Ethiopia Milk cooperative members
Ethiopia Milk cooperative members

በቀንድ ከብቷ በብዛት በአፍሪካ አንደኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ያህል የቀንድ ከብቶች ያሏት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አስር ሚሊዮኑ የወተት ላሞች መሆናቸውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል፡፡

ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የወተት ምርት የሚገኘውም ከቀንድ ከብቶች ነው፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ እና ድርቅን መቋቋም የሚችል የግመል ዝርያ እንዳላት የሚነገርላት ሀገራችን በግመል ወተት ምርት ከኬንያ፣ ሱማሊያና ማሊ ቀጥላ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የግመል ወተት በከተሞች አካባቢ ያልተለመደ ሲሆን ለፑንትላንድ፣ ሱማሊላንድና ጅቡቲ በመሸጥ ሀገሪቱ በኣመት 300 ሺህ ዶላር ገቢ እንደምታገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በውጭ ገበያ አንድ ሊትር የግመል ወተት እስከ 20 ዶላር ይሸጣል፡፡

(ቻላቸው ታደሰ ዘርዘር ታለ ዘገባ አለው አድምጡት)

በጠቅላላው በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ በዓመት የሚመረተው ወተት ከአራት ቢሊዮን ሊትር እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከግመል ወተት ደግሞ በዓመት የሚገኘው ምርት 170 ሺህ ቶን ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት እንደሚያሳየው በ2007 ዓ.ም ከተገኘው ጠቅላላ የወተት ምርት ውስጥ አርባ ስድስት በመቶው በጥሬው ለዕለት ፍጆታ ሲውል ስድስት በመቶው ብቻ ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ አርባ ሶስት በመቶ ያህሉ ደግሞ ለፍጆታ የሚውሉ የወተት ተዋፅኦዎችን ለማምረት ውሏል፡፡ ከላም ወተት የላቁ ንጥረ ነገሮች እንደያዘ የሚነገርለት የግመል ወተትም ቢሆንም በአብዛኛው ለአርብቶ አደሮች ፍጆታ የሚውል ነው፡፡ ሽያጩም ቢሆን ገበያው ያልተስተካከለ በመሆኑ የዕለት ምግብ ፍጆታን ለመሸፈን ብቻ እንደሚውል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የወተት አቅርቦትና ፍጆታ ዕጥረት ባለባት ሀገራችን ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት የተመጣጠነ ዕድገታቸው አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ነው፡፡ መንግስት የሚያምነውን የአምናውን የዲሞግራፊ እና ጤና ዳሰሳ ጥናት ብንወስድ እንኳ አርባ በመቶ የሚሆኑት ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናት በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን የህፃናት ጤናማ እድገት መስፈርቶች አያሟሉም፡፡

በዓለም ላይ የአንድ ሰው አማካይ ዓመታዊ የወተት ፍጆታ ሰባ አምስት ሊትር ሲሆን በሀገራችን ግን አስራ ዘጠኝ ሊትር ብቻ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው ነዋሪ በሚበዛባት አዲስ አበባ ግን ፍጆታው እስከ ሃምሳ ሊትር የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡ በንፅፅር ሲታይ የሀገራችን አማካይ ፍጆታ የሱዳንን አስር በመቶ እና የኬንያን ደግሞ ሃያ በመቶ ያህል ብቻ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው የኬንያዊያን የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ፍጆታ 110 ሊትር ደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ በ2020 ዓ.ም ፍጆታዋን ወደ ኬንያ ደረጃ ለማድረስ በዓመት ከአስር ቢሊዮን ሊትር በላይ ማምረት እንደሚጠበቅባት ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነምመንግስት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕድገት ወተት ልማት-ተኮር መሪ ዕቅድ ነድፎ ምርቱን በ2020 ዓ.ም በእጥፍ ለማሳደግና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ኢንዱስትሪው በበርካታ ማነቆዎች ተተብትቦ በሚገኝበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱ ዕቅድ እጅጉን የተለጠጠ መሆኑን ይተቻሉ፡፡ ያም ሆኖ ከአምስት ዓመት በኋላ የታለመው ምርት መጠን ከአሁኑ የኬንያዊን ፍጆታ እንኳ ያነሰ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአምስት ዓመት በኋላ የወተት ፍጆታ በ132 ፐርሰንት እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡

በአዲስ አበባ የአንድ ሊትር ወተት ወቅታዊ ዋጋ ከአንድ ዶላር በላይ ሲሆን በናይሮቢ ግን 0.78 ዶላር ብቻ ነው፡፡ በኡጋንዳዋ ካምፓላም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ በአንፃሩ በጅቡቲ ውድ በመሆኑ በ1.8 ዶላር ይሸጣል፡፡ ስለሆነም የወተት ዋጋ አነስተኛ ገቢ ላለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የማይቀመስ እንደሆነ የዳሰሳ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ዘጠና በመቶ የሀገራችን የወተት ላሞችም በምርታማነታቸው በጣም ዝቅተኛ ከሆኑት ሀገር በቀል ዝርያዎች የተገኙ በመሆናቸው ከአንድ ላም በቀን ሊገኝ የሚችለው ወተት በአማካይ ከግማሽ እስከ ሁለት ሊትር ያህል ብቻ ነው፡፡ የተዳቀሉ ምርጥ ዝርያዎች ግን በቀን እስከ አስር ሊትር ወተት ሊሰጡ እንደሚችሉ በምርምርም ሆነ በተግባር ተደርሶበታል፡፡ አንድ ግመል ደግሞ በአማካይ የምትሰጠው ወተት ስድስት ሊትር ብቻ ሲሆን መኖን ጨምሮ ሁሉም ግብዓቶች ቢሟሉ ግን እስከ አስራ ስምንት ሊትር ድረስ የመስጠት አቅም እንዳላት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአውሮፓና እስያ ኢኮኖሚ በመቀዛቀዙ በርካታ የምግብና ወተት ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ገበያ አዙረዋል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በወተት ምርቷ ቀዳሚ የሆነቸው ኒውዚላንድ ኩባንያ የሆነው ግዙፉ ፎንቴራ በኢትዮጵያ “አንከር” የተሰኘ የዱቄት ወተት በማምረት በዓመት ሁለት ነጥብ አምስት ሺህ ቶን የዱቄት ወተት ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል፡፡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ ቶን ሲያመርት ደግሞ አርባ አምስት በመቶውን የሀገሪቱን ፍላጎት እንደሚያሟላና ለጎረቤት ሀገሮችም እንደሚሸጥ ይገልፃል፡፡ እስካሁን በሀገሪቱ ዱቄት ወተት የሚያመርት አንድም ኩባንያ ባለመኖሩ ሀገሪቱ አምና ብቻ ከውጭ ላስገባችው ዱቄት ወተት ከአስር ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንዳወጣች ከመንግስት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ባሰለፍነው ወር ደግሞ የፈረንሳዩ ግዙፍ ምግብ አቀነባባሪ “ዳኖኔ” ከኬንያው “ብሩክሳይድ” የወተት ኩባንያ የአርባ በመቶ ድርሻ በመግዛት የምስራቅ አፍሪካ ወተት ገበያን ለመቆጣጠር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን እየገለፀ ነው፡፡“ብሩክሳይድ” በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ ወተት አቀነባባሪ ሲሆን በኬንያ ገበያ ብቻ የአርባ በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ዳኖኔ ከአንድ መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ የኬንያ ወተት አምራች ገበሬዎች በፅሁፍ ማስያዣ ብቻ ከባንኮች ብድር እንዲወስዱ ዋስትና ሆኗቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምቹ ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኩባንያው በኡጋንዳም ቀዳሚው ወተት አምራችና ሻጭ ሆኗል፡፡

በጠቅላላው ይህን ዘርፍ በተመለከተ መንግስት ከእንቅልፉ የባነነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ስለሆነም በዕቅዱ ዘመን ኢንዱስትሪውን ሸብበው የያዙት መዋቅራዊ ችግሮች ተቀርፈው በጥራት፣ በመጠንና በዓይነት ተሸሽሎ እያደገ የሚሄደውን ፍላጎት ማርካቱ አጠያያቂ ነው፡፡