Abiy Ahmed with world Bank President David R. Malpass- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የአለም ባንክ ኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚል ቀርጻ እተገብረዋለሁ ላለችው መርሀ ግብር እሰጠዋለሁ ብሎ ቃል የገባው ሁለት ቢሊየን ዶላር ያህል ብድርና ድጎማ መስተጓጐል ከገጠመው በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ከባንኩ ጋር ለመወያየት ጥያቄ ማቅረቡን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።


የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው ጥሪ በጥቅሉ በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አተገባበር ዙርያ ለመነጋገር እንደሆነም ተገልጿል። የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ እተገብረዋለሁ ያለችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በፍጥነት አልተገበረችም በሚል ስበብ ሀገሪቱ ቃል የተገባላትን ገንዘብ በወቅቱ እንዳታገኝ አድርጓል። እርምጃው ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በያዘችው አቋም ሳቢያ የተወሰደ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን የሚናገሩ አሉ።


ባንኩ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል የገባውን ብድርና ድጋፍ ማጠፉን አስመልክቶ ዋዜማ ራዲዮ ላወጣችው ዘገባ የዓለም ባንክ ከቀናት በፊት ምላሽ ሰጥቷል። ሆኖም የባንኩ አጭር የፅሁፍ መግለጫ መረጃዎችን ያስተባበለ ሳይሆን በደፈናው ባንኩ የኢትዮጵያን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በቅርበት መደገፍ ይቀጥላል የሚል ነው።


የዓለም ባንክ ለስብዓዊ ዕርዳታ በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያቀርበው ድጋፍ ባለፉት ወራት ከዓለም ባንክ እንደተለቀቀ የባንኩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁንና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን ለመደገፍ ቃል የተገባው ብድር ድጋፉን ለሚያፀድቀው የባንኩ ቦርድ እንዳይቀርብ መስተጓጎሉን ዋሽንግተን ካለው የባንኩ ዋና መስሪያቤት ምንጮች ስምተናል።


የኢትዮጵያ መንግስት አደርገዋለሁ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በሀገር ቤት ካለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ባሻገር በተደረጉ የተለያዩ ምክክሮች የማሻሻያ ዕቅዶቹ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ በባለሙያዎች ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። መንግስትም የባለሙያዎችን አስተያየት ተከትሎ ዕቅዱን የመከለስና የማዘግየት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል።


አንድ የባንኩ የግምገማ ሪፖርት ሰነድ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውታል ብሎ ያምናል። ባንኩ ባለው ግምገማ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለውን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር ዕቅድ በአግባቡ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም።

የፋይናንስ ዘርፉን ለገበያ ክፍት የማድረግና የመንግስትን ቁጥጥር በማላላት በኩልም ያለው እንቅስቃሴ ከጅምር ያለፈ አይደለም። ይልቁንም የማሻሻያ እርምጃውን ተግባራዊ ያለማድረግ አዝማሚያ ታይቶበታል። በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ቁልፍ ተዋናይ የሆኑት የመንግስት ባንኮች ድርሻ በሂደት በግል ባንኮች እንዲተካ የማድረጉ ሂደት ገና አልተጀመረም። መንግስት የግል ባንኮች ላይ የውጪ ኢንቨስተሮች እንዲሳተፉበት የሚያስችል ማሻሻያ አላደረገም። [ዋዜማ ራዲዮ]