Debretsion GMeachel-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የትግራዩ ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም እንዲረዳው፣ በክልሉ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ወደ ወደ አንድ ቋት (ባንክ) እንዲገባ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። 

በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በትግራይ ክልል ያጋጠመውን ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ ሲል የክልሉ መንግሥት ከመጋቢት 15፣ 2014 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የፋይናንስ ተቋማት መመሪያ በማውጣት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህንኑ እንቅስቃሴውን የሚያስተባብርለት የፋይናንስ ፎረም አቋቁሟል።

የተቋቋመው አዲሱ የፋይናንስ ፎረም አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መብርሀቱ መለሰ፣ በክልሉ የፋይናንስ አገልግሎት በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ የክልሉ መንግሥት በክልሉ ሥራ ለመስራት ከባንክ ውጭ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ባንክ መመለስ እንዳለበት አሳስበዋል። በክልሉ ያሉ ባለሃብቶችም ገንዘባቸው ወደ ባንክ እንዲያስገቡ የማግባባት ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን እስካሁን ድረስ ወደ ባንክ የገባው የገንዘብ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ባለሀብቶች በእጃቸው የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ እና በእጃቸው የሚገኘውን የውጭ አገራት ገንዘብ ደሞ እንዲያስመዘግቡ ጥሪ  ቀርቦላቸዋል፡፡ ገንዘባቸውን ወደ ባንክ ገቢ በማያደርጉ አካላት ላይ የክልሉ መንግሥት ርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጧል፡፡

በትግራይ መደበኛ የባንክ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ይሁንና ክልሉ በራሱ ያቋቋመው ግብረ ኀይል ከንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ጋር በመሆን ይህን የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተረድተናል። 

ለዚህ ስራ የትኞቹ ባንኮች በስራው እንደሚሳተፉ የተብራራ መልስ አላገኘንም። 

የክልሉ መንግሥት ባወጣው አዲስ የፋይናንስ መመሪያ መሠረት፣ አንድ ግለሰብ በእጁ ከ100 ሺህ ብር በላይ እንዲይዝ አይፈቀድለትም።

በክልሉ በንግድ ሥራ ለተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግን፣ እንደ ንግድ ደረጃቸው ከ150 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ መያዝ እንደሚችሉ ሃላፊው አክለው ተናግረዋል፡፡   

የትግራይ ዲስትሪክት የንግድ ባንክ ሃላፊ ኤሊያስ ልሳነወርቅ ጉዳዩን አስመልክቶ በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ እንዲህ ብለዋል፤ 

አሁን ባለው ሁኔታ ሕዝባችን በከባድ ረሃብ እና በሽታ ላይ ወድቆ ይገኛል። ችግሩን ለማቃለል የክልሉ መንግሥት በሰጠው መመሪያ መሠረት፣ የፋይናንስ ተቋማት ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። ነገር ግን አብዛኛው የግለሰቦች እና ባለሃብቶች ገንዘብ ከባንክ ውጭ በመሆኑ፣ የፋይናንስ ተቋሞቹ በሚፈለገው ልክ መስራት አልቻሉም።

ሃላፊው አክለውም፣ ” ሕዝባችን ያጋጠመውን ከባድ ችግር ለመፍታት፣ ገንዘብ ያላችሁ አካላት በሙሉ ገንዘባችሁን ወደ ፋይናንስ ተቋም በማስገባት ችግሩን ተደጋግፈን እንድንሻገረው አብረን በጋራ መስራት አለብን የሚል ጠንከር ያለ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለው” በማለት መድረኩ ላይ ተናግረዋል። ሃላፊው ኤሊያስ አያይዘውም፣  ሕዝቡ የመተጋገዝ አቅሙን እና ባህሉን ማጠናከር እንዳለበት በአጽንዖት አሳስበዋል።

በትግራይ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የባንክ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን፣ ማዕከላዊ መንግስት ትግራይ በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች ላይ የጣለው እገዳ ተደምሮ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን ከባንክ ወጪ ባለ ገንዘብ ላይ አድርገው ቆይተዋል። ዓለማቀፍ ድርጅቶች ወደ ትግራይ በሚያስገቡት የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ፌደራል መንግሥቱ የጣለውን ገደብ ገደብም ችግሩን አባብሶታል። አሁንም በትግራይ የባልክ አገልግሎት ስለመጀመሩ ከማዕከላዊ መንግስት የተሰጠ ፍንጭ የለም። 

ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ግን መንግስት በአስቸኳይ ለትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያስጀምር ጫና እያደረጉ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]