Addis Ababa City Hall, head of the adminstration
Addis Ababa City Hall, head of the adminstration
  • ለአንድ ካሬ የመኖርያ ቦታ 50ሺህ ብር ቀርቧል

ዋዜማ ራዲዮ- ሦስት ክፍለ ከተሞችን ብቻ ባሳተፈው የ25ኛው ዙር የሊዝ ገበያ በከተማዋ ድንበር ላይ ያሉ ቦታዎች ባልተለመደ ኹኔታ ከፍ ያለ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ኮልፌ ቀራንዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ለዚህ ዙር በድምሩ 107 ቦታዎችን ለቢዝነስ፣ ለመኖርያ ቤትና ለቅይጥ አገልግሎት አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ዉስጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ 20 ቦታዎች፣ ኮልፌ ቀራንዮ 11 ቦታዎችን ብቻ ለጨረታ ሲያቀርቡ አቃቂ ቃሊቲ 96 ቦታዎችን በሊዝ አገበያይቷል፡፡

ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሰፈሮች ለቡ ሰፈር በተደጋጋሚ ውድ ዋጋ የሚቀርብበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አካባቢው የብዙ ባለሐብቶች አይን የሚያርፍበትና ለኑሮ ምቹ የተባሉ ዘመናዊ ቤቶች የተገነቡበት ከመሆኑም ባሻገር የቫርኔሮ ዉድ አፓርትመንቶች የሚገኙበት ዘመናዊ ሰፈር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚወጡ ቦታዎች ከፍ ያለ ዋጋ የሚስቡትም ለዚሁ ነው፡፡

ቀድሞ እንደተፈራውም በዚህ ዙር ለቡ አካባቢ አስደንጋጭ ዉጤት ተመዝግቦበታል፡፡  በኮድ 12309 አገልግሎቱ ለመኖርያ ቤት የኾነ፣ ስፋቱ 208 ካሬ ቦታ፣ አቶ አብረሀም የተባሉ ግለሰብ ለአንድ ካሬ 50ሺ 250 ብር በመስጠት ይህን ጠባብ መሬት በ10 ሚሊዮን 452ሺ ብር የግላቸው አድርገውታል፡፡ በዚህ አካባቢ የቀረቡ ሌሎች አምስት ቦታዎችም በተመሳሳይ ከፍ ያለ ዋጋ የቀረበባቸው ናቸው፡፡

በዚሁ ስፍራ በኮድ 12312 የተወከለ ስፋቱ 1137 የኾነና በአገልግሎቱ ቅይጥ እንደሆነ የተጠቀሰ ቦታ አቶ አብዱልሐሚድ የተባሉ ግለሰብ ለካሬ 40ሺህ 703 ብር በመስጠት መሬቱን በ46 ሚሊዮን 279ሺህ 311 ብር የግላቸው አድርገውታል፡፡ ይህ ስሌት የወለድ ተመን ያልተጨመረበት መኾኑን ልብ ይሏል፡፡

ከሁሉም ላቅ ያለው ዋጋ የቀረበው ለቡ ሴፍዌይ ሱፐርማርኬት አካባቢ ለ1228 ካሬ ቦታ ሲኾን አቶ ኡስማን አሊ የተባሉ ግለሰብ 40ሺ 227 ብር በመስጠት ለ50 ሚሊዮን ጥቂት ብሮች በጎደለው ዋጋ ቦታውን በስማቸው አድርገውታል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤቴል ሆስፒታል አለፍ ብሎ ከቀረቡት አስራ አንድ ቦታዎች በአመዛኙ ለካሬ ከ35ሺህ ብር በላይ የቀረበባቸው ሲኾን በስፋት ግን ሁሉም አነስተኛ ካሬዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ዙር ከቀረቡት ቦታዎች ሁሉ በካሬ ስፋቱ ጠባቡ በቤቴል ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኘው ሲኾን 110 ስኩዌር ካሬ ብቻ ይሰፋል፡፡ አገልግሎቱ ለመኖርያ እንዲሆን ተወስኖ የቀረበው ይህ ቦታ ወይዘሮ ሰላም መዝሙር የተባሉ ግለሰብ የግላቸው አድርገውታል፡፡ ለአንድ ካሬ ያቀረቡት ዋጋ 41ሺህ ብር ሲኾን የወለድ መጠንን ሳይጨምር አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ለመክፈል ፈቅደዋል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ድንበር ሀና ማርያም ሰፈር ከቀረቡ ቦታዎች ምስጋና ሻኪሶ የተባሉ ግለሰብ የዙሩን ዝቅተኛ ሂሳብ በመስጠት ማሸነፋቸው ተነግሯል፡፡ በኮድ 12139 የቀረበና ስፋቱ 311 ካሬ የኾነ፣ አገልግሎቱ ለቅይጥ የተወሰነ መሬት ለአንድ ካሬ 4ሺህ 320 ብር ብቻ በመስጠት በአስገራሚ ዉጤት ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በዚህ ሀና ማርያም ሰፈር የቀረቡ ቦታዎች ለአብዛኛዎቹ መሬቶች የተሰጠው ዋጋ ተቀራራቢ ሲኾን አብዛኛዎቹ ከ11ሺ እስከ 16ሺህ ብር ለካሬ የቀረበባቸው ናቸው፡፡  ከ7ሺህ እስከ 9ሺህ በሚጠጋ የካሬ ዋጋ ያለቁት በቁጥር ከአምስት አይበልጡም፡፡ ይህ ዉጤት ሲታይ 25ኛው ዙር ካለፉት ተከታታይ የሊዝ ጨረታ ዙሮች አንጻር አነስ ያለ ዋጋ የቀረበበት ቢመስልም ከመሐል ከተማ ለራቁና በአመዛኙ ለኢንደስትሪ እንጂ ለኑሮ እንደማይመቹ በሚታሰቡ እንደ አቃቂና ሀና ማርያም ሰፈሮች እንዲህ አይነት ከፍ ያለ ዋጋ መሰጠቱ የከተማዋን የመሬት ፍላጎት ንረት አሁንም እየጋለ መምጣቱን የሚመሰክር ተደርጎ ተወስዷል፡፡

በቀጣይ የ26ኛ ዙር ሊዝ መስተዳደሩ ዋጋ ለማረጋጋት በሚል በርከት ያሉ ቦታዎችን በአንድ ጊዜ ለጨረታ ለማቅረብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ዋዜማ ከለማ መሬትና ሊዝ ጽሕፈት ቤት ያገኘቸው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለባለ ኮከብ ሆቴሎች ብቻ የሚኾኑ ከፍተኛ ባለሐብቶችን ለይተው የሚያሳትፉ ልዩ ጨረታዎችም በቅርብ ሳምንታት ዉስጥ በተከታታይ ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡