ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ ህዝብ አመታዊ የኢሬቻ አከባበርን በተመለከት ከክልሉ የፀጥታ ሀይሎች ጋር የጋራ ዕቅድ ነደፈ።
የኦሮሞ አክቲቪስቶችና አድመኛ ወጣቶች በበኩላቸው በበዓሉ ወቅት በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻቸው ድምፃቸውን ለማሰማት እየተሰናዱ ነው።
ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች እንዳገኘችው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኢሬቻ በዓል ወቅት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ፣ ችግሮች በሚከሰቱ ጊዜ መወሰድ ስላለበት እርምጃና ማን ምን ሀላፊነት ይወስድ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ስፊ ውይይት ተደርጎ የስራ ክፍፍል ተደርጓል።
መንግስት በሺህ የሚቆጠሩ ሲቪል ደህንነቶችን የሚያሰማራ ሲሆን የኦሮምያ ፖሊስ ዋና የፀጥታ ማስከበር ስራዎችን ይሰራል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ድጋፍ ስጪ ሆነው የሚሰሩ ሲሆን “ልዩ ሀይል”  አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ተሳታፊ ይሆናል።
“ልዩ ሀይል” በቅርብ ርቀት ላይ በመሆን ቦታ እንዲይዝ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የቀይመስቀልና የበጎ ፈቀደኞች በተለያየ አካባቢ ማዕከላትን በመክፈት ለድንገተኛ አደጋ እርዳታ ለመስጠት ይመደባሉ። አምቡላንስና የእሳት አደጋ ሰራተኞችም በቦታው ይገኛሉ።

አጠቃላይ ሂደቱን የሚመራ ጊዜያዊ የማዘዣ ጣቢያ የሚኖር ሲሆን በፌደራሉና በኦሮምያ ክልል በተወከሉ ከፍተኛ ሀላፊዎች ይመራል።

መንግስት በበዓሉ ላይ ሁከት ለመቀስቀስ የተደራጀ ቡድን መኖሩንና ሁከት ለመቀስቀስ የሚሞክሩትን አስቀድሞ ለመቆጣጠርና ፍተሻ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ለመረዳት ተችሏል።

የኦሮሞ አክቲቪስቶችና አድመኛ ወጣቶች አምና ለሞቱትና በሌሎች አካባቢዎች ግፍ ለደረሰባቸው ድምፃቸውን ለማሰማት እንደተዘጋጁ ለመረዳት ችለናል።
“እንቅስቃሴያችን ሁሉ ሰላማዊ እንዲሆን እንጥራለን- ከዚህ አልፎ መንግስት ሁኔታውን ወደ ሁከት ከቀየረው እኛ ሀላፊነቱን አንወስድም” ብሏል የኦሮሞ ወጣቶችን በማስተባበር የሚንቀሳቀስና ስሙን የሸሸገ ወጣት።

PHOTO-FILE