Sheik Al Amoudi-PHOTO FILE

 ዋዜማ ራዲዮ- የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት አድርጎ መሻሻል ስለሚገባቸው አሰራሮችም ተነጋግሯል። በዚሁ ለመገናኛ ብዙሀን ዝግ በነበረ ስብሰባ ላይ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትሩ ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በሚድሮክ ወርቅ ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ ለማንሳት የሚያስችል ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።


እገዳው የሚነሳው ሚድሮክ በአካባቢው አስከትሎታል የተባለውን ብክለት የሚያጠና የተፅዕኖ ግምገማ ቡድን ጥናቱን አጠናቆ በመጨረሱ ነው። ይህ ሳይንሳዊ ጥናት ሚድሮክ አስከትሎታል የተባለው ጉዳት በመብት ተሟጋቾች እንደቀረበው ሳይሆን በአነስተኛ የእርምት እርምጃዎች የሚስተካከል ነው። ድርጅቱ አሳሳቢ የሚባልና የነዋሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳት ስለማድረሱ መረጃ አለመገኘቱንም ከባለሙያዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ሚንስትሩ የጥናት ውጤቱን መደምደሚያ ምን እንደሆነ ግን አልተናገሩም።

ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለሀያ አመታት በተሰጠው ፈቃድ በኦሮምያ ክልል በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ለገደንቢ አካባቢ ሻኪሶ ከተማ አቅራቢያ ወርቅ ሲያመርት ቆይቶ ባለፈው አመት ለተጨማሪ አስር አመታት የማምረት ፈቃዱ በወቅቱ በማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከታደሰለት በሁዋላ የመብት ተሟጋች ነን የሚሉ ግለሰቦች ኩባንያው ወርቅ ለማንጠር የሚጠቀምበት ኬሚካል እጅግ አካባቢን የበከለ ነው በሚል በህዝቡ ላይ ባደረጉት ቅስቀሳ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ተነስቷል።

ይህን ተከትሎም ሚኒስቴሩ በኩባንያው ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ፣የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፣የአካባቢ ጥበቃ ተቋማትና የውጭ ሀገራት  ባለሙያዎች ተካተው የኩባንያው የአካባቢ ብክለት ሁኔታ እስኪጠና ኩባንያው የታደሰለት የወርቅ ምርት ፍቃድ ታግዶ እንዲዘጋ ተደርጓል።

 ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው አሁን በሜድሮክ የወርቅ አምራች ኩባንያ ላይ በባለሙያዎች እየተደረገ ያለው ጥናት ተጠናቋል።ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየውም የሳይንሳዊ ጥናት ባለሙያዎች ቡድኑ ባደረገው ጥናት የሜድሮክ ወርቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉት ግለሰቦች እንደሚሉትና በተወሰኑ መገናኛ ብዙሀን ሲቀርብ እንደነበረው በአካባቢና በሰው ላይ የከፋ ጉዳት አላደረሰም። ኩባንያው ጉዳት አደረሰ ከተባለም ሊስተካከልና ሊካስ የሚችል ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ሰምተናል። የመአድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኩባንያው ፈቃዱ ተመልሶለት ሊከፈት ይችላል የሚል ፍንጭ የሰጡትም ከዚህ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። የሳይንሳዊ ጥናት ባለሙያዎቹ የጥናት ውጤትም በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

 የሜድሮክ ወርቅ ኩባንያ ወርቅ ባመረተባቸው ጊዜያት በተለይ በቅርብ አመታት በአመት ሁለት መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ምንዛሬ ሲያስገኝ ነበር። ሀገሪቱ ከአራት አመታት በፊት ከወርቅ ብቻ ስታገኝ የነበረው ከአምስት መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ምንዛሬ በዚህ በጀት አመት ሌሎች መአድናት ጋር ተዳምሮ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ ቀንሶ ከ30 ሚሊየን ዶላር ብዙም ያልበለጠ ምንዛሬ የተገኘው ሌሎች ምክንያቶች ተዳምረው ሜድሮክ ወርቅ ማእድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመዘጋቱም ነው።

ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም እንደዘገበችው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ሼክ መሀመድ አላሙዲን ከፍተኛ ድርሻ የተያዘው ሜድሮክ ወርቅ ፈቃድ የታገደበት ሁኔታ አወዛጋቢ ነበር። በወርቅ አምራች ኩባንያው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሲቀርቡ የነበሩ ሰዎችን የሳንሳዊ ጥናት ቡድኑ ወደ ስፍራው ሲሄድ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። ሜድሮክ ወርቅ ለማንጠር ሲጠቀምበት የነበረው ሶዲየም ሳናይድ ነው።ይህ ኬሚካል ለአካባቢ ብክለት መንስኤ ነው ቢባልም ማዕድን ሚኒስቴር በሶዲየም ሳናይድ እጥረት ምክንያት ምርት ላቆመውና ትግራይ ላለው ኢዛና ወርቅ ኩባንያ 40 ቶን ሶዲየም ሳናይድ እንዲያበድረው መጠየቁን የሚያሳይ ደብዳቤም አግኝተናል። ይህም ኦሮምያ ውስጥ በካይ ተብሎ የተከለከለ ኬሚካል እንዴት ትግራይ ለሚመረት ወርቅ በምልጃ ተጠየቀ የሚል ጥያቄን አስነስቷል።ሜድሮክ ወርቅ ያለበት ስፍራ ላይ በአለማቀፍ ደረጃ የተከለከለ ሜርኩሪ ጭምር ወርቅ እየተመረተ ሜድሮክ ብቻ የእርምጃ ኢላማ መሆኑም ያልተመለሰ ጥያቄ ነበር።

 የኦሮምያ ክልል ውስጥ አሁን ላይም የህግ የበላይነት ባልመጣበት ሁኔታ የሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ቢከፈት ሌላ የጸጥታ ችግርን አይከስትም ወይ ? የሚል ጥያቄ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ምንጮቻችን ላነሳነው ጥያቄ ; ኩባንያው ሲንቀሳቀስ የነበረበት አካባቢ ከፍተኛ ስራ አጥነት ስላለ ኩባንያው በመከፈቱ ሌላ ችግር ችግር ይኖራል የሚል እምነት እንደሌለ ፣ ነገር ግን ሮያሊቲን ጨምሮ ከ ማዕድን መሰብሰብ ያለባቸውን ገቢዎች በተገቢው መልኩ መሰብሰብ እንደሚገባና መንግስትም የአካባቢውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት አለበት የሚል ምላሽ አግኝተናል። የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ