Fana logo

ዋዜማ – በፓርቲ ንብረትነት ለሚታወቁት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ለዋልታ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ባልተለመደ መልኩ የፌደራሉ መንግስት  በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ ድጎማ እያደረገላቸው መሆኑን  ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የሚድያ ተቋማቱ ገንዘቡን ስራቸውን ለማስፋፊያ እንዲሁም ለሰራኞቻቸው ደሞዝ ጭማሪ እና ማሻሻያዎችን ለመተግበር ይጠሙበታል ተብሏል። 

ሁለቱ ሚድያዎች በኢህአዴግ ጊዜ ከአራቱ እህት ድርጅቶች የቦርድ አባላት የሚሾሙላቸው ፣ እንዲሁም አመታዊ ትርፋቸውን በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ከሚተዳደሩ ኩባንያዎች ጋር የሚከፋፈሉት ነው። ገንዘብ ሲያስፈልጋቸውም ከባንኮች ይበደሩ ይሆናል እንጂ በቀጥታ በፌደራሉ መንግስት በኩል አይሰጣቸውም ነበር።

ዋዜማ ከምንጮቿ እንደሰማችው ዋልታ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት እስከ ሁለት ቢሊየን ብር ከመንግስት እንደሚያገኝ እንደሚያገኝ ታሳቢ አድርጎ ዕቅድ አውጥቷል። የገንዘቡን መጠን ፣ እንዲሁም ገንዘቡ የሚሰጠው በብድር ይሁን በልግስና ከተቋሙ አመራሮች ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ይሁንና የሚዲያ ተቋሙ አመራሮች ገንዘቡን ለማግኘት ከገንዘብ ሚኒስቴር ሰዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ እንደነበር ተረድተናል። 

ዋልታ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቅርብ ሰው እንደሆኑ በሚነገርላቸው እና “ሰውዬው” የሚለውን መጽሀፍ በጻፉት መሀመድ ሀሰን በዋና ስራ አስፈፃሚነት እየመሩት ይገኛሉ።

ተቋሙን ሰፋፊ የፕሮግራም ማሻሻያዎችን ለማድረግ ፣ የህንፃና እና ስቱዲዮ ግንባታዎችን ለማከናወን እየተዘጋጀ መሆኑን ሰምተናል። እንዲሁም ለሰራተኞች የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ማስተካከያ ባለፉት ቀናት አድርጓል። 

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በበኩሉ ድጎማን ለመቀበል  ሰሞኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሀን ከመንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ድጎማ ያገኙት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በሰላም ሚኒስቴር በኩል ገንዘብ ፈሰስ በተደረገላቸው ወቅት ነበር።

በውጪ ሀገራትና በሀገር ቤት በመንግስት ላይ ተቃውሞና ትችት የሚያቀርቡ የኢንተርኔት ሚዲያዎች መበራከታቸው እንዲሁም በመንግስት ላይ የተደራጀ የተቃውሞ ዘመቻዎች መጀመራቸው መንግስት በሙሉ አቅሙ ተቃውሞውን ለመመከት አስቦ ሚዲያዎች ላይ ትኩረት አድርጓል ብለው እንደሚገምቱ አንድ የፋና ብሮድካስት የስራ ሀላፊ ነግረውናል። 

ዋልታም ሆነ ፋና የኢህአዴግ መክሰምን ተከትሎ ብልፅግና ሲመሰረት በየኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በነበረው አለመግባባት እንድም እንዲፈርሱ አልያም ባለቤትነቱ ለሌላ አካል እንዲተላለፍ የሚሉ አማራጮች ቀርበው ነበር። በወቅቱ የብልፅግና ሊቀመንበር በሚዲያ ተቋማቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ጥናት እንዲደረግና እንዲቀርብ አዘዙ። ጥናቱ የሚዲያ ተቋማቱ ወደ ሕዝብ ንብረትነት ቢዛወሩ የተሻለ መሆኑን አልያ ግን ከመዘጋት ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ምክረ ሀሳብ አቀረበ። ይሁንና “የፖለቲካ ፍላጎት” እንዳለው የሚነገርለት “ቡድን” አጀንዳውን አደፋፍኖ ተቋማቱን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁና በሂደቱ የተሳተፉ ምንጮቻችን። [ዋዜማ]