lamb(ዋዜማ ሬድዮ)-የኢትዮዽያ ፊልሞች በቁጥርና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በቴክኒክ ብቃት መሻሻል ቢያሳዩም ሙያው የሚጠይቀውን ክህሎት በመላበስ በኩል ግን ገና ሩቅ ናቸው። በተለይ የታሪክ አመራረጣቸው “ብግን” የሚያደርግ “አሰልቺና ተደጋጋሚ” መሆኑን የፊልም ተመልካቹ በአንድ ድምፅ ይስማማል። በዚህ ሁሉ መሀል የፈረንጁን አለም ፊልም ሰሪዎችን ቀልብ መግዛት የቻሉና ለሽልማትም የታጩ ኢትዮዽያዊ ፊልሞች አልታጡም። “ፈረንጆቹ ስለኛ መስማትና ማየት የሚፈልጉትን ካቀረብን ሰሚ ሳናገኝ አንቀርም”  የሚሉ አስተያየት ስጪዎች ልክ ሳይሆኑ አልቀሩም። በሲኒማው ዓለም ምናልባትም ኩራት ራት አይኾንም!

(መዝገቡ ሀይሉ ያዘጋጀውን መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች-አድምጡት)

በያሬድ ዘለቀ የተሰራውና በእንግሊዘኛው ላምብ ተብሎ የተሰየመው ፊልም በፈረንሳይ ካን በሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በመቅረብ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም ኾኗል። ይህ ላምብ የተሰኘ ፊልም እድሉን ከማግኘቱም በተጨማሪ በተለያዩ የፊልም ሐያስያንም ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እንዳገኘ የሚያሳዩ አስተያየቶች እየተሰጡትም ይገኛል።
ለ 3 የተለያዩ ሽልማቶችም በእጩነት ቀርቦም ነበር። ይህን በሐያስያኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን ፊልም የሰራው ያሬድ ዘለቀ የኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የሲኒማ ትምህርት ቤት ምሩቅ ነው። ላምብ የያሬድ የመጀመሪያው ፊልም እንደመኾኑ መጠን በቀጣይም በሚያደርገው የሲኒማ ስራው ተስፋ የሚጣልበት እና ብዙ የሚጠበቅበት ባለሙያ እንደሚኾንም ግምት አሳድሯል።

ላምብ በውጪው ዓለም ባሉ የፊልም ባለሙያዎች ዘንድ በዚህ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችሉትን ባሕርያት በአብዛኛው ያሟላ መኾኑን ከሐያሲዎቹ አስተያየቶች ለመረዳት ይቻላል። በጥሩ የሲኒማ አቀራረጽ መቅረቡ፣ ውብ የኾነውን የገጠሪቱን ኢትዮጵያ መልክዓምድር መርጦ ያሳየበት መንገድ ከተደነቁለት የፊልሙ ባሕርያት መካከል ናቸው። ይህ ምናልባትም ኢትዮጵያውያን ተመልካቾችም ሊያደንቁት የሚችሉት የፊልሙ ገጽታ ነው።

የምዕራቡ ዓለም ስለኢትዮጵያ ሊያየውና ሊሰማው የሚፈልገውንም የኢትዮጵያን ገጽታም አልነፈገውም። ድርቅ፣ ረሃብ፣ ችግር፣ ችግር፣ ጭለማ፣ ሞት፣ እንስሳት እነኚህን ሌላው ዓለም ስለኢትዮጵያ ሲያስብ የሚመጡለትን የአዕምሮ ስዕሎች አልተቃወማቸውም። ሊያዩት የሚፈልጉትን አሳይቷቸዋል። ምናልባት እነኚህም ተቀባይነትን ካገኘባቸው ብዙ ምክንያቶች መካከል ስፍራ ይኖራቸዋል።

በቅርቡ የአሜሪካን ሚዲያዎች ትኩረት አግኝቶ የነበረውም ሌላውdifret ፊልም ድፍረትም በውስጡ የያዘው ሌላውን ችግራችንን ነው። ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ ጥቃት የፊልሙ ዋንኛ ጉዳይ መኾኑን ልብ ይሏል።
ላምብ የፊልሙ ታሪክ የሚያጠነጥነው በልጅነቱ እናቱ በረሃብ የሞተችበት የ9 ዓመት ልጅ ከበጉ ጋር የነበረውን ፍቅር በማሳየት ላይ ነው። በረሃቡ ምክንያት በሌላ አካባቢ ወዳሉ ዘመዶቹ ጋር ሔዶ ለመኖር የተገደደው ትንሽ ልጅ ጓደኛውና አጫዋቹ ከኾነች አንዲት በግ ጋር ወደ ዘመዶቹ ቤት ይሔዳል። የእርሻ ስራውንም የዘመዶቹንም ቁጣ አልወደደውም። ይህ አልበቃ ብሏቸው ወዳጁ የኾነችውን በግ ሊያርዱበት ሐሳብ ያቀርባሉ። በጉን ለማዳን ሲል ዳግመኛ ስደት የመረጠው ትንሽ ልጅ የመጓጓዣ ገንዘብ ለማግኘት ሳምቡሳ ለመሸጥ ሲገደድ ይታያል።ያሬድ ይህን ታሪክ ሲተርክ እግረ መንገዱን የገጠሪቱን ኢትዮጵያ ችግር የሞላበት ኑሮና ዐይን የሚያማልል መልክዓ መድር እያሳየ ይቀጥላል ።
ይህን የመሰለ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት መቼም የብዙ ፊልም ባለሞያዎቻችን ምኞት መኾኑ አያስገርምም። በጅምር ላይ ባለው የኢትዮያ ሲኒማ ዓለም ውስጥ ኾኖ ከሌላው ዓለም የፊልም ኢንደስትሪ ጋር ለውድድር እንኳን በማይቅርብ የገንዘብ ወጪና የፊልም መስሪያ ቁሳቁስ ተሰርቶ እዚህ ዕውቅና ላይ መድረስም ትልቅ ፈተና መኾኑን የፊልም ባለሞያ ያልኾንም ሰው ሊገምተው ይችላል።

ከዚያም ሁሉ በላይ ግን ለዓለም ተመልካች ይዘነው የምንወጣው ታሪክ እነርሱ ሊያዩት በሚፈልጉት እና እኛ ብናሳያቸው ደስ በሚለን ማንነታችን መካከል ያለውም ልዩነት በቀላሉ የማይታለፍ ሊኾን ይችላል። ፍቅራችንን፣ ማኅበረሰባዊ ኩራታችንን፣ ጀግንነታችንንና ስለ ሕይወት ያለንን የተለየ አመለካከት አሳይቶ ተቀባይነት ማግኘትም ፈተና ሊኾን ይችላል። በሲኒማው ዓለም ምናልባትም ኩራት ራት አይኾንም።