለማህበራቱ እያደላ መጣ ።ስለዚህ ቦታው በጂፒኤስ እንጂ በሜትር አይለካም ብሎ ስራውን አቋረጠ።ነገሩ ከሳሾች ላይ ጫና ለመፍጠር ስለሆነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ማብራሪያ ሲጠየቅ ነበር።ዲዲኤም የተባለ መሳርያ የተሻለ መለኪያ እንደሆነም ተነገረ። ይህም መሳርያ ግን በጂፒኤስ የሚሰራ ነው።

ህዳሴ ግድብ የሚሰራበት ቦታ ሄዶ መልካም የተፈጥሮ አቀማመጥ ያለውን ቦታ በሜትር አስቸጋሪውን ደግሞ ዲዲኤም በተባለው መሳርያ ተመነጠረ የተባለውን ስፍራ እንዲለካ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ሱፐርቪዥን የተባለ ድርጅት ታዘዘ በአዲሱ ዳኛ።
በዚህ ድርጅት አሰራር ላይ ብዙ እሰጣገባዎች ቢኖሩም ; በመጨረሻም ባለሙያዎቹ ደን ያለበት ቦታ አንድም በሜትር አይለካም ብለው ሜቴክ ቀድሞ ያቀረበውን 29 ሺህ ሄክታር ነው የተመነጠረው የሚለውን መረጃ ለፍርድ ቤት አቀረቡ። ከሳሽ ማህበራቱ ላይ ፍርድ ቤቱ ፈረደባቸው። ቀሪ ክፍያቸውን ሊያገኙ አይደለም ሜቴክ ቀድሞ ለፍርድ ቤት ባቀረበው መረጃ መሰረት ፍርድ ቤቱ በማህበራቱ የተመነጠረው መሬት 29 ሺህ ሄክታር ነው በሚል ቀድሞም 56 ሺህ ሄክታር መሬት መንጥረናል በሚል ያልተገባ ክፍያ ወስደዋል በሚል ባለ እዳም አደረጋቸው። ፍርዱም እስከ ሰበር ጸንቷል። የማህበራቱ አባላትም በእዳ ተይዘው ችግር ውስጥ አሉ።

በዚህ ሂደት ውስጥ የፍትህ ጥሰትም ተካሂዷል። እነዚህ ደን መንጣሪ ማህበራት የቀጠሯቸው ሌሎች ንኡስ ኮንትራክተሮች አሉ።ዋናዎቹ ማህበራት በክስ ሂደት ውስጥ በመሆናቸው ለበታች ኮንትራክተሮች ገንዘብ አልከፈሏቸውም።በዚህም ምክንያት በተዋረድ ስራውን ያገኙት ማህበራት ሜቴክን የከሰሱትን ማህበራት ይከሷቸዋል።ታዲያ እነዚህ ማህበራት ክሳቸውን ሲያቀርቡ የሜቴክ ከሳሽ ማህበራት 56 ሺህ ሄክታር ሰርተናል የሚለውን መረጃ ይዘው ነው። ሜቴክ ደግሞ የበታች ማህበራት በሌላ ፍርድ ክስ ሲያቀርቡ 56 ሺህ ሄክተር ተሰርቷል የሚለውን መረጃ ደግፎ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። የሜቴክ ከሳሾች ይህንን መረጃ ለፍርድ ቤት አቅርበውም ነው የተፈረደባቸው።

በሜቴክ በደል ተፈፅሞብናል የሚሉት የማህበራቱ መሪዎች የሰራንበት ገንዘብ ይከፈለን ሲሉ እ የተማፀኑ ነው።
የሜቴክ የስራ ሀላፊዎችን ምላሽ ጠይቀን ጉዳዩ በፍርድ ቤት ያለቀ የተወሰነውም እየታየ ያለ በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት ይቸግረናል። እንዲሁም አሁን ያለው አመራር አዲስ በመሆኑና ድርጅቱ በአዲስ መልክ እየተደራጀ በመሆኑ መረጃውን አሰባስበን መናገር አንችልም ሲሉ መልስ ሰጥተውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]