PM Abiy Ahmed -FILE
  • ከአምናው 83 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው
  • 100 ቢሊየን ብር ከሀገር ውስጥና ከውጪ ብድር የሚገኝ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2013 አ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ የተባለውን በጀት አጽድቋል።በጀቱም ከ470 ቢሊየን ብር በላይ እንደሆነም ዋዜማ ራደዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። በጀቱ ለ2013 አ.ም የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት በጀት ተብሎ እንዲጸድቅም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንዲያጸድቀው ልኮለታል።
በጀቱ በዚህ ደረጃ ከፍ ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ ስላሳየ ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት መሆኑን ሰምተናል። የኮሮና ቫይረስ ዘጠኝ በመቶ እንዲያድግ ይጠበቅ የነበረውን የኢትዮጵያን የዚህ አመት አጠቃላይ ምርት (Gross Domestic Product) ትንበያውን ወደ ሶስት በመቶ ዝቅ እንዳደረገው መንግስት መግለጹ የሚታወስ ነው። የቫይረሱ ጫና በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አመታዊ አጠቃላይ ምርት እድገቱ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ስለሚችል በጀቱም ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ተብሏል።


ለ2013 አ.ም በጀት ሆኖ የቀረበው ብር በብዙ መልኩ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል።በእየ አመቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየጸደቁ ከሚመጡ በጀቶች ያለው አመታዊ ብልጫውም እጅግ ከፍተኛው ነው። ይህንንም በአጋማሽ በጀት አመት ላይ የሚጸድቀው ተጨማሪ በጀትን ሳይጨምር በ2011 አ.ም ሰኔ ለዚህ አመት ማለትም ለ2012 አ.ም የጸደቀው የፌዴራል መንግስት በጀት 387 ቢሊየን ብር ነው። ይህ በጀት ለ2011 አ.ም ከጸደቀው 347 ቢሊየን ብር ያለው ልዩነት 40 ቢሊየን ብር አካባቢ ነው።

የ2011 አ.ም በጀትም ከ2010 አ.ም በጀት 321 ቢሊየን ብር ያለው ልዩነት የ26 ቢሊየን ብር ሲሆን ፣ ይህ ለ2009 ከጸደቀው 274 ቢሊየን ብር ደግሞ ልዩነቱ 47 ቢሊየን ብር ነው።

ለ2013 በጀት አመት የጸደቀው በጀት ግን ከዚህኛው 2012 አመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የ83 ቢሊየን ብር ልዩነት አለው።በየአመቱ ከሚጸድቁ በጀቶችም ለ2013 አ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀውን ያክል እድገት ያሳየ ብዙም የለም።


በየበጀት አመቱ ግማሽ የሚጸድቁ ተጨማሪ በጀቶችን አክለን ብናነጻጽር ራሱ ለ2013 አ.ም በሚኒስትሮች ምክርቤት የተዘጋጀው በጀት እድገት ከፍተኛ ነው። የ2011 አ.ም በጀት እስከ ጭማሬው 391 ቢሊየን ብር ነው። የዚህ አመቱ ማለትም የ2012 አ.ም እስከ ጭማሬው 415 ቢሊየን ሲሆን ካለፈው አመት ልዩነቱ የ24 ቢሊየን ብር ነው።

የ2013 አ.ም በጀት በቀጣይ አመት አጋማሽ በጀት ላይ የሚጨመረው ብር አጠቃላይ በጀቱን ከግማሽ ትሪሊየን ብር በላይ ስለሚያደርገው ልዩነቱም የዛኑ ያክል ከፍ የሚል ይሆናል። በጀቱ ለካፒታል እና መደበኛ ተብሎ የተከፈለ ሲሆን በዚህ ውስጥም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊዳከም የሚችል ዘርፍን የማካካስ አላማ እንዳለም ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ብድርና እርዳታ

ብድርና እርዳታ ከእስካሁኑ ከተለመደው በተለየ መልኩ የተሻለ ድርሻን በበጀቱ ውስጥ ቦታ እንዳለውም ለመረዳት ችለናል።ከበጀቱ ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ብድር ለማሟላት ታስቧል። ከሀገር ውስጥና ከውጭ ብድር ለ2013 አ.ም በጀት እንዲሞላ የታሰበውም 100 ቢሊየን ብር ይሆናል። ከዚህ ውስጥ 70 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ የተለያዩ ምንጮች በብድር የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው 30 ቢሊየን ብር የበጀቱ አካል ከውጭ አበዳሪዎች እንደሚገኝም ተጠብቋል። በእርዳታ የሚሞላ የበጀቱ አካል እንደሚኖርም ይጠበቃል።


በተለየ መልኩ ግን የ2013 አ.ም በጀትን ከፍ ያለ ጉድለት ሊያጋጥመው የሚችልበት ስጋት እንዳለ ሰምተናል። በጤነኛ ኢኮኖሚ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ አመታዊ ምርት ከሶስት በመቶ ባይበልጥ ይመከራል። ሆኖም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት ብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች በመዳከማቸው ምክንያት በሚሰበሰብ ግብርና ቀረጥ የሚሞላው በጀት ከሚጠበቀው በታች ዝቅ የማለት እድሉ ከፍ ስለሚል የበጀት ጉድለቱም የዛኑ ያክል ከፍ ሊል ይችላል።

የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የሚወሰዱ እርምጃዎችም የዋጋ ግሸበት ጨማሪ የመሆን እድላቸው ከፍ ያለ ነው የሚሆነው።ይህ ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊትም ከእቅድ በላይ የሆነውን የዋጋ ግሽበት ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል። [ዋዜማ ራዲዮ]