Daniel Bekele -EHRC Head
  • ኢሰመጉ መንግስት ሀላፊነቱን አልተወጣም ሲል ተችቷል

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮምያ ክልል በንፁሀን ዜጎች ላይ በታጣቂዎች የተፈፀመውን ግድያ በተመለከተ መንግስት  ለዜጎች ደሕንነት ጥበቃ እንዲያደርግና ሀላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫው ጠይቋል። 

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ  ቶሌ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የሰዎች ሕይወት እንደጠፋ የገለፀው ኢሰመኮ የአካባቢው ነዋሪዎች ከግድያው በኋላ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሆኑ እና መንግሥት የጸጥታ ጥበቃ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እየጠየቁ እንደሆነ ኮሚሽኑ ገልጧል። 

ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ መንግሥት ሲቪል ሰዎች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ርምጃዎችን እንዲወስድ፣ ሲቪሎች የጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል።

ምዕራብ ወለጋ

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ የንጹሃን ጅምላ ጭፍጨፋውን የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደሆኑ እና የጥቃቱ ዒላማዎች በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች እንደሆኑ የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል። ከግድያው በኋላ መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው እንደገባ ተገልጧል። የክልሉ መንግሥት ግድያውን የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ሲል፣ ቡድኑ ግን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።

ዳዋጨፋ

በሌላ በኩል ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በመዘዋወር ላይ የሚገኘውንና በርካታ ሰዎች ከመኪና እንዲወርዱ ተደርገው በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል በተመለከተ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠይቀዋል፡፡

ኢሰመኮ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየው ግድያ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ድርጊት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢሰመኮ በምርመራ ሪፖርት ከምስክሮች እና በስፍራው በመገኘት በመስክ ምልከታ አሰባሰብኩት ባለው መረጃ ድርጊቱ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ አካባቢ በታኅሣሥ ወር 2014 ዓ.ም. መፈፀሙን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ወንጀሉ የተጸፈፀመበተን ቀን በትክክል ለማወቅ እንዳልቻለ ነገር ግን አለኝ ባለው መረጃ መሰረት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሁለት የጭነት መኪኖች ጭነው ያመጡዋቸውንና ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች በጅምላ በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው በመግለጫው አስረድቷል፡፡ 

ኮሚሽኑ በተጨማሪ የቴክኒክና የመስክ ምርመራ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ምርመራዎችን ማካሄዱንና ወንጀሉ ከፍርድ ውጭ የተፈጸመ የግድያ ድርጊትን የሚያመለክት ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያት እንዳለው አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በተሰራጨ ምስል በርካታ ቁጥር ያላቸው የታጠቁና የጸጥታ አካል ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች በመኪና ላይ ተጭነው የነበሩ ሰዎችን ሲደበድቡ እና እያስወረዱ ሲረሽኑ መታየቱንና ይህ ድርጊት መቼ፣ በማን፣ ለምን፣ የት እና በማን ላይ እንደተፈጸመ ለማወቅ ባይቻልም ድርጊቱ ግን ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ እንደሆነና ድርጊቱ ኢ-ሰብዓዊ ከመሆኑም በላይ  እየተደጋገመ የመጣ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ጋምቤላ

በሌላ በኩል ሰኔ 07 ቀን 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በፈፀሙት ጥቃት ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ንብረት መውደሙን አስረድቷል፡፡

በዚሁ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እንዲሁም ከታጣቂ ቡድኑ በተተኮሱ ጥይቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን የአካባቢው ነዋሪዎች መሞታቸውንና የአካል ጉዳት መድረሱን በመረጃ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡

በዚህም በጋምቤላ ከተማ ውስጥ አንድ ወጣት የጸጥታ አካላት ዩኒፎርምን በለበሱ ሰዎች አጁን ታስሮ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በጥይት ተደብድቦ ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ  መገደሉን አስታውቋል፡፡

በዚሁ ዕለት በተደራጁ ቡድኖች በርከት ያሉ ንጹሀን ሰዎች ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል እንዲሁም ማንነትን መሰረት ያደረገ በሚመስል ጥቃት አባት እና ልጅ ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው መገደላቸውን በመግለጽ በአካባቢው አሁንም ስጋት ቢኖርም መንግስት ንጹሀንን የመጠበቅ ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ በመግጫው አቅርቧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]