ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ተበድሮ ብድሩን በአግባቡ መክፈል ያልቻለው በቱርካውያን ባለቤትነት የተመሰረተውን ኢቱር ቴክስታይል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ተረክቦ ማስተዳደር ጀመረ።

ዋዜማ ራዲዮ እንዳረጋገጠችው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው የተበደረውን ገንዘብ በአግባቡ መመለስ ባለመቻሉ ለብድር አመላለስ በዋስትናነት የተመዘገበውን በአዳማ ከተማ ያለውን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ተረክቦ ማስተዳደር ጀምሯል። የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰቦችን በማንሳትም ልማት ባንክ ለኩባንያው ስራ አስኪያጅ ፣የፋይናንስ ሀላፊ ፣የማርኬቲንግ እና ሌሎች ሀላፊዎችን ራሱ መድቧል።

 በ1950ዎቹ በቱርክ የተቋቋመውና በጨርቃጨርቅ ምርቶች አለም አቀፍ አቅራቢነት የሚታወቀው የዩክሴል ቴክስታይል እህት ኩባንያ የሆነው ኢቱር ቴክስታይል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ስራ የጀመረው በ2002 አ.ም ነበር። በወቅቱም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቢሊዮን የሚቆጠር ብድር ከወሰዱ መሰረታቸውን ቱርክ ካደረጉ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚመደብ ነው።


አዳማ ላይ ባቋቋመው ፋብሪካ በዋነኝነት ክርን የሚያመርት ሲሆን ክርን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ለሚያመርቱ የተለያዩ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ግብአት ሲያቀርብም የቆየ ነው።

ነገር ግን እንደሌሎች የቱርክ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የወሰደውን ብድር በጊዜው መክፈል አልቻለም። ከስድስት አመት ወዲህም ፋብሪካው የልማት ባንክን ብድር መመለስ ስላልቻለ የተበላሸ ብድር መዝገብ ውስጥ ገብቶ የቆነ ነው።

በተደጋጋሚ ብድሩን እንዲመልስ ከልማት ባንኩ ደብዳቤ የተጻፈለት ቢሆንም በተገቢው መንገድ ብድሩን እንዳልከፈለ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

 የፋብሪካው ብድር ከነወለዱ ከ1.2 ቢሊየን ብር እንደሚያልፍያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ልማት ባንኩ በተደጋጋሚ ፋብሪካውን ሽጦ ገንዘቡን ለማስመለስ አስቦ የነበረ ቢሆንም ኩባንያው የሰራው ፋብሪካ እና ያስመጣቸው ማሽኖች ዋጋ ከወሰደው ከፍተኛ ብድር አንጻር በጣም አነስተኛ መሆኑና የቀጠራቸው ሰራተኞች የስራ ዋስትና ስጋት ስለፈጠረበት ሀራጅ የማውጣቱን ነገር አልተገበረውም።

 አልሲ አዲስና አይካ አዲስ የሚባሉ ሁለት የቱርክ ኩባንያዎች ልክ እንደ ኢቱር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቢሊየን የሚቆጠር ብር ተበድረው መክፈል ስላልቻሉ ባንኩ ገንዘቡን ለማስመለስ ተደጋጋሚ ጨረታ ቢያወጣው የፋብሪካዎቹ ዋጋ ብድሩን የማያስመልስ ብቻም ሳይሆን የወሰዱት ብድርና ያስገቧቸው ማሽኖች ዋጋ ሊመጣጠን ባለመቻሉ ተረክቦ ማስተዳደር ከጀመረ ሰነባብቷል። በተለይ ለቱርክ ኩባንያዎች የተሰጠው ብድር የተጋነነና የሰሩት ፋብሪካና ያስመጡት ማሽን የወሰዱትን ብድር አይመጥንም በሚል በተደጋጋሚ ባንኩ ላይ ትችት ሲቀርብ እንደቆየ የሚታወቅ ነው።

ልማት ባንኩ ኢቱር ቴክስታይል ኩባንያን ካለበት የብድር አከፋፈል ችግር እስኪወጣም ራሱ በሰየመለት አመራሮች እየተመራ የሚቀጥል ይሆናል። [ዋዜማ ራዲዮ]