Tobacco

ዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑትምባሆ ሞኖፖልበመንግስት ድርጅቶች አክስዮን ሽያጭ ታሪክ አዲስ የዋጋ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡ እስካሁን ለባለሃብቶች ከተዛወሩ የመንግስት ድርጅቶች ውስጥ በዋጋ ውድነት በቀዳሚነት ሲጠቀስ የቆየው ለዲያጂኦ 225 ሚሊየን ዶላር የተሸጠው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ነበር፡፡ጃፓን ኢንተርናሽናል ቶባኮ” (JIT) ይሕን ዋጋ እጥፍ ባስከነዳ 510 ሚሊየን ዶላር ነው፣ የትምባሆ ሞኖፖልን 40% አክሲዮን በመግዛት የጨረታ አሸናፊ መሆኑ የተገለጸው፡፡ ጄአይቲ (JIT) ከአሜሪካ ውጪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዊኒስተን፣ ካሜል እና ቤንሰን ኤንድ ሄጅስ ሲጋራዎችን ያመርታል፡፡በአፍሪካ በታንዛንያና ሱዳን ሲጋራ ፋብሪካዎች ከፍተኛ ትረፍ ያገኘው ኩባንያው በኢትዮጵያ መንግስት ጭምርያልተገመተም፣ ያልተጠበቀምአስደንጋጭ መጫረቻ ዋጋ በማቅረብ ማሸነፉ ተነግሯል፡፡ ለግዢው 510 ሚሊየን መቅረቡ የተጋነነ ነው የሚል እምነት ያላቸው  ተንታኞችጄአይቲ ይሕን ያሕል ዋጋ አውጥቶምን ለማትረፍ እንደፈለገ አልገባንምበማለት ግራ መጋባታቸውን ይናገራሉ።

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን ሀኒ ሰለሞን ታቀርበዋለች- ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

የኢትዮጵያን ሲጋራ ፋብሪካ አክስዮን ለመሸጥ በወጣው ጨረታ አምስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ሆኖም የጃፓኑ ኩባንያ ካቀረበው ግማሹን ያሕል አልቀረበም፡፡ ማለት ሌሎች ያቀረቡት አነስተኛ ነበር ማለት አይደለም፡፡ በጨረታው ሁለተኛ ወጥቶ የተሸነፈውብሪቲሽ አሜሪካ ቶባካ ፒእልሲእንኳሜታ ቢራ ከተሸጠበት የላቀ ገንዘብ ነበር ያቀረበው፡፡ ቻይና ሎጀስቲክስ ሊሚትድ 40 % አክስዮን ድርሻ 156 ሚሊየን አቅርቦ ነው ከውድድሩ ውጪ የሆነው፡፡ የቀድሞው የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ አሠፋ አብርሃ የሚያማክሩት ሌላ የቻይና ኩባንያም በጨረታው የመሳተፍ ፍላጎት አሳይቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡ አንድ የኒጀር ኩባንያም 10 % አክስዮን 35 ሚሊየን ዶላር መድቦ ነበር፡፡ ትንሹን መጫረቻ ዋጋ አቅርቦ የነበረውበቅርቡ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ግማሽ ሚሊየን ዶላር የለገሰው የአሜሪካውፊሊፕ ሞሪስ ኢንተርናሽናል120 ሚሊየን ዶላር ያነሰ አልመደበም፡፡ ይሕም ከመንግስት የማምረቻ ተቋማት የትምባሆ ሞኖፖል ሽያጭ የሚገኝበትን ደረጃ ጠቋሚ ነው፡፡

ሲጋራ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በትምባሆ ማሸጊያዎች በጉልሕ እንዲጻፍ የሚደረገው በዋዛ አይደለም፡፡ በርካታ የጤና ጆርናሎች እንዲሁም የዓለም አቀፉ የጤና ተቋም WHO እና CDC ዶክመንቶች ጭምር ሲጋራንጅምላ ጨራሽ የእልቂትና ሞት ሠበብመሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በዓለማችን ከአስር ሰዎች መሐል አንዱ የሚሞተው በሲጋራ ማጨስ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች2030 ከስድስት ሰዎች አንዱ ለሞት የሚዳረገው በሲጋራ ጦስ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ 600 ሺህ ሲጋራ የማያጨሱ ሰዎች የሚያልቁት ከአጫሾች በሚለቀቅ ጪስ የተነሳ መሆኑ ነው፡፡ 80 % ከሲጋራ ጋር የተያያዘ ሞት የሚከሰተው ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ታዳጊና መካከለኛ ሃገራት ተርታ መሆኑ የነዚህን ሃገራት ችግር የከፋ እና ተደራራቢ ያደርገዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የትምባሆ አምራች ኩባንያዎችበምዕራባውያን ሃገራት የሚደረግባቸው ቁጥጥር ትርፋቸውን በእጅጉ ስላወረደው ትኩረታቸውን ወደ ታዳጊ ሃገራት በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

የሲጋራና ትምባሆ ምርት ትርፍዝቆሽመሆኑን የሚገልጹ ምንጮች የኢትዮጵያ መንግስት በትምባሆ ሞኖፖል ይዞት የቆየውን 71% ድርሻ ላለመልቀቅ ሲያንገራግር የነበረው ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡ ለጃፓኑ ኩባንያ 40 ከመቶ ድርሻውን የሸጠውም በአጭር ጊዜ ሊያገኘው የማይችለው ገንዘብ ስለቀረበለት ነው ይላሉ፡፡  መንግስት ከትምባሆ ሞኖፖል የአክስዮን ድርሻ አሁንም 31 ከመቶውን አሳልፎ የማይሰጠውም ጥቅም ተጋሪነቱን በቅርበት ለመቆጣጠር እንደሆነ የሚገልጹም አሉ፡፡ ከተጫራቾች ወገን የነበሩ ጠንካራ የቅስቀሳ ቡድኖች መንግስት ከፋብሪካው ከሚያገኘው ትርፍ ሙሉ በሙሉ ሳያጣ እና ተጠቃሚነቱን ሳይነጠቅ የፋብሪካውን አክስዮን እንዴት ባለ መልኩ ሊሸጥ እንደሚገባ አማራጭ ሃሳብ ማቅረባቸውን የገለጹ የዜና ምንጮች የጃፓኑን ኩባንያ ከዚሀ አንጻር መመረጡን ይገልጻሉ፡፡ የትንባሆ ሞኖፖል 29 ከመቶ ድርሻ ከአስር ዓመት በፊት ለየመናውያን ባለሃብቶች መሸጡ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሽያጭ ላይ ብዙ አጠራጣሪ ጉዳዮች ቢኖሩም፡፡ 

የምጣኔሃብት ባለሙያወችና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የመንግስት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት መዛወር ለኢኮኖሚው መነቃቃት ወሳኝ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ፡፡ አሁንም ግን በኢኮኖሚ እንቅሰቃሴው የአንበሳውን ድርሻ የያዙ ትርፋማ ፋብሪካዎችና ተቋማት አንድም በመንንግስት አለያም ከገዢው ፓርቲ ከተሳሰሩ የንግድ ኩባንያዎች እጅ አለመውጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይሕም ፈጽሞ ጤናማ ኢኮኖሚያዊ እንደማያመጣ ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ ትምባሆን በዘመናዊ መልኩ በፋብሪካ ማምረት የተጀመረው በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ በድሬዳዋ ከተማ በአርመናውያን ባለሃብቶች የተከፈተው የመጀመሪያው ማምረቻ 1931 ነበር ወደ አዲስ አበባአሁን አራዳ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው በኒን አካባቢ የተዛወረው፡፡ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስም በቀን 300 ያሕል ሲጋራዎችን ያመርት ነበር፡፡ የጣሊያኖች መምጣት ፍጆታው ከፍ እንዲል በማድረጉ ላጋር ጉምሩክ አካባቢ ከሃገር እስኪባረሩ ድረስ ያመርቱ ነበር፡፡ ከሃገር ከወጡ ከአንድ ዓመት በኋላ የትምባሆ ምኖፖል 300 ሠራተኞችን በመቅጠር ሥራ ጀመረ፡፡ በወታደራዊው መንግስት ዘመን በአሥመራ ይመረት የነበረውን አይዲያል ሲጋራና እዚያው ይገኝ የነበረውን ክብሪት ፋብሪካ ጠቅልሎ በሚያስተዳድርበት ወቅትብሔራዊ ትምባሆና ክብሪት ኮርፖሬሽንሲባል ቆይቷል፤ የዛሬ 17 ዓመት ገደማ ደግሞ 250 ሚሊየን ብር በአክሲዮን ማሕበርነት ተዋቀረ፡፡

ዲቨሎፕመንት ስተዲስ አሶሼትስ (DSA) እንዳካሄደው ጥናት ከሆነ በኢትዮጵያ የሲጋራ ፍጆታ በየዓመቱ በአማካይ 8 % ጭማሪ እያሳየ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2002 . 1.8 ሚሊየን ሲጋራዎችን በመሸጥ 243 ሚሊየን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያገኘው ትምባሆ ሞኖፖልከአስር ዓመት በኋላ ምርቱን ከሦሥት እጥፍ በላይ አሳድጎገቢውን ወደ 1.1 ቢሊየን ብር ከፍ አደርጋል፡፡ ባለፈው ዓመት አጠቃላይ ገቢው 1.7 ብር የነበረ ሲሆን፣ የተጣራ ትርፉ 400 ሚሊየን ብር ደርሷል፡፡ ትምባሆ ሞኖፖል በዚህ ዓመት የሚያመርተውን ሲጋራ ብዛት 5.9 ሚሊየን ለማድረስ አቅዷል፡፡ ይሕን ለማሳካት በደቂቃ 500 ፓኬት ሲጋራ የሚያመርት ማሽን 145 ሚሊየን ብር ገዝቷል፡፡ በሸዋሮቢት፣ ብላቴ፣ ሐዋሳ እና ወላይታም የትምባሆ እርሻዎች አሉት፡፡ትምባሆ ሞኖፖል ለገበያ የሚያቀርባቸው ኒያላ፣ ግስላ፣ እሌኒ፣ ኒያላ ፕሪሚየም እና ዲላይት ፕሪሚየም ሲጋራዎች ሲሆኑ፣ ኒያላ 80 ከመቶ ገበያውን ተቆጣጥሯል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት 135 ሃገራት ላይ ባካሄደው ጥናት ኢትዮጵያ በዓለም አነስተኛ መጠን ሲጋራ ከሚጨስባቸው ሃገራት አንዷ መሆኗን ጠቁሞ ነበር፡፡ 15 ዓመት ዕድሜ በላይ ካላቸው አዋቂዎች 5 % በታች አጫሽ ከሆኑባቸው 6 የዓለማችን ሃገራትም የኢትዮጵያ ስም ነበረበት፡፡ ይሕም ከጎረቤት ኬንያ 26% ከቻይና 29% አንዲሁም ከአሜሪካ 23% ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ የሚባል ቁጥር ነው፡፡ ይሕ መሰሉ ሁኔታ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት እየተቀየረ ይገኛል፡፡ በሃገሪቱ የሲጋራ ምርት እየጨመረ፣ የአጫሽ ቁጥር እያሻቀበ፣ የአምራቹም ትርፍ እየጨመረ መሄዱ ነው የሚታየው፡፡ በሕዝብ መሰባሰቢያ ሥፍራዎች ሲጋራ እንዳይጨስ የሚከለክል አዋጅ ከዓመታት በፊት ቢጸድቅምከመቀሌና አዲስ አበባ በቀር ለተግባራዊነቱ የረባ ሙከራ እንካ ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ በሕግ ክልከላ ቢጣልበትምየሲጋራ ማስታወቂያዎች ዛሬም ከአደባባይ የሰሌዳ ማስታወቂያዎች ውስጥ አይታጡም፡፡