ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ሶስት ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ከተሞች ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተስፋፍቶ መቀጠሉንና ችግሩን ለማስቆም የተወሰደ እርምጃ ባለመኖሩ ችግሩ ወደ ከፋ ቀውስ ይደርሳል የሚል ስጋት እንዳለው የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ሴታ ለፓርላማ አባላት ባቀረቡት ሪፖርት የመሬት ወረራን ለማስቆም ብሎም እንዳይከሰት ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ባለመዘርጋቱ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።

ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የ2014 ዓ.ም በጀት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ግምገማ ባደረገበት ጥር 16 ቀን 2014 ዓ.ም ነው፡፡

‹‹የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ውስን የሆነውን የከተማ ሃብት መች፣በማን እንደተያዘና ለምን አገልግሎት እንደዋለ የማናውቅ በመሆናችን ሃብቱ የማንም ሆኗል ›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

በተለይም አለመረጋጋት በታየባቸው አካባቢዎች ሕገ ወጥ የመሬት ወረራው በስፋት የታየ ሲሆን በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ችግሩ መኖሩንና ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ከተሞች በአስተዳደራቸው ውስጥ ያለውንና የአስተዳደር ወሰናቸውን በአግባቡ ከልለውና ቆጥረው ለማስተዳድር የሚያስችል  ስርዓት ባለመዘርጋታቸው እንደሆነ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።፡፡

‹‹ይህ ህገ-ወጥነት በእርግጠኝነት ወደ ቀውስ የሚወስድ በመሆኑ ወደዛ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በአጭር ጊዜ አሁኑን እንዲቆም ፓርላማው እገዛ ያድርግልን›› ሲሉም ጠይቅዋል፡፡

ሕጋዊ የተባለው የመሬት አስተዳደርም ቢሆን ደረጃውን በጠበቀ ስርዓት የማይመራ ለሌብነት የተጋለጠና ዜጎች ዕሮሮ የሚያሰሙበት የአደባባይ ችግር መሆኑን ሀላፊው አንስተዋል።

መሬት በተጋነነ የሊዝ ዋጋ ወስዶ ከአንድ ዓመት በኋላ  ምንም ሳይከፍሉ መጠቀም እየተበራከተ የመጣ ችግር ሲሆን ከተሞች ከሊዝ ሊያገኙ የሚገባቸውን ገቢ እንዲያጡ አድርጓል። 

መንግስት ከመሬት ሽያጭና ዝውውር ጋር በተያያዘ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እጅግ ስር በሰደደ የድብብቆሽ አሰራር ምክን ያት ማግኘት እንደተሳነው ይህ ደግሞ ለከተሞች ዕድገት አሰፈላጊ የሆነ የሀብት ምንጭ እንዲባክን አድርጓል።

የመሬት ነክ ግብይቱ ከፍተኛ ቢሆንም መቆጣጠሪያ ስርዓት ባለመኖሩና በህገወጥ መንግድ የተወረረውን መሬትን ማሰቆም ካልተቻለ የሚታሰበው እድገት አይሳካም ብለዋል፡፡

የመሬት ወረራን ለማስቆም በተደረገ ጥረት ለአብነትም በህገወጥ መንገድ የተያዘን መሬት ለማስለቀቅ በአዲስ አበባ፣በሃዋሳ፣በድሬዳዋ ያደረጉት ሙከራ ቀውስ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

እየታየ ያለውን ችግር ለመፍታ በዘመናዊ መንገድ የማደራጀትና የመመዝገብ ስራው ካባድ አለመሆኑን የጠቀሱት ዳይክተሩ ይህን ሰፊ የተባለውን የመሬት ወረራ ለማስቆም ዘመናዊ የመሬት አመዘጋገብ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል እና በከተሞች ላይ  ቁርጠኝነት የጎደላቸውና አንዱ የሌላውን እጅ ጠምዝዞ መኖር የሚፈልጉ በርካታ አመራሮችን ማስተካከል ሲቻል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የአመራር ቁርጠኘነት ካለ የሚፈለገው ቴክኖሎጅ በጣም ቀላል መሆኑንና  አብዛኛዎች የአለም አገራት ከ2ኛው የአለም ጦርነት ማግስት መተገበር የጀመሩት የመሬት ቴክኖሎጅ እንደሆነ አቶ ወንድሙ አክለው ገልጸዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]