TPLF Chair Dr Debretsion G/Michael- PHOTO -Fortune
TPLF Chair Dr Debretsion G/Michael- PHOTO -Fortune

ዋዜማ ራዲዮ-በህወሀት ዝግና ምስጢራዊ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባዔ የደህንነት ሀላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋና ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አሸናፊ ሆነው ወጥተዋል። ትዕግስትና የመግባባት ችሎታ ለሚያንሳቸው ዶ/ር ደብረፅዮን ዝቅተኛ የካድሬነት ልምዳቸው ተደምሮበት በፓርቲው ውስጥ “ምንም አዲስ ነገር ሊያመጡ አይችሉም” ሲሉ ከወዲሁ ትችት የሚያቀርቡ አሉ። ለመሆኑ አዲሱ የህወሀት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ማን ናቸው? ከመጋረጃ ጀርባ ህወሀት ሰለተነጋገራቸውና ውሳኔ ስላሳለፈባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ለምን ሸሸገን? ቻላቸው ታደሰ የሚከተለውን ፅፏል ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ያገኛሉ

ኢሕአዴግ መራሹ መንግስት በህዝባዊ አመጽ እና እያደገ በመጣ ብሄር ግጭት በተጠመደበት ሰዓት ካንድ ወር ለበለጠ ጊዜ መቀሌ ላይ ስብሰባ ተቀምጦ የከረመው የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር ደብረ ፂዮን ገብረ ሚካዔልን በሊቀመንበርነት፣ ወይዘሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚያብሄርን ደሞ በምክትል ሊቀመንበርነት መምረጡን  አስታውቋል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው ዶክተር ደብረጺዮንን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠው እንግዲህ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የሕወሃት ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱን በግምገማ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ካሰናበተ በኋላ ነው፡፡
በርግጥም አቶ አባይ ወልዱ የአስኳሉ የሕወሃት ሊቀመንበር በሆኑበት ወቅት ከፌደራሉ መንግስት እና ዋና መቀመጫውን አራት ኪሎ ላይ ካደረገው ኢሕአዴግ የተነጠሉ ስለነበሩ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ፖለቲካ ተጽዕኖ የነበራቸው ሰው እንዳልነበሩ ግልጽ ነው፡፡ ዶክተር ደብረጺዮን ግን የፌደራሉን መንግስትም ሆነ የገዥውን ግንባር ውስጣዊ ፖለቲካ አጣምረው ሁነኛ ሚና ለመጫወት እድል ያገኛሉ፡፡

ህወሀት በሀገራዊ አጀንዳ ላይ ለምን ለብቻው ይነጋገራል?
ማዕከላዊ ኮሚቴው በሀገሪቱ ስለሚታየው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ከኤርትራ ስለሚኖረው ግንኙነት እና ስለ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአመራር ብቃት ጭምር አንስቶ ሲመክር እንደከረመ የዋዜማ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመው ሳለ ድርጅቱ ግን በመግለጫው በአመራር ሽግሽጉ ላይ ብቻ ያተኮረው፡፡ ይህም ሚስጢራዊ ከሆነው የሕወሃት ተፈጥሮ የሚመነጭ እና ራሱ ሕወሃትም የሚያምነው ባህሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዋናነት ግን ሕወሃት ዛሬም ከተቸከለበት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ሳይላቀቅ በዋናነት ቡድናዊነት ባጠላባቸው ውስጣዊ ድርጅታዊ ጉዳዮች ብቻ ተጠምዶ መክረሙን የሰሞኑ ግምገማ ውጤት ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በርግጥም ርዕዮተ ዐለማዊ ጥራት በሚጎድላቸው የተወናበዱ የገዥው ግንባር ፖሊሲዎች እና ሀገራዊ ራዕይ ባነገበ አመራር እጥረት ሳቢያ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የገባቸው ኢትዮጵያ አሁንም በዋነኛት የተራማጅነት እንጥፍጣፊ በሌለው ነጻ አውጭው ሕወሃት እየተመራች መቀጠሏ ለብዙ የውጭ ታዛቢዎች እንቆቅልሽ ነው የሚሆንባቸው፡፡
የሰሞኑ ግምገማ እና የአመራር ለውጥ የሚያሳየው እንግዲህ አቶ መለስ በሕይወት እያሉ በአምስት ዐመታት ውስጥ በየምዕራፉ እንደሚተገበር ይናገሩለት የነበረው የአመራር መተካካት ጉዳይ በሕወሃት ዘንድ ውሃ በልቶት እንደቀረ እና የተከተለው መንገድ ቡድናዊነት ባጠላበት ግምገማ ነባር አመራሮቹን ከሃላፊነት ማንሳት መሆኑን ነው፡፡
የሰሞኑ ሁኔታዎች የሚሳዩት ነባሩ አመራር ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ለመዝለቅ ያለውን ዝግጁነት የሚጠቁም ነው፡፡ በመጭው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔም በወጣት ወይም ለውጥ ፈላጊ አባላቱ እና በነባሩ አመራር መካከል ሁነኛ ፖለቲካዊ ፍጭት ተደርጎ ለውጥ ናፋቂው አዲሱ ሃይል አሸናፊ ሆኖ ካልወጣ አሮጌው ነባር አመራር ሁነኛ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ለመውሰድ የሚኖረው ቁርጠኝነት እምብዛም ነው የሚሆነው፡፡ እናም ሕወሃት ባሁኑ ወቅት በመንግስትም ሆነ በገዥው ግንባር ውስጥ መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችለው ቁርጠኝነት በእጅጉ አጠራጣሪ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ጊዜውን የሚመጥኑ ማሻሻያዎችን ያፈልቃል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡

ሕወሃት ለመንግስት አዳዲስ ፖሊሲዎች እና ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመምጣቱ ዕድል አነስተኛ ቢሆንም ላለፉት ሦስት ዐመታት ያሳየውን ድርጅታዊ መዳከም ግን በመጭው መጋቢት በሚካደው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ አሻሽሎ ለመቅረብ ሲዶልት እንደከረመ መገመት አያስቸግርም፡፡ በርግጥም የዋዜማ ምንጮች እንዳሉት ሥራ አስፈጻሚው በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም የአመራር ብቃት ላይ ተወያይቶ ሁነኛ ውሳኔ ላይ ደርሶ ከሆነ በቀጣዩ መጋቢት በሚካሄደው የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነቱን እና የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታውን መልሶ ለመያዝ የማሰቡ ነገር ጨርሶ ዝግ አይደለም፡፡

እናም ከመጋቢቱ የኢሕአዴግ ጉባዔ በፊት ወይ በጉባዔው ወቅት ኦሕዴድ እና ብአዴን በጋራ ወይም በተናጥል በፖለቲካ ስልጣን እና ሃብት ክፍፍል ረገድ ሁነኛ አቋም ይዘው ብቅ ካላሉ እና የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም ባለበት ከቀጠለ ሕወሃት በቀጣዩ ምርጫ በትምህርት የላቁትን ዶክተር ደብረጺዮንን ለጠቅላይ ሚንስትርነት ይዞ ሊቀርብ ይችላል፡፡
በርግጥ ካፉት ሁለት ዐመታት ወዲህ ኢሕዴድ እና ብአዴን በኢሕአዴግ ውስጥ ሕወሃትን ሙሉ በሙሉ ባይገዳደሩም እንኳ የወሰኑ ጥቅሞቻቸውን ማስጠበቅ የሚችሉበት አንጻራዊ መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁን ባላቸው ቁመና ግን በቅርቡ የሃይል ሚዛኑን የማስተካከል እድላቸው አናሳ ይመስላል፡፡ እናም ከመጋቢት በኋላም በዶክተር ደብረጺዮን የሚመራው ሕወሃት የበላይነቱን አስጠብቆ የመቀጠል እድሉ ሰፊ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

የዶክተር ደብረፂዮን ስውር መሰላል
የሰሞኑ ግምገማ ዶክተር ደብረፂዮን እና የደህንነቱ ሹም አቶ ጌታቸው አሠፋ አሸናፊ ሆነው የወጡበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ አቶ ጌታቸው አሠፋ ለአቶ መለስ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ ቀኝ እጅ የነበሩትን ምክትላቸውን አቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስን ከዐመት በፊት ከመስሪያ ቤቱ ማሰናበት ችለው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካ ሳይንስ እና ከሰላም እና ደህንነት ጥናት ተቋም ያገኟቸውን ሁለት የድህረ ምረቃ ዲግሪዎች በመጥቀስ የአቶ ጌታቸው ቦታ እንዲሰጣቸው በግልጽ ስብሰባ ጭምር ይወተውቱ የነበሩት ሌላኛው የደህንነት ሹም እና የአድዋ ተዋላጁን አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካዔልን ደሞ ከስራ አንሳፍፈው ካቆዩ በኋላ በሙስና አስወንጅለው ከሦስት ዐመታት በፊት ዘብጥያ አስወርደዋቸዋል፡፡ በርግጥም አቶ ጌታቸው አቶ ኢሳያስን ሲያሰናብቱ እና ወልደ ሥላሴን ወደ ወህኒ ቤት ሲልኩ የወይዘሮ አዜብ መስፍንን ደጃፍ ለማንኳኳት የመጨረሻውን እንቅፋት እንዳስወገዱ ግልፅ ነበር፡፡ በርግጥም ወይዘሮ አዜብ ሰሞኑን ከሕወሃት አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ መታገዳቸው የዚሁ ሂደት መቋጫ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በድርጅቱ ከያዙት ሃላፊነት አንጻር ዶክተር ደብረፂዮን ሊቀመንበር መሆናቸው ባይደንቅም ሰውዬው ግን ለፖለቲካ የሚመጥን ልምድም ሆነ ተፈጥሯዊ ጠባይ ስለሌላቸው በብዙ ወገኖች ዘንድ ግርምት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ደብረ ፂዮን በበረሃ ትግል ወቅትም በሕወሃት ሬዲዮ ጣቢያ በቴክኒኩ ዘርፍ እንጂ በካድሬነቱም ሆነ በድርጅት ፖለቲካዊ አመራር ልምድ ያላቸው ሰው አይደሉም፡፡ ከ1983 ጀምሮ ደሞ ለረዥም ዐመታት በደኅንነቱ መስሪያ ቤት ውስጥ ከአቶ ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ በተጨማሪ የሟቹ ክንፈ ገብረ መድኅን ምክትል ሆነው ሲሰሩ ስለኖሩ አብዛኛው ልምዳቸው ከደኅንነት ሙያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በደኅንቱ መስሪያ ቤት ውስጥም የመሠረታዊ ደኅንነት ኪነ ሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በማቋቋም በሃላፊነት መርተዋል፡፡ ማሰልጠኛው ነባሮቹን የደህንነቱ ባልደረቦች እና አዳዲስ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎችን ተቀብሎ ለጥቂት ዐመታት ማሰልጠን ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ተቀዛቅዟል፡፡
ከ1993 የሕወሃት ክፍፍል በኋላ ግን አቶ መለስ ደብረ ፂዮንን ከደህንነቱ አንስተው ወዳንድ የትግራይ ክልል ዞን መድበው ልከዋቸው ነበር፡፡ በኋላም የክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ሆነው ከቆዩ በኋላ ነው የሀገሪቱ ቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ መስፋፋቱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የቴሌኮሚኒኬሽን ሚንስትር የሆኑት፡፡ ይህን ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ ደሞ የኢንፎርሜሽን ኔትወርክ ኤጀንሲን ከማቋቋም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመምራት ላይ ስለሆኑ ዞሮ ዞሮ ከደኅንነት እና መረጃ ስራ ሳይርቁ ነው የቆዩት፡፡
ዶክተር ደብረጺዮን የማሳመን ችሎታ፣ ፖለቲካዊ ብልጠት እና የመደራደር ችሎታ እንዲሁም ሀገራዊ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ሰፋ አድርጎ ለማየት ትዕግስት ያጥራቸዋል ሲሉ በቅርብ የሚውቋቸው ይገልጧቸዋል፡፡ ከጥቂት ዐመታት በፊት ሚንስትር ሳሉ አንዴ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንን ሰብስበው ሲያናግሩ መምህራኑ መንግስት ደመወዝ እንዲጨመርላቸው ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ ደብረፂዮን ፈጣን ግን ደሞ አስደንጋጭ ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ “ደመወዝ አንጨምርም፤ ከፈለጋችሁ በትርፍ ጊዚያችሁ ከዩኒቨርስቲው ውጭ የማማከር ስራ እየሰራችሁ ራሳችሁን መደጎም ትችላላችሁ” ነበር ያሉት፡፡ ከህዝብ በሚሰበሰብ ቀረጥ ደመወዝ የሚከፈላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመህራን ትርፍ ጊዚያቸውን ለዩኒቨርስቲያቸው እና ለሀገሪቱ እድገት በሚጠቅሙ የምርምር ስራዎች እንዲያውሉ መምከር ሲገባቸው እውቀታቸውን ለዐለም ዐቀፍ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሸጡ መገፋፋታቸው ካንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ያልተጠበቀ ነበር፡፡

አባይ ወልዱ በክልል ፕሬዝዳንትነት ይቀጥላል?
አቶ አባይ ወልዱ ከህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስለተነሱ ምናልባት በቅርቡ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያካሂድ የትግራይ ክልል ርዕስ መስተዳድርነቱን ጭምር እንደሚለቁ መጠበቅ ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደሞ በድርጅቱ ህገ ደንብ መሠረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል ያልሆነ ሰው የክልሉን መንግስት ሊመራ የማይችል መሆኑ ነው፡፡ ያም ሆኖ ዶክተር ደብረጺዮን የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣን በመሆናቸው የሕወሃት ሊቀመንበር ቢሆኑም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የመሆን እድላቸው ግን ላሁኑ ዝግ ነው፡፡ ምናልባት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር አዲስ ዐለም ባሌማ ቦታውን ይይዛሉ ተብሎ እንዳይጠበቅ ደሞ በሰሞኑ ስብሰባ በማስጠንቀቂያ የታለፉ መሆናቸው መሰማቱ እድሉን ዝቅተኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ሕወሃት እስካሁን ሊቀመንበሩ አዲሳባ ተቀማጭ ከሆነ ምክትሉ መቀሌ ላይ መቀመጥ አለበት የሚል ደንብ ባይኖረውም በውስጣዊ አሰራሩ ግን ይህንኑ ሊከተል እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

አሽናፊው አንጃ
ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግዲህ ባሁኑ ግምገማ አሸናፊ ሆኖ የወጣ የሚመስለው የአንጋፋው ፖለቲከኛ የአቶ ስብሃት ነጋ ቡድን በተለይ ከኤርትራ ጋር እርቅ እንዲፈጸም የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለው ነው የሚገመተው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ሕወሃት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ያሉ መምራንን እና ሌሎች ያገባኛል ባይ የትግራይ ተወላጆችን በመጠቀም ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበትን እና ውሉ ያልለየለትን ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት በተለይ ትግራይ ክልልን በልማት ተጎጅ እንዳደረጋት በመግልጽ መፍትሄ እንዲበጅለት ጥሪ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተደጋግመው መሰማት መጀመራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በርግጥም ሕወሃት ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል ከኤርትራ በኩል የሚመጡበትን አደጋዎች መዝጋትን እንደ ሁነኛ አማራጭ ማየቱ አይቀሬ ይመስላል፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ ዶክተር ደብረጺዮን ሕወሃትን እና ከቀውስ መውጫ ያጣውን ገዥውን ኢሕአዴግ ወዴት አቅጣጫ ይወስዱት ይሆን? የሚለው በቀጣይ ወራት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡