ከመመሪያው በፊት የተገዙና በግዥ ሂደት ላይ የነበሩትን አይመለከትም ብሏል።

Photo SM

ዋዜማ ራዲዮ- ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ሀገር ውስጥ ሲገቡ እንዲቀር የተደረገው 30 በመቶ የእርጅና ግብር ቅነሳ መመርያው ከመውጣቱ በፊት ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ትእዛዝ የተሰጠባቸውን እንደማይመለከት የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።


ግንቦት 7 ቀን 2011 አ.ም በገቢዎች ሚኒስቴር ጸድቆ በጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 14 2011 አ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ የወጣው መመሪያ ፣ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ያገለገሉ እቃዎች ከውጭ ሀገር ተገዝተው ሲገቡ ከምርቶቹ ዋና ዋጋ ላይ እስከ 30 በመቶ እየተቀነሰ የሚሰላው የእርጅና ግብር እንዲቀር ማድረጉን ዋዜማ ዘግባ ነበር።

መመሪያው ይውጣ እንጂ አፈጻጸሙ ላይ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ። ከዚህ ውስጥ ተሽከርካሪን ጨምሮ ያገለገሉ እቃዎች የእርጅና ግብር ቅነሳ ሲቀር መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ግዥ ተፈጽሞባቸው ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዙ ያሉና ለመጓጓዝ ዝግጁ የሆኑ እቃዎች እንዴት ነው የሚታዩት የሚለው አንዱ ነበር።


የገቢዎች ሚኒስቴር ይሄን ብዥታ ያጠራል ያለውን ተጨማሪ መመሪያ አውጥቶ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2011 አ.ም በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ለጉምሩክ አስፈጻሚ አካላት አሰራጭቷል።


ተጨማሪ መመሪያውም ፣ ተሽከርካሪን ጨምሮ ላገለገሉ እቃዎች እንዲቀር የተወሰነው የእርጅና ግብር ቅናሽ የመጀመርያው መመሪያ ግንቦት 7 ቀን 2011 አ.ም ከመውጣቱ በፊት ፣ የባንክ ፈቃድ ማረጋገጫ ያገኙ ያገለገሉ እቃዎችን እንዲሁም ያለውጭ ምንዛሬ ክፍያ ተገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የተጫኑ ያገለገሉ እቃዎችን አይመለከትም። ይህም መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ሀገር ውስጥ እንዲገቡ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ተሽከርካሪዎን ጨምሮ ያገለገሉ እቃዎች ቀረጥ የሚከፍሉት ቀድሞ በነበረው መመሪያ ወይንም የእርጅና ቀረጥ ቅናሽን በሚፈቅደው መመሪያ የሚስተናገዱ ይሆናል ብሏል። የእርጅና ቅናሽ እንዲቀር የተወሰነባቸው ያገለገሉ እቃዎችም ከመመሪያው መውጣት በሁዋላ ግዥ ሂደት ውስጥ የገቡትን ይሆናል።


ሆኖም ይህ ህግ መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ተገዝተው በሚገቡና በገቡ በተለይ ተሽከርካሪዎች ላይ የዋጋ መረጋጋትን ያመጣ አይደለም።የእርጅና ግብር ቅናሽ እንደቀረ ሲሰማም ነው በሀገሪቱ የመኪና ዋጋ ከፍተኛ ጭማሬን ያሳየው።ትንሹ ያገለገለ የመኪና ዋጋ ጭማሬም 80 ሺህ ብር እንደሆነም የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።ከአንዳንድ አስመጭዎች እንደሰማነው አዲሱ መመሪያ ተግባራዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ያገለገሉ መኪኖች ላይ በትንሹ የጨመረው ቀረጥም ከ80 ሺህ ብር በልጧል።