ዋዜማ ራዲዮ- የጸረ-ሙስና ኮሚሽን መስሪያ ቤት በ2006ዓ.ም ጀምሮት የነበረውን የመንግስት ሰራተኞችና ባለስልጣናትን የሐብት ምዝገባ ወደ ብየነ መረብ ስርዓት  ቀየረ፣ ዛሬ የካቲት 11፤ 2014 አዲሱን ቴክኖሎጂ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በህንዱ ሲ.ኤስ.ኤም ቴክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የተሰራው የብየነ መረብ የሃብት መመዝገቢያ ስርዓት ተጠናቆ ስራ ለመጀመር ስምንት አመታትን የፈጀ ሲሆን ለዚህም የቀደመው የመንግስት የአሰራር ሂደት ብልሹ መሆን ምክንያት እንደነበር የኮምሽኑ የሐብት ምዝገባ እና ማረጋገጥ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ መስፍን በላይነህ ያስረዳሉ።

አዲሱን ቴክኖሎጂ ለመግዛት እና ስራ ላይ ለማዋል 198 ሺህ የአሜሪካን ዶላር (10 ሚሊየን ብር ገደማ) ወጪ ተደርጎበታል፡፡

የኮሚሽን መስሪያቤቱ አዲሱን ቴክኖሎጂ ካሳተዋወቀ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሐብታቸውን ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

ኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ሐብታቸውን ያስመዘገቡ ሰራተኞች ሰነድ እንደ ሪከርድ የሚያዝ ሲሆን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ግን ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ሐብታቸውን እንደ አዲስ ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ 

የሐብት ምዝገባውን ተከትሎ በአቃቤ ህግ እና በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘ ግለሰቦች ግን አዲሱ ምዝገባ አይመለከታቸውም፡፡

አንድ የመንግስት ሰራተኛ የሆነ ግለሰብ አዲሱን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ያለውን ሐብት  ማስመዝገብ ሲፈልግ ወደ ኮሚሽኑ ድረ-ገፅ ይሄድና የሐብት ማስመዝገቢያ የሚገኝበትን መስፈንጠሪያ (ሊንክ) ተጠቅሞ ምዝገባውን ማካሄድ ይችላል።

ከዚህ በፊት ነበረው የሃብት ምዝገባ ሂደት በወረቀት ላይ ብቻ በመሆኑ ብዙ እንከን እንደነበረበት ለዋዜማ የገለጹት አቶ መስፍን በላይነህ የአሰራር ስርአቱን ወደ ድረ-ገፅ መቀየሩ ኮሚሽን መስሪያ ቤቱ በሚሊዮኖች የሚያወጣበትን የወረቀት ፍጆታ ወጪ እንደሚያስቀርለት የገለጹ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የሐብት ምዝገባው በወረቀት በነበረበት ወቅት የነበረውን የደህንነት ስጋት ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር እና የኮሚሽን መስሪያ ቤቱን ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሚያጎለብት ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የሙከራ ሂደቱ የተፈጸመው በራሱ በጸረ-ሙስና ኮሚሽን መስሪያ ቤት ሲሆን የኮሚሽን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ሐብታቸውን እንዳስመዘገቡ ቀሪዎቹም እያስመዘገቡ እንደሆነ ተረድተናል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]