ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮ ቴሌ ኮም እነ ዋትሳፕና ሚሴንጀር መሰል ማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ልዩ ታሪፍ ከማውጣት እስከ መዝጋት የሚያስችለውን የቴክኖሎጆ መሳሪያ ግዥ መፈፀሙን ዋዜማ ራዲዮ ጉዳዩን ከሚያውቁ ምንጮች አረጋግጣለች።

እንዳሰባሰብነው መረጃ ፣ ኢትዮ ቴሌ ኮም እንደ ዋትሳፕ : ሚሴንጀር : ቫይበር : ኢሞ : ዊቻትና ቴሌግራም አይነት የኢንተርኔት መገናኛዎች አጠቃቀም ላይ የተለየ ታሪፍ ለመጣልና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እነዚህ መተግበሪያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ለመዝጋት የሚያስችለውን የቴሌ ኮም ሲስተም ለመዘርጋት ያሰበው ከሁለት አመት በፊት ጀምሮ ነበር።ሆኖም በወቅቱ ባጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከመሳርያው አቅራቢ ኩባንያ ጋር ተነጋግሮ ቢጨርስም  ግዥው ዘግይቷል።

አሁን ግን ኩባንያው የውጭ ምንዛሬ በማግኘቱ ግዥውን ፈጽሟል።የማህበራዊ ሚዲያዎቹን መተግበሪያ ከታሪፍ ጀምሮ ለመቆጣጠር የሚያስችለው መሳርያ ወይንም ስርአት ; policy charging rule function and traffic detection function, pcrf/tdf ; የሚባል ሲሆን አቅራቢው ደግሞ ዋና መቀመጫውን ጀርመን ያደረገ ባይት የተባለ ኩባንያ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም በዋነኝነት ይሄንን የቁጥጥር ስርአት ለመዘርጋት የፈለገው ከአለማቀፍ ጥሪ ያገኘው የነበረው ገቢ በቢሊየን ብሮች እየቀነሰበት በመምጣቱ ነው። እንደ ዋትሳፕ :ቫይበርና ሚሴንጀር አይነት መተግበሪያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው ጥቅም ላይ መዋል ከጀመሩ በሁዋላ ዜጎች በቀላሉ ውጭ ሀገር ካሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ወይንም የስራ አጋሮቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል። ይህም የቴሌን መደበኛ አገልግሎት ለአለማቀፍ ጥሪ የሚጠቀሙ ደንበኞችን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶታል።

እንደ ዋትሳፕ ያሉ መተግበሪያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውሉ ኢትዮ ቴሌኮም የሰራቸውን መሰረተ ልማቶች ተጠቅመው ነው የሚሰሩት። በዚህም በተለያየ ሀገር እንደታየው የመተግበሪያዎቹ ባለቤቶች ገንዘባቸውን በተለያየ መልኩ ያገኙታል። ኢትዮ ቴሌ ኮም ከዚህ የሚያገኘው ታድያ የመተግበሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ኢንተርኔት ኮኔክሽን/አገልግሎት ስለከፈቱ ብቻ ነው። ይሄ ደግሞ መተግበሪያዎቹ የአለማቀፍ ጥሪ ገቢዬንም ቀንሰው የሰራሁትን መሰረተልማት ተጠቅመውም የሚገባኝን ጥቅም እንዳላገኝ አድርገውኛል ብሎ ኩባንያው አስቧል።

ስለዚህም በምጽሀረ ቃሉ pcrf/tdf የተባለው ስርአት የማህበራዊ ሚዲያ የድምፅና የፅሁፍ አገልግሎት መተግበሪያዎችን የተለየ የአገልግሎት አከፋፈል ስርአት /special tariff zone/ ውስጥ እየጨመረ ከኢንተርኔት ኮኔክሽን ባሻገር የተወሰነ ክፍያ እንዲጠየቁ እንደሚያደርግ ከኩባንያዎቹ ምንጮቻችን ሰምተናል።

ስርአቱ መተግበሪያዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሩ የማድረግ አቅምንም ለኢትዮ ቴሌ ኮም ይፈጥርለታል።ሀገራት እንደዋትሳፕ ያሉ መተግበሪያዎች በተመሳሳይ ስርአት ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች መነሻነት በግዛታቸው ውስጥ እንዳይሰሩ ሲያደረጉ ታይቷል።የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የማድረግ አላማ ይኑረው አይኑረው ለጊዜው ያገኘነው መረጃ  የለም።

pcrf/tdf የተባለውን ስርአት በኢትዮጵያ የቴሌ ኮም ሲስተም ውስጥ ለመዘርጋት ከ10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ ግዥ መፈጸሙንም ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ መረዳት ችላለች።
በሌላ በኩል የቁጥጥር ስርአቱ የኢንተርኔት አቅርቦትን እንደተጠቃሚዎች የሚጠቀሙበት ዘርፍ አስፈላጊት ፍጥነት ለመገደብ ያስችለኛል ብሏል የቴሌኮም ኩባንያው።
እንዲሁም ኩባንያው መቆጣጠር ያቃተውን በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎች በኢትዮጵያ ቁጥር እየተጠቀሙ ሀገር ውስጥ የሚደውሉበትን የቴሌኮም ማጭበርበርን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠር እንደሚያስችለው አምኗል።ኩባንያው በዚህ ማጭበርበር ብዙ ገቢ እያጣ መሆኑን ሲናገር ቆይቷል።

የተጨመረ– ኢትዮ ቴሌኮም ዘገባችን ከወጣ 10 ስዓታት በኋላ በትዊተር ገፁ በሰጠው ምላሽ፣ የተባለውን ቴክኖሎጂ ለመግዛት ተዘጋጅቶ እንደነበር ይሁንና በመጨረሻ ሰዓት በተፈጠረ የግዥ ስነምግባር ጉድለት ግዥው መሰረዙን ገልጿል። [ዋዜማ ራዲዮ]