Getachew AMBAYE, Minster of Justice
Getachew AMBAYE, Minster of Justice

ዋዜማ ራዲዮ- ገዥው ፓርቲ የተወሰኑ እስረኞችን ለሀገራዊ መግባባት ስል እፈታለሁ ማለቱን ተከትሎ በደህንነት መስሪያ ቤቱና በፍትህ አካላት እንዲህም በፖለቲካ ድርጅቶቹ መካከል የከረረ አለመግባባት መከሰቱን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እየተናገሩ ነው።

ከእስር የሚፈቱ ፍርደኛና ክሳቸው በሂደት ላይ ያሉ የፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦችን ስም ዝርዝር ለፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት እንዲያቀርቡ የታዘዙት ፍትሕ ሚኒስቴርና ፍርድ ቤት ስም ዝርዝር እያዘጋጁ በነበረበት ወቅት የደህንነት መስሪያ ቤቱ ጣልቃ መግባቱን የፍትሕ ሚንስቴር ባልደረባ የሆኑ የዋዜማ ምንጭ ነግረውናል።
“ሀሞስ ዕለት ስብሰባ ተደርጎ የእስረኞች ስም ዝርዝር ላይ ውይይት እየተደረገ በነበረበት ወቅት የደህንነት መስሪያ ቤት ሀላፊዎች ስልክ ደውለው አዲስ መመሪያ ስጥተዋል”  ይላሉ ባልደረባው

የገዥው ግንባር አባል ድርጅቶችም የሚፈቱ እስረኞችን ማንነት ቀድሞ እንዲነገራቸው ብሎም የሚፈልጓቸው ታሳሪዎች እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ሙከራ እያደረጉ መሆኑንና በተለይ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች በሂደቱ ላይ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ መዋላቸውም ተሰምቷል።

የደህንነት መስሪያ ቤት ሀላፊዎች በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር እንደሚነጋገሩበት በመግለፅ ለሀገር ደህንነት ስጋት የሆኑና ቢለቀቁ ችግር ይፈጥራሉ ያሏቸውን ግለሰቦች ከዝርዝሩ ለመሰረዝ እንደዛቱ ምንጫችን መታዘባቸውን ተናግረዋል።
ለይቅርታም ይሁን ለምህረት የታጩ የፖለቲካ እስረኞች ስም ዝርዝር ወደ ፕሬዝዳንቱ ፅህፈት ቤት በዚህ ሳምንት እንዲላክ ትዕዛዝ ቢተላለፍም በተለያዩ ተቋማት መካከል የተፈጠረው መጓተት ፍርሀትና ጭንቀት መፍጠሩን ተመልክቻለሁ ብለዋል ባልደረባው።
ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የሚል ግምት የለኝም፣ ስም ዝርዝር ላኩ የተባለውም ለይስሙላ ነው ይላሉ ግለሰቡ።