Lencho Teamዋዜማ ራዲዮ- መንግሥት በሽብርተኝነት ለፈረጃቸው ተቃዋሚ ቡድኖች የሽብርተኝነት ፍረጃውን በማንሳት ትልቅ ርምጃ ወስዷል፡፡ ጸረ-ሽብር ሕግ አንስቶ የምህረት አዋጅ አጽድቋል፡፡ ይህንኑ ርምጃ ተከትሎ በሽብር ተከሰው የነበሩ ፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ብሄርተኞች የክልልነት፣ የሙስሊም መብት ተሟጋቾች ደሞ ነባር ጥያቄያቸውን እያሰሙ ያሉት ለውጡን ለመጠቀም ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ በውጭ ሀገራት ያሉ የተቃራኒ ፖለቲካ ቡድኖች ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር መግባታቸውን በበጎ የሚያዩት እንዳሉ ሁሉ በስጋት የሚያዩትም ወገኖች አልጠፉም፡፡ እናም ቡድኖቹ ተቃራኒ ፍላጎቶቻቸውን እና ፖለቲካዊ አጀንዳዎቻቸውን በምን መልኩ ያንጸባርቁ ይሆን? ቡድኖቹ ባንድ ጊዜ መሰባሰባቸው ለሀገሪቷ ምን ዐይነት ትሩፋት እና ስጋት ይፈጥር ይሆን? ሁኔታው በጠቅላላው ምን ዐይነት ቅራኔዎችን እና ግጭቶችን ሊፈጠር ይችላል? [በድምፅ የተሰናዳውን ዝርዝር ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

* * *

አንተም ና! አንተም ና!

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እየወሰዷቸው ያሉት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ አድናቆትን አትረፈውላቸዋል፡፡ በርግጥም ፖለቲካዊ ምህዳሩን በሰፊው እየከፈቱት መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ሀገሪቱ ወደ ማይቀለበስ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እየገባች ስለመሆኗ ብዙዎች ዕምነት አሳድረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ትልቅ ትኩረት የሳበው አንዱ መሠረታዊ ከስተት በውጭ ሀገራት ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር መግባት መቀጠላቸው ነው፡፡ አንዱ የፖለቲካ ቡድን የሌላኛውን ውሳኔ እየሰማ ተመሳሳይ ውሳኔ እየደረሰ በመሆኑ አፈንጋጭ አቋም የሚቀር አንድም ድርጅት ያለ አይመስልም፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን የትሩፋቱን ያህል ስጋት መደቀኑም አልቀረም፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት በውጭ ሀገራት ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖች ወደ ሀገር እንዲገቡ ጥሪ በማድረግ ኦሕዴድ የመጀመሪያው ነበር፡፡ ብአዴንም በቅርቡ ተከትሏል፡፡ በርግጥ ይሄ ለሀገሪቱ የራሱ አወንታዊ አስተዋጽዖ አለው፡፡

በኦሕዴድ ጥሪ መሠረት ቀድሞ የገባው የሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሲሆን በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ወደ ሀገሩ እንደሚመለስ ተናግሯል፡፡ በግለሰብ ደረጃም እነ ዮናታን ድቤሳን የመሳሰሉ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች ተመልሰዋል፡፡ በቅርቡም ከኦነግ አንጃ የሆነው የተባበሩት ኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚባል ከኦነግ የተገነጠለ አንጃ የገባ ሲሆን ሌላኛውን የኦነግ አንጃ የሚመሩት የጄኔራል ከማል ገልቹም ተመልሰዋል፡፡

ከሕብረ ብሄራዊ ሃይሎች መካከል ደሞ አርበኞች ግንቦት 7 ትጥቅ ትግሉን ያቆመ ሲሆን፣ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካው በቅርቡ እንደሚመለስ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡ በአማራ ብሄር ስም የተደራጁትም ሆኑ በአረጋዊ በርሄ የሚመራው የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር እንዲሁ በሀገር ቤት ሆነው ለመታገል ወስነዋል። በተራዘመ ነፍጥ ትግሉ የሚታወቀው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር እንኳ ለውጡን በአወንታዊነት እንደሚቀበለው ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ዶክተር ካሳ ከበደም እንዲሁ ለውጡን ደግፈው አስተዋጽዖ ለማድረግ ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡

አንዳንዶቹ ገና በቅርቡ በነፍጥ መታገላችን ትተናል ያሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደሞ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ አክራሪ ብሄርተኞች ሲሆኑ የመገንጠል መብትን በሃይልም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ለማሳካት ሲታገሉ የኖሩ እና ቀደም ሲልም ሕዝቦችን ለቅራኔ እና ግጭት የዳረጉ ሃይሎች ጭምር “እኛም ለመደመር ልንመጣ ነው” ባይ ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው የአንድነት አቀንቃኝ ሃይሎችም አሉ፡፡

በአቋም ረገድ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ለውጥ “በጣም ፈጠነ፣ በቂ ጥናት አልተደረገበትም፤ የሚመለከታቸው ወገኖችም አልተሳፉበትም” የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል በተቃራኒው አዝጋሚ የሆነባቸው አሉ፡፡ ለውጡ ጥገናዊ እና አዝጋሚ መሆኑን የሚደግፉ ሃይሎች ባንድ በኩል ሲኖሩ በሌላ በኩል ደሞ “ስር ነቀል ለውጥ ካልመጣ ምን ዋጋ አለው?” የሚሉም አልጠፉም፡፡ “ለውጡ ከውጭ ሃይሎች ቢመጣ ይሻል ነበር” የሚሉ እና “የለም፣ ከራሱ ከገዥው ድርጅት መምጣቱ ለሀገሪቱ አንድነት እና ሕልውና መረጋገጥ ጠቃሚ ነው” የሚሉ አመለካከቶችም ይንጸባረቃሉ፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩን የይቅር ባይነት፣ ምህረት እና የአንድነት ትርክት ከምር የሚወዱ አሉ፡፡ ሌሎች ደሞ ለጊዜው አንገታቸውን ቢደፉም ከመጠን በላይ የተለጠጠ እና ፖለቲካዊ የዋህነት የበዛበት መሆኑን የሚያመኑ አሉበት፡፡

በጠቅላላው የፖለቲካ ቡድኖቹም ሆኑ አስተሳሰቦች ስር የሰደደ ተቃርኖ ያላቸው እና ቡድኖቹም ተጻራሪ ግቦችን የያዙ ናቸው፡፡

ቦሌ ከደረሱ በኋላስ?

በሌላ በኩል መንግሥት ጥሪውን ያደረገው በቂ የፖለቲካ እና ሕጋዊ ማዕቀፍ ዝግጅት ሳያደርግ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ተቃራኒ ቡድኖች እንዴት አድርጎ እንደሚያስተናግዳቸው ግልጽ አይደለም፡፡ በርግጥ መንግስት ጥቂት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን ወስዷል፡፡ መዋቅራዊ፣ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ግን ገና ይቀራሉ፡፡ ሕገ መንግስታዊ ተቋማት ገና ደካማ ከመሆናቸው በላይ ስር የሰደደ የገለልተኝነት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡

በተለይ አንገብጋቢ የሆነው የጸጥታ ተቋማት ተቋማዊና መዋቅራዊ ማሻሻያ ገና አልተሞከረም፡፡ ቢታሰብም ገና ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ እናም አሁን ተቋማቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ ስለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ ስለሌለ ሕዝቡም ሆነ ወደ ሀገር የሚመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች “ጸጥታ ሃይሎች አጋሮቻችን ናቸው፤ የሀገሪቱ እና ሕገ መንግስቷ እንጅ የገዥው ኢሕአዴግ ጠበቃ አይደሉም” ብለው ለማመን የሚችሉበት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ ምናልባት ቢያንስ የጸጥታ ተቋማቱ ሃላፊዎች በተለይም የጦር ሠራዊቱ አዛዦች ከፓርቲ ፖለቲካ ፍጹም ገለልተኛ መሆናቸውን፣ በሕገ መንግስቱ እና ሕዝቡ ፊት ድጋሚ ቃል ኪዳን ቢገቡ ትንሽ አመኔታ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፡፡

ሌላው ነጥብ የፖለቲካ ቡድኖቹ ምህዳሩን ሊቆጣጠሩ የሚያቆበቁቡት ጠንካራ ሲቪክ ማህበራት እና መገናኛ ብዙሃን በሌሉበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ አካላት አወንታዊ ሚና ሳይኖራቸው ደሞ ዘላቂ ዲሞክራሲ ሊሰፍን አይችልም፡፡

ዐብይ ምን አላቸው?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እነዚህን ሁሉ ተመላሽ ተቃዋሚ ቡድኖችን እየተቀበሉ ሲያነጋግሩ ምንድነው ቃል ነው የገቡላቸው ? በመንግሥት ወይም ድርጅት ደረጃ የተያዙ አቋሞችስ አሉ ወይ? የየቡድኖቹ መሪዎችስ ምን ቅድመ ሁኔታዎች ነው እያስቀመጡ ያሉት? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ከመንግሥት በቂ መልስ የለም፡፡ “መደመር” የሚባለውን ቃል ያመጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሆኑም ቀስ በቀስ ግን የመንግሥት ኦፊሴላዊ ፍልስፍና ሆኗል፡፡ በፖለቲካዊ ትርጓሜው ዙሪያ ግን ሰፊ ብዥታ ነው ያለው፡፡

የገዥው ድርጅት ኢሕአዴግ ውስጣዊ ክፍፍም እየተባባሰ ነው የመጣው፡፡ ባንድ በኩል የኦሕዴድ እና ብአዴን የበላይ አመራሮች የለውጡ አቀንቃኝ እና ጠባቂ ሆነዋል፡፡ ሕወሃት አኩራፊ ከሆነ ወዲህ ጠቅላይ ሚንስትሩ እየወሰዷቸው ባሉ ፖለቲካዊ ማሻሻዎች እና ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ጥሪ በተደረገላቸው ብዙዎቹ የፖለቲካ ቡድኖች ደስተኛ አለመሆኑን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲገልጽ ይሰማል፡፡ ለለውጡ የሚደረጉ ድጋፍ ሰልፎች ደሞ የበለጠ ወደ ዳር ሲገፉት እየታየ ነው፡፡ አኩራፊ የሕወሃት አንጃዎች የሕዝብን ሰላም ለመንሳት እና ጸጥታ ሃይሉም እንዳይረጋ ለማድረግ እንደቆረጡ ጠቅላይ ሚንስትሩም ቢሆኑ በይፋ አምነዋል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ አሁን የኢሕአዴግ ድርጅታዊ እና ፖለቲካዊ ቁመና ተዳክሟል፡፡ አሁን እየተፈጠሩ ያሉትን ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ክስተቶች በሆደ ሰፊነት ማስተናገድ የሚያስችል ውስጣዊ ድርጅታዊ አንድነት እና ዲስፕሊን የለውም፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ደሞ ወደፊትም በለውጥ ሃይሎች እና አኩራፊ ሃይሎች መካከል ውስጣዊ ትግሉን በማባባስ የድርጅቱን ሕልውና ሳይቀር ችግር ውስጥ ሊጥለው ይችላል፡፡

በፌደራል እና ክልል ደረጃ ከሹመታቸው እየተሻሩ፣ እየተባረሩ ወይም እየታሰሩ ያሉ የጸጥታ ሃይሉ አባላት እና ፖለቲከኞችም ቢሆኑ ለአጭር ጊዜ ጸረ-ለውጥ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ የብሄር-ተኮሩ ሥርዓት እና የኢሕአዴግ መዋቅር ደሞ በባህሪው ለአፍራሸ ተልዕኮ እና አሻጥር ምቹነት አለው፡፡

የነገ ስጋቶች

ይህን ካልን በኋላ እንግዲህ ተጻራሪ ቡድኖቸ ባንድ ጊዜ ሀገር ውስጥ መክተታቸው ምን ፖለቲካዊ አንድምታ አለው? የሚለው ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ቡድኖቹ እና አስተሳሰቦች ስብጥር ሲታይ በርግጥም ኢትዮጵያ ማዕበል ሊፈጥር ወደሚችል የፖለቲካ ባህር እየገባች መሆኗን መታዘብ ይቻላል፡፡ ተቃራኒ ቡድናዊ ፍላጎቶች መንግስትን እና ሀገሪቱን ሰንገው የመያዛቸው ነገርም በቅርቡ የሚከሰት ይመስላል፡፡ ይሄም ፖለቲካዊ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንዳንዶች መጭውን ማዕበል የሚጠበቅ እና ጊዜያዊ “ፖለቲካዊ ናዳ” አድርገው ሊቆጥሩት ይችላሉ፡፡ ለሌሎች ደሞ “አርማጌዶን” ሆኖ እንደሚታያቸው ካሁኑ ግልጽ ሆኗል፡፡

ይህን ስጋት መነሻ በማድረግም ወደፊት ዐይነት ፖለቲካዊ ቅራኔች እና ግጭቶች ይፈጠሩ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ከወዲሁ የቢሆን ታሳቢ መላ ምቶችን ማስቀመጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ ወሳኝ ፖለቲካዊ ክስተቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ነገ ከነገ ወዲያ ምን ታሳቢ ሁኔታዎች ሊመጡ እንደሚችሉ አስቀድሞ መተንበይ እንደሆነ በፖለቲካ የነበረና ያለ ነው፡፡ ታሳቢ ተቃርኖዎች እና ግጭቶች ሁለት መስክ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡

አንደኛው፣ የግጭት መስክ በመንግስት እና በፖለቲካ ቡድኖቹ መካከል ሊፈጠር የሚችለው ተዋረዳዊ ግጭት ነው፡፡ በርግጥም ይሄ የግጭት መስክ የመፈጠር ዕድሉ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ለውጥ ደገፊ የሚመስሉ አክራሪ ብሄርተኛ ቡድኖች ነገ ከነገ ወዲያ ፖለቲካዊ አደጋ የሚደቅኑበት ዕድል አለ፡፡

አንዳንዶቹ ብሄርተኞች የሀገሪቱን ነባር ተቋማት እና ብሄራዊ ምልክቶች አምርረው የሚጠሉ ናቸው፡፡ ባንዲራ እንኳ ካሁኑ ዋነኛ የውዝግብ እና ቅራኔ መስክ መሆን ጀምሯል፡፡

ከአንድነት ሃይሎችም ተቃራኒው ስጋት ሊመጣ ይችላል፡፡ እውነት መንግስት ትናንት ነፍጥ አንስተው ሲዋጉት ከነበሩ ድርጅቶች ጋር ለመስራት ሙሉ ስምምነት እና ዝግጁነት አለው ወይ? ቢባል ገና ብዙ አጠራጣሪ ሁኔታዎች እንዳሉ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡

መንግስትም ሆነ ኢሕአዴግ ለዐመታት ቀውስ ውስጥ ስለከረሙ ገና ውስጣዊ የሃሳብ አንድነትም ሆነ ዝግጁነተ የላቸውም፡፡ እንዲህ ያሉ፣ በሁለት ጫፍ የቆሙ አስተሳሰቦችን መሸከም እና ማስተናገድ የሚችሉበት ተቋማዊ እና ፖለቲካዊ ጡንቻ አላዳበሩም፡፡ በዚሀ ሁኔታ ደሞ መንግስት ውሎ አድሮ ወደ አምባገነንነት ሊመለስ የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም፡፡

መንግስታዊ ተቋማት እና ኢሕአዴግ በቡድናዊ ጫና ከተዳከሙ ደሞ የሀገሪቱ ሕልውና ለአደጋ መጋለጡ አይቀሬ ነው የሚሆነው፡፡

ሁለተኛው፣ የግጭት መስክ በተለያዩ ቡድኖች መካከል ሊፈጠር የሚችለው ተዋረዳዊ ቅራኔ እና ግጭት ነው፡፡ ለ27 ዐመታት በመንግስት እና ተቃዋሚዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ወገኖች መካከል ያለው የአግድሞሽ ተቃርኖ ራሱ ስር የሰደደ ነው፡፡ ለዚህ የግጭት መስክ አስተዋጽዖ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ እንግዲህ በመካከላቸው ያለው የብሄር እና አስተሳሰብ ልዩነት ነው፡፡

በተለይ የአንድነት ሃይሎች እና ብሄርተኛ ሃይሎች እንዴት ሊስመማሙ እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በብሄርተኛ ሃይሎች መካከልም አክራሪ ተገንጣይ ሃይሎች እና በኢትዮጵያ አንድነት ማዐቀፍ የላቁ የብሄረሰብ መብቶችን መጎናጸፍ የሚፈልጉ ሃይሎች ቅራኔ ውሰጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ ንዑስ ቅራኔዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡

በርግጥ የርዕዮት ልዩነቱ በራሱ ቡድናዊ ቅራኔና ግጭት ላይቀሰቅስ ይችላል፡፡ የየድርጅቶቹ ዜሮ ድምር ፖለቲካዊ ባህል እና ብሄር-ተኮሩ ሥርዓት የፈጠራቸው ቁርሾዎች ግን ለቡድናዊ ግጭት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ መረሳት የለበትም፡፡ ብዙዎቹ ቡድኖች ለዐመታት ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተነጥለው የኖሩ ናቸው፡፡ “አስተማማኝ ሕዝባዊ መሰረት አለኝ” ብሎ አፉን ሞልቶ ሊናገር የሚችል ድርጅትም ያለ አይመስለንም፡፡ አብዛኛዎቹ በሀገር ውስጥ ሰላማዊ እና ሕጋዊ የተቃውሞ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አልነበራቸውም፡፡ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፉክክርን፣ ሕዝብ ማንቃት እና ማደራጀትን በኩል ያላቸው ፖለቲካዊ እና ድርጅታዊ ዲስፕሊን ገና በተግባር አልተፈተነም፡፡

በተለይ በብሄር የተደራጁ ቡደኖች ማንኛውንም ጉዳይ ወደ ከማንነት ጋር በማያያዝ ማጦዝ እንጅ እምብዛም ለመርህ ተገዥ የመሆን ልምድ የላቸውም፡፡ እንዲህ ያሉ እጥረቶች ያባቸው ቡድኖች ባቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ወይም ሕዝባዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ቡድናዊ እና ብሄር ግጭትን ወደመቀስቀስ ሊያዘነብሉ ይችላሉ፡፡ በሀገሪቱ ሰፈኖ የኖረው ጠባብነት፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት እና የተዛባ የፖለቲካ እና የታሪክ ቁርሾ ደሞ እንዲህ ያሉ ቡድኖች አሉታዊ ፖለቲካን እንዲያቀጣጥሉ ምቹ ይሆንላቸዋል፡፡

በኦነግ እና በአንድነት ሃይሎች መካከል ያለው የታሪክ አረዳድ ይቅርና በኦነግ እና በሌሎች የኦሮሞ ብሄር ድርጅቶች መካከል ያሉ ሰፊ ልዩነቶችን ጎን ለጎን እንዲንጸባረቁ ለማድረግ የሚያስችል ሀገራዊ እና ድርጀታዊ ፖለቲካዊ እሴት አልተገነባም፡፡

ይሄ የቅራኔ መስክ በራሱ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከልም ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ባንድ በኩል ምናልባት ኦሕዴድ እና ብአዴን በውጭ ላሉ ተቃዋሚዎቻቸው ጥሪ ማድረጋቸው የተቃውሞ ፖለቲካውን ወደ ጎን እየተው፣ የየራሳቸውን ብሄርተኝነት የሚያጠናከር ፖለቲካዊ አሰላለፍ የመያዝ እሽቅድድም ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይሄ ደሞ ወደ ብሄር-ተኮር ቅራኔ እና የሥልጣን ሽኩቻ ሊያመራ ይችላል፡፡ ሌላው እንደ ኦነግ እና አርበኞች ግንቦት 7 ያሉ ድርጅቶች ወደ ሀገር መመለሳቸው ሕወሃትን፣ እንዲሁም በተወሰኑ የኦሕዴድ እና ብአዴን አመራሮች ላይ ቅሬታ መፍጠሩ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ በኦነግ መመለስ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን እና በአማራ ብሄር ስም የተደራጁትን ማስቆጣቱ ስለማይቀር ቡድናዊ መተነኳኮስ እና ቁርሾን የማወራረድ ሙከራዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የአብዮቱ ማግስት ቀውስ ይደገም ይሆን?

ባጠቃላይ ሁኔታው የ1966ቱን ቡድናዊ ትርምስ ይመልስብን ይሆን? የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች ቀላል አይደሉም፡፡ በ66ቱ አብዮት በውጭ ሀገራት የነበሩ ተማሪዎች እና ምሁራን ያቋቋሟቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ሀገራዊ ስረ መሠረት የሌለውን ግራ ዘመም ርዕዮተ ዐለማቸውን በመያዝ ነበር በይፋ እና በሕቡዕ ወደ ሀገር የገቡት፡፡ ወዲያውኑ ግን ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሰደድ፣ ኢማሌዲህ፣ ወዝ ሊግ፣ ኢጭአት ወዘተ የተባሉት ቡድኖች ርስበርስ ወደ መጠፋፋት አዘነበሉ፡፡ ወታደራዊው ደርግም ቡድናዊ ሽኩቻው እና ትርምሱ የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሥልጣኑን ተቆጣጠረ፤ የሕዝባዊ መንግስት ምስረታ ጥያቄውን አከሸው፡፡ የበላይነቱንም ለመያዝም ሀገር ዐቀፍ ሽብር አውጆ እስካሁን አሻራውና መዘዙ ያላላቀ ዕልቂት አድርሷል፡፡

ዛሬም ተመሳሳይ የፖለቲካ አሰላለፍ እያየን ነው፡፡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ለውጥ ለመደገፍ የዘመናችን መኢሶኖችን ከውጭ ሀገራት እየጎረፉ ነው፡፡ “ጥገናዊ ለውጥ ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉን ዐቀፍ ድርድር ይደረግና ነጻ ምርጫ ይካሄድ” የሚል አላማ ያነገቡ ዳግማዊ ኢሕአፓዎችም ይታያሉ፡፡ ሕወሃት በበኩሉ የውስጥ ቀልባሽ አንጃ ወደመሆን አዘንብሏል፡፡ አብዛኛዎቹ ከ66ቱ በተቃራኒ በብሄር እና ቋንቋ የተደራጁ መሆናቸው ደሞ የአሁኑን ስጋት የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ላሁኑ ድሎቹ የበቃው አንድም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራር ሳይሰጠው ነበር፡፡ አሁን የሚታውን ክስተት እንደ ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት ካየነው እውነትም ሕዝቡ ብቁ ድርጅታዊ አመራር የሚፈልገው አሁን ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ ግን ወደ ሀገር እየተመለሱ ያሉት ቡድኖች ቀድመወ የተደራጁ እንጅ ከጸረ-መንግሥቱ ሕዝባዊ ተቃውሞ ማህጸን የተገኙ አይደሉም፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ በስተቀር አዲስ የተፈጠረ ተቃዋሚ ድርጅት የለም፡፡ ይሄ ደሞ ሕዝቡ እስካሁን ያገኛቸውን ፖለቲካዊ ድሎች ከምር ለማይወክሉት መጤ ተቃዋሚ ቡድኖች እንዲሁም ብልጣብልጥ እና ብሄርተኛ ፖለቲከኞች አሳልፎ ሊሰጥ የሚችልበትን ዕድል ያሰፋዋል፡፡

አሁን የለውጡ ባለቤት ኢሕአዴግ ሲሆን የፖለቲካ ቡድኖች ግን ለጊዜው የዳር ተመልካች እና አዳናቂ ብቻ ነው የሆኑት፡፡ ጸረ-መንግሥት ተቃውሞውን ያቆመው ሕዝብም የለውጡ ባለቤት የሚሆንበት ዕድል በጣም ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ እናም ሕዝቡ ላለፉት ሦስት ዐመታት ያነሳቸው የሥራ አጥነት፣ ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና ዲሞክራሲ ጥያቄዎ ሳይመለሱ በቡድናዊ ፍትጊያ ተቀብረው እንዳይቀሩ ስጋት ይፈጥራል፡፡

ሌላው አንድምታ መጤዎቹ እምቅ የአመራር እና ገንዘብ አቅማቸውን ተጠቅመው ሀገር በቀል የሆኑ ተቃዋሚዎችን ሊደፍቁ የሚችሉበት ዕድል መኖሩ ነው፡፡ ይሄም ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር የራሱ አሉታዊ ጎን አለው፡፡

በ1983 ዓ.ም የሀገራችን ወርቃማ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር ዕድል ባክኖ የቀረው የሽግግር ሂደቱ በብሄር ብቻ የተደራጁ ቡድኖች ስለተቆጣጠሩት ነበር፡፡ ዛሬም ግን በጣም ተፈላጊ የሆኑት ሕብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አስተሳሰቦች አላቆጠቆጡም፡፡ እናም ሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የብሄርተኛ ቡድኖች አውድማ ልትሆን ቋፍ ላይ ደርሳለች፡፡ ምናልባትም ብሄርን ማዕከል ወዳደረገ ቡደናዊ ቅራኔ እና ግጭት ለመግባት ዳዴ እያለች እንደሆነም ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ግጭት ባይነሳ እንኳ ብሄርተኛ ቡድኖች ከብሄር-ተኮሩ ሥርዓት ለብሄረሰባቸውና ለራሳቸው የላቀ ትርፍ ለማጋበስ ካልሆነ በስተቀር እኩልነት እና ዲሞክራሲ ለሚያሰፍን ሥርዓታዊ ለውጥ ይታገላሉ ተብሎ ስለማይጠበቅ የተናፈቀው ዲሞክራሲ ደሞ ሌላ ትግል ሊጠይቅ የሚችልበት ዕድል እንዳለ መረዳት አያዳግትም፡፡[በድምፅ የተሰናዳውን ዝርዝር ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/wkaIcdcjJso